Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የገበያ ሥርዓት አብዮት ያስፈልገናል

ዓለም ቀውስ ላይ ነች፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ደሃ አገሮች ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚፈተኑበት ጊዜ ላይ ናቸው፡፡ የዓለማችን ታላላቅ ብለን የምንጠራቸው አገሮች ዓለምን በፈለጉት መንገድ ለመዘወር ያላቸውን ፍላጎት ዳር ለማድረስ ሲሉ፣ እንዲሁም ኪሳራቸውን ለማካካስ የሚወስዱት ዕርምጃዎች በደሃ አገሮች ሀብትና ትከሻ ላይ ይሆናል ተብሎ ስለሚታሰብ ፍዳችን ሊበዛ ይችላል፡፡

ዛሬ በሩሲያና በዩክሬን መካከል ከተከፈተው ጦርነት ጀርባ እነዚህ አገሮች የሚወስዷቸው ዕርምጃዎች እነርሱንም እየፈተነ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በየአገሮቻቸው የታየው የዋጋ ንረት ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡

ጦርነቱ ከቀጠለ ከዚህም የከፋ ይሆናል፡፡ እንዲህ ያለው ችግር ደግሞ ደሃ አገሮችን የበለጠ ይደፍቃቸዋል፡፡ ይህ ጦርነት በእርግጥም ጣጣው ብዙ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀውስ ውስጥ የገባው የዓለም ኢኮኖሚ ከአሠርት ዓመታት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የዋጋ ንረትን እያስተናገደ ነው፡፡

ወትሮም በዋጋ ንረት እየተናጠች ያለችውን ኢትዮጵያና መሰሎቿን ችግርም ያባብሳል፡፡ ያልተረጋጋው ፖለቲካ ሲታከልበት ደግሞ ‹‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ›› እንደሚባለው ይሆናል፡፡ አሁን እያማረረን ያለውን የዋጋ ንረት መወጣት ባልቻልንበት ሁኔታ ወቅታዊው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ይዞብን የሚመጣው የዋጋ ንረት በዘዴ ካልተያዘ ደግሞ ችግራችንን ዕጥፍ ድርብ ያደርገዋል፡፡

በተለይ በዓመት ከ18 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆን ዕቃ ከውጭ በማስገባት የምትታወቀዋ አገር፣ ወቅታዊው ሁኔታ በሚፈጥረው ዓለም አቀፋዊ የዋጋ ንረት ሳቢያ የሚፈጠረው የዋጋ ንረት ያስጎነብሳታል፡፡

ወትሮም ፍፁም ምክንያታዊ ባልሆነ ሁኔታ ወደ ላይ የተሰቀለው የምርትና ሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ የአሁኑ ክስተት ሰበብ ሆኖ ተደርቦበት ሲመጣ የኢትዮጵን ገበያ የበለጠ የሚረብሸው መሆኑ ታውቆ፣ ከወዲሁ መዘጋጀት የግድ ማለቱ ብቻ ሳይሆን፣ አሁን ከመቼውም ጊዜ በላይ የምንፈተንበት ወቅት በመሆኑ ይህንን ቀውስ ለመቀነስ ያለ የሌለ አቅምን መጠቀም ግድ ይላል፡፡

በሥነ ልቦና ደረጃ ከመዘጋጀት ጀምሮ ቢያንስ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን በአግባቡ ኅብረተሰቡ ሊያገኝ የሚችልበትን አሠራር መዘርጋት የግብይት ሥርዓቱን ከልብ ሆኖ ማስተካከል ያሻል፡፡ እንደ ከዚህ ቀደሙ በተልፈሰፈሰና በተዝረከረከ አሠራር ሳይሆን ቆምጨጭ ማለትም ይጠይቃል፡፡

እንደቀልድ አምስት ሌትር ዘይት 1,000 ብር ገባ የተባለበት ምክንያት ዋጋው ወቅቱ የፈጠረው ዓለም አቀፋዊ የዋጋ ንረት ብቻ ሳይሆን፣ የዘይት ገበያንም ሆነ ሌሎች መሠረታዊ ምርቶችን በአግባቡ ለተጠቃሚ ለማድረስ ካለብን የከረመ ችግር ጋር የተያያዘ መሆኑን መርሳት የለብንም፡፡

ስግብግብነትም ሌላው ምክንያት ነው፡፡ ሕዝብ በዋጋ ንረት እየተንገላታና እየተማረረ ነው፡፡ መንግሥት በሕዝብ ገንዘብ በውጭ ምንዛሪ የሚገባ የምግብ ዘይት አሁን ያለበትን ዋጋ ተገንዝቦ ቆራጥ ውሳኔ ካልተወሰነ ገበያውን ለማረጋጋት ከልብ ካልተሠራ፣ ከዛሬው ይልቅ የነገው የዋጋ ንረት የበለጠ ይጎዳናል፡፡

በተለይ ያላግባብ አሁን የተደረገው የዋጋ ጭማሪን መሠረት አድርጎ ዋጋ የሚያሠላ ከሆነ ደግሞ አደጋው ከፍ ስለሚል በመጀመርያ አሁን ያለውን ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ወደ ቦታው መመለስ አለበት፡፡   

የምግብ ዘይት እንደ ቅንጦት ዕቃ ወደመሆን ደረጃ ከደረሰ፣ በቃ ከዚህ በኋላ ግብይቱ በተለየ መንገድ እንዲከናወን ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ እስካሁን ያለው የዋጋ ንረት በወቅቱ ማስታመምና መፍትሔ ያልሰጠነው ሆኖ ሳለ፣ አሁን በተጨባጭ ንረቱን የሚያባብስ ሁኔታ በተፈጠረበት በዚህ ወቅት የመንግሥት ቀዳሚ አጀንዳ ሊሆን የሚገባው የማያዳግም ዕርምጃ መውሰድ ላይ ነው፡፡

የእስካሁኑን የዋጋ ንረት እየተለሳለሰም ቢሆን የቻለው ሸማች፣ ከዚህ በኋላ ሊሆን ይችላል ተብሎ የሚጠበቀውን ተጨማሪ የዋጋ ንረት ለመሸከም የሚችልበት ትከሻ ስለሌለው ጉዳዩን ቀዳሚ አጀንዳ ማድረግ ግድ ይላል፡፡

አሁን አጠቃላይ የግብይት ሥርዓቱ አብዮት የሚያስፈልገው የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ግልጽ የሆነ አሠራር እንዲኖረው የሚያስፈልግ ከመሆኑም በላይ፣ ንግድ እንደተፈለገ ትርፍ የሚዛቅበት ያለመሆኑን ማሳየት ያስፈልጋል፡፡

ቢያንስ ይህንን ወቅት ለማለፍና ለወደፊቱም ቢሆን ሊጠቅም ስለሚችል በተለይ ከውጭ የሚመጡ ምርቶች አጠቃላይ ወጪያቸው ተሠልቶ የትርፍ ምጣኔያቸው እንዲገደብ የሚያደርግ ግልጽ ፖሊሲ ማስቀመጥ አስገዳጅ መሆን አለበት፡፡

ሌሎች መፍትሔ የሚሆኑ ሐሳቦች ከመንግሥት ብቻ የሚጠበቁ ባለመሆኑ የተሻለ የሚባል መፍትሔ የሚሆን ሐሳብ ከሁሉም ኅብረተሰብ ያስፈልጋል፡፡ በተለይም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደ ዜጋ ‹‹ይኼ ቢሆን ይሻላል›› የሚለው ሐሳባቸውን በማቅረብ አገርን መታደግ ይኖርባቸዋል፡፡

መንግሥት ያላየውን ማሳየት የሁላችንም ኃላፊነት በመሆኑ፣ በተለይ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች መፍትሔ የሚሆን ሐሳብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ከፊታችን ያለውን ችግር ለመወጣት አሁንም በአፅንኦት መገለጽ ያለበት መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች በእጅጉ ደግሞ የምግብ ሰብሎችን በማምረት ራሳችንን ለመመገብ ያለንን ጉልበት ሁሉ አሟጠን መጠቀም ላይ ጊዜ መስጠት እንዳለብን ነው፡፡ ዘለዓለም ስንዴና የምግብ ዘይት እየገዛን መዝለቅ የማንችል ብቻ ሳይሆን፣ እስካሁን እንደሚደረገው እንኳን ገበያን ለማረጋጋት የሚደረጉ ግዥዎችን ለመፈጸም የሚቻልበት አቅም ስለማይኖር በዚህ ጉዳይ ላይ አሁን ከሚደረገው በላይ መታሰብ አለበት፡፡

የህዳሴ ግድብን ለመሥራት ያሳየነውን ተነሳሽነት፣ በግብርናው ዘርፍም መድገም ይኖርብናል፡፡ እስካሁን ያደረግናቸው የተበጣጠሱ ሙከራዎች የትም የማያደርሱ ሆነው የዋጋ ንረቱንም ሊያክሙልን ስላልቻሉ መንግሥት የታላላቅ እርሻዎች ፕሮጀክቶች በመቅረፅና ሕዝባዊ ተሳትፎ በማድረግ ዘለዓለም ከመራብና በዋጋ ንረት ከመዠለጥ እንድንወጣ መሥራቱ የግድ ነው፡፡

ልክ እንደ ህዳሴ ግድብ በእርሻው ዘርፍ ትልቅ ፕሮጀክት ለመተግበር የማንችልበት ምክንያት ስለሌለ በዓባይ ላይ ያሳየነውን ድፍረት መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶችን በማምረት መድገም አለብን፡፡ አሁን ያለንበትን ችግር ለመወጣት የመጨረሻ አማራጫችን ተደርገው ከሚወሰዱ ሥራዎች መካከልም ሊሆን ይገባል፡፡

ይህ ዕርምጃ እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የሚያሳትፍ ሆኖ፣ አትራፊ ሆኖ እንዲሠራ ማድረግ ይቻላልና ራሳችንን ለመመገብ የሚያስችለን እንደ ህዳሴ ያለ አንድ ትልቅ ፕሮጀክት ይቀርፅ፣ ሰፋፊ ፆም የሚድሩ መሬቶቻችንን እንጠቀምባቸው፡፡

ከመመፅወትና ዘለዓለም ከመራብ ሊያላቅቁን የሚችሉ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ካለብንም ይህንኑ ለማድረግ ክፍት የሆነ አሠራር መዘርጋት አለበት፡፡ ለማንኛውም አሁን ያለው የዓለም ሁኔታ ከፊታችን የሚጠብቁን ብዙ ሥራዎች መኖራቸውን የሚያመለክት በመሆኑ፣ ዜጎች ይህንን ታሳቢ ያደረገ የሥነ ልቦና ዝግጅት ማድረግና ግልጽ የሆነ የግብይት ሥርዓት መፍጠር የግድ ስለመሆኑ ድጋሚ ማስታወሱ ተገቢ ነው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት