የግንባታ ፕሮጀክቶች የሚመሩበት አዲሱ የኮንስትራክሽን ኮድ ከአምስት ዓመታት በኋላ በአስገዳጅነት እንደሚተገበር፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
አዲሱ ኮድ የኮንትራክተሮችን፣ የአሠሪዎችን፣ የሠራተኞችንና የሁሉንም የፕሮጀክት ተሳታፊ አካላት መብትና ግዴታ የሚወስን ሲሆን፣ በሁሉም ዘርፎች ላይ የመተግበሪያ ደረጃዎች ተዘጋጅተውለታል።
አዲሱ ኮድ ለኮንትራክተሮችና ለአሠሪዎች የተዘጋጁ 19 የሥራ ስታንዳርዶች (ማኑዋሎች) እንዳሉት፣ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የሥርዓት ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ አበራ አውግቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል።
‹‹ማኑዋሎቹ ከፕሮጀክት ዕቅድ እስከ ማጠናቀቂያ ድረስ ያለውን አሠራር በግልጽ ለማሳየት የሚያስችሉ ሆነው የተዘጋጁ ናቸው፤›› ብለው፣ የሠራተኞች ደኅንነት በኮዱ ውስጥ ተፈጻሚነት ካላቸው ዋና ዋና መመርያዎች ውስጥ አንዱ መሆኑን፣ የኮንስትራክሽን ዘርፉን እየተፈታተኑ ያሉት የወጪ አስተዳደር፣ ግዥ፣ ኮሙዩኒኬሽን፣ የግንባታ ጊዜና ሌሎች መመርያዎች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሠራተኞችን የሚያሳትፈው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ለሠራተኞች የሥራ ቦታ ደኅንነት ሥጋት ያለበት ሲሆን፣ አስገዳጅ የደኅንነት ሥርዓት አለመኖሩ ለኮንትራክተሮችም ሆነ ለሠራተኞቹ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ነው። በዚህም መሠረት አዲሱ ኮድ የግንባታ ፕሮጀክቶች ሲቀርቡ በዋጋ ዝርዝራቸው ውስጥ ለደኅንነት የሚመደብ በጀት በአስገዳጅነት ይጠየቃል። ‹‹ተቋራጮች ለደኅንነት ምንም ዓይነት በጀት ስለሌላቸው ሠራተኞቹ በአደጋ ጊዜ ዋስትና አይኖራቸውም፤›› ያሉት አቶ አበራ፣ አሠሪዎቹ የደኅንነት ወጪን የመቀበል ግዴታ አለባቸው ብለዋል።
‹‹ኮዱ እንደታቀደው ከአምስት ዓመታት በኋላ አስገዳጅ ይሆናል። ነገር ግን አሁን ለኮንትራክተሮችና ለአሠሪዎች እየተሰጠ የሚገኘው ማኑዋል በተሻለ ሁኔታ የአስገዳጅነት ጊዜው ወደ ሦስት ዓመት ዝቅ ይላል፤›› በማለት ገልጸዋል።
የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አንዱ ፈተና የሠራተኞችን ደኅንነት አለመጠበቅ በመሆኑ፣ አዲሱ ኮድ ይህንን ችግር የሚቀርፍ እንደሚሆን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዚዳንት ግርማ ኃይለ ማሪያም (ኢንጂነር) ገልጸዋል።
አሠሪውም ሆነ ኮንትራክተሩ ለደኅንነት ቅድሚያ በመስጠት በራስ ላይ የሚኖርን ሥጋት መቀነስ የሚያስችል አሠራር እንደሚሆን የገለጹት ግርማ (ኢንጅነር)፣ በደኅንነት ላይ የሚሠሩ በቂ ባለሙያዎች ባለመኖራቸው ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ሥልጠና ሊሰጡ ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
ሌላው የኮንስትራክሽን ዘርፉ ፈተና የግንባታ ዕቃዎች የዋጋ ንረት ሲሆን፣ ይህም ፕሮጀክቶች በታሰበላቸው ጊዜና በጀት እንዳይጠናቀቁ በማድረግ በአሠሪዎችና በኮንትራክተሮች መካከል አለመግባባት እንዲፈጠርና ፕሮጀክቶችም እንዲቋረጡ እያደረገ ነው ብለዋል፡፡ በመሆኑም ኮንትራክተሮች የፕሮጀክቶችን ዋጋ ሲያወጡ በቂ ግምገማ በማድረግና የሚኖረውን የዋጋ ንረት ግምት ውስጥ በማስገባት ኪሳራና አለመግባባትን የሚያስቀሩ ሳይንሳዊ መንገዶችን እንዲከተሉ የሚያደርግ እንደሚሆን አቶ አበራ አስረድተዋል።