Monday, December 5, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊበኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች የተከሰተው ድርቅ የቁም እንስሳት ገበያ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንደሚያሳድር...

  በኦሮሚያና ሱማሌ ክልሎች የተከሰተው ድርቅ የቁም እንስሳት ገበያ ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንደሚያሳድር ተገለጸ

  ቀን:

  በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ የቁም እንስሳት ሞት ምክንያት የሆነው የኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ድርቅ፣ የቁም እንስሳት የአገር ውስጥ ገበያንና ቀድሞውንም የተቀዛቀዘውን የኤክስፖርት ዘርፍ በከፍተኛ መጠን እንደሚጎዳ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

  ከፍተኛ የሆነ የቁም እስስሳት ሀብት ባለበት ቦረናና የሶማሌ ክልል ድርቅ ከመከሰቱ በፊት መሠራት የነበረባቸው እንደ ቅድመ ዝግጅት ማድረግ፣ ትንበያ መሥራት፣ መፍትሔ ማበጀት ሥራዎች በቅንጅት እንዳልተሠሩ በሚኒስቴሩ የቁም እንስሳት፣ ቆዳና ሌጦ ግብይት ዳይሬክተር አቶ ዴስነት በላይ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ይኼ ችግር የተፈጠረው በዘርፉ ላይ ድርሻ ያላቸው ተቋማት ቅንጅት ለመፍጠር ባለመቻላቸው ነው፡፡

  ድርቁ ከተከሰተ በኋላ በድርቅ የተጎዱ እንስሳትን በጊዜያዊነት ወደ ሌላ ቦታ ማዘዋዋር፣ እንስሳቱ ባሉበት መኖ እንዲያገኙ ማድረግ፣ እንዲሁም ከላኪዎች፣ ነጋዴዎችና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር ትስስር በመፍጠር የገበያ ዕድል እንዲያገኙ የማድረግ መፍትሔዎች መሞከራቸውን አስረድተዋል፡፡ ይሁንና እነዚህ ሥራዎች እንስሳቱ ላይ የደረሰውን ጉዳት እንዳላስቆሙና አርብቶ አደሮች ላይ ከደረሰው ጉዳት ባሻገር የቁም እንስሳት ገበያው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ገልጸዋል፡፡

  አቶ ዴስነት ‹‹በንግድ ሒደቱ ላይ የሚያዛባው፣ የሚቀንሰው፣ ሚያከስረው ነገር አለ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር የሚያሳጣን ከፍተኛ ሀብት እንደሆነ መረዳት ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡

  በተከታታይ የዝናብ ወቅቶች እርጥበት ባለማግኘታቸው የተራዘመው የኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ድርቅ ሚሊዮኖችን ዕርዳታ ጠባቂ ከማድረጉ ባሻገር፣ የአርብቶ አደሮች ሀብት የሆኑትን እንስሳት በከፍተኛ መጠን ገድሏል፡፡

  ድርቁ ከፍተኛ የቁም እንስሳት ሀብት ባለበት ቦረና ብቻ እስካሁን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሆኑና ዋጋቸው 7.3 ቢሊዮን ብር የሚገመት እንስሳትን ገድሏል፡፡ ከዚህም በላይ 481 ሺሕ ከብቶች በሞት አፋፍ ላይ ሲሆኑ፣ የቦረና ዞን አስተዳደር ድርቁ በዚሁ ከቀጠለ ተጨማሪ ከ900 ሺሕ በላይ ከብቶች እንደሚሞቱ ሥጋቱን ገልጿል፡፡

  ይኼ ቁጥር በሶማሌና በሌሎች ድርቅ ባለባቸው የአገሪቱ ክፍሎች ከተከሰተው የእንስሳት ጉዳት ጋር ሲደመር ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከ100 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ ያሳየውንና የሚላክባቸው አገሮች ብዛት ከግማሽ በላይ የቀነሰበትን የቁም እንስሳት ኤክስፖርት ዘርፍ ይበልጡኑ ይጎዳዋል፡፡

  የኢትዮጵያ የቁም እንስሳት ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ክብሬ ሙላት እንደሚናገሩት፣ ይኼ ወቅት የኤክስፖርት መጠን የቀዘቀዘበት በመሆኑ ድርቁ የሚያስከትለው ተፅዕኖ እስካሁን በጉልህ አልተስተዋለም፡፡ ይሁንና ብዙዎቹ የኢትዮጵያን የቁም እንስሳት የሚያስገቡት ዓረብ አገሮች ከመሆናቸውና በቀጣይ የረመዳን ፆም የሚገባ በመሆኑ፣ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ውስጥ ድርቁ የሚያስከትለው ጉዳይ በግልፅ ይታያል፡፡

  የረመዳን ወቅት ገበያ የሚጨምርበት መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቷ፣ በዚህ ጊዜ ድርቁ ካለበት አካባቢ የሚመጡ እንስሳት የክብደት መቀነስ እንደሚያጋጥማቸው አስረድተዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ እንስሳት በመሞታቸውና በተለይ በቦረና ያሉ አርብቶ አደሮች ድርቅ ሲከሰት ከብቶቻቸውን ይዘው ወደ ጎረቤት አገር ኬንያ የመጓዝ ልምድ ስላላቸው፣ ላኪዎች የሚፈልጉትን ያህል መጠን የሆነ የቁም እንስሳት ለመላክ እንደሚቸገሩ ተናግረዋል፡፡

  ‹‹ለገበያ የሚፈለጉ እንስሳትም ጭምር እየሞቱ ነው›› ያሉት ወ/ሮ ክብሬ፣ ላኪዎች ወቅቱን ተከትሎ በሚቀጥለው ወር ላይ ከሚፈጽሙት ግዢም ባሻገር ለወደፊቱም ገበያውን ሊጎዳ እንደሚችል አክለዋል፡፡

  የቁም እንስሳት፣ ቆዳና ሌጦ ግብይት ዳይሬክተሩ አቶ ዴስነት አሁንም ቢሆን የሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ያስቀመጠውን ቅድመ ትንበያ ተከትሎ ለአርብቶ አደሩና ለእንስሳቱ አደጋውን መቀነስ የሚቻልበት ሁኔታ ሊሠራበት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴሩ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት መፍትሔ እንዲያበጁ የሚረዳ የቅንጅት ዕቅድ ለማውጣት እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

  የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የ2013 ዓ.ም. መረጃ እንደሚያሳየው፣ ኢትዮጵያ 70.2 ሚሊዮን የዳልጋ ከብት፣ 52.5 ሚሊዮን ፍየል፣ 42.9 ሚሊዮን በግ እና 8.1 ሚሊዮን ግመል በመያዝ በእንስሳት ሀብት ከሚጠቀሱ የአፍሪካና የዓለም አገሮች አንዷ ነች፡፡ የቁም እንስሳት ዘርፉ ለጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ከ12 እስከ 16 በመቶና ለግብርና ምርት 30 በመቶ አስተዋፅኦ አለው፡፡

  ከዚህ ባሻገር ዘርፉ ከ60 እስከ 70 በመቶ ለሚሆኑ ኢትዮጵያውያን አኗኗር በቀጥታና በተዘዋዋሪ አስተዋፅኦ ያደርጋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  ዳግም ነፍስ የዘራው የተማሪዎች ማርች ባንድ

  የሙያው ፍቅር ያደረባቸው ገና በልጅነታቸው ነው፡፡ በ1970ዎቹ መጀመርያ፣ ለቀለም...

  በስንደዶና ሰበዝ የተቃኘው ጥበብ

  በአንዋር አባቢ ተወልዳ ያደገችው መሀል አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው፡፡...

  አዲስ ጥረት የሚጠይቀው  ኤችአይቪ  ኤድስን  የመግታት  ንቅናቄ

  ‹‹ኤችአይቪ በመላው ዓለም  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃ ዋነኛ የሕዝብ...

  የኅትመት ብርሃን ያየው ‹‹የቃቄ ወርድዎት›› ቴአትር

  ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ይታይ...