Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአፍሪካ ሕዝብ መናፈሻ እስከምን?

የአፍሪካ ሕዝብ መናፈሻ እስከምን?

ቀን:

ለቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ለአሁኑ አፍሪካ ኅብረት መመሥረት በግንባር ቀደምነት የሚጠቀሱትን ቀዳማዊ ኃይለ ሥሳሌ፣ የኬንያ ፕሬዚዳንት ጆሞ ኬንያታና የጋና ፕሬዚዳንት ክዋሜ ንክሩማህን ጨምሮ 30 የድርጅቱ መሥራች አባል አገሮች መሪዎች በ1955 ዓ.ም. በወርኃ ግንቦት ነበር ችግኝ በመትከል አሻራቸውን ያሳረፉበት፡፡

 በታላቁ ቤተ መንግሥት፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት፣ በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽንና በሒልተን አዲስ አበባ ተከቦ በ45,707 ስኩዌር ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው ይህ መናፈሻ፣ የወቅቱ አፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት ቀድሞ በሥፍራው በነበሩ ዛፎች ላይ የቴሌቪዥን ስክሪኖች ተደርገው ሕዝቡ  ሒደቱን በቀጥታ የተከታተለበት መሆኑንም በወቅቱ በሥፍራው የነበሩት የአሁኑ አንጋፋ ጋዜጠኛ አቶ ታደሰ ገብረ ማርያም ያስታውሳሉ፡፡

በደርግ ዘመን በ1977 ዓ.ም. የተተከለውና ኢሕአዴግ አዲስ አበባ በ1983 ዓ.ም. ከመግባቱ በፊት ሕዝብ ያፈራረሰው የሌኒን መታሰቢያ ሐውልትም ለብሔራዊ ቤተ መንግሥት በሚቀርበውና ቀድሞ ሌኒን አደባባይ በሚባለው የመናፈሻው ሥፍራ የተተከለበት ነበር፡፡

የአዲስ አበባ 100ኛ ዓመት ሲከበር በታላቁ ቤተ መንግሥት አቅጣጫ ያለው ሥፍራ ትንሽ ዕድሳት ተደርጎለት የነበረ ቢሆንም፣ በዘመናት ሒደት የጎላ እንብካቤ ሳይደረግለት እንዲሁ ነዋሪዎች አረፍ ይሉበት የነበረው ይህ ሥፍራ፣ ቀን የወጣለትና አምሮ የተሠራው 2000 ዓ.ም. መጀመርያ አካባቢ ሚድሮክ ኢትዮጵያ ባደረገው የ13.5 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ነበር፡፡

የአፍሪካ ሕዝብ መናፈሻ እስከምን?

 

ኩባንያው ለልጆች መጫወቻ የሚሆኑ ዥዋዥዌ፣ ከፕላስቲክ የተሠሩ መንሸራተቻዎችና የመጫወቻ ቤቶች በውስጡ ከማስቀመጡ በተጨማሪ ሥፍራው ዓይነ ግቡና አረንጓዴ እንዲሆን አድርጓል፡፡ የካፌና የሬስቶራንት አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ ቤቶችንም ገንብቷል፡፡  

የመናፈሻና መዝናኛ ቅርፅ የተላበሰው ይህ መናፈሻ እንደተከፈተ ብዙዎች ልጆቻቸውን ለማዝናናት ይሄዱበትም ነበር፡፡ ነገር ግን ዓመታት እንኳን ሳያገለግል አገልግሎቱን አቋርጧል፡፡

‹‹የአፍሪካ ሕዝብ መናፈሻ›› በመባል ደግሞ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ዳያስፖራው የገና በዓልን አስመልክቶ ወደ አገሩ እንዲገባ በኅዳር በ2014 ዓ.ም. ጥሪ ማቅረባቸውን ተከትሎ ነው፡፡ አገልግሎት እንዲሰጡና በመብራቶች እንዲዋብ ከተደረጉ ሥፍራዎች አንዱ የሆነው ይህ መናፈሻ፣ ዳያስፖራው ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት በነበረባቸው ከገና ዋዜማ እስከ ጥምቀት ማብቂያ ባሉት ቀናት በመብራት ተውቦና የተለያዩ ቀለማት ባላቸው የውኃ ፏፏቴዎች (ፋውንቴን) ደምቆም ከርሟል፡፡

ይሁን እንጂ መናፈሻው ለአዲስ አበባ መሀል ከሚባሉ ሠፈሮች ከመገኘቱ፣ ተደራሽ ከመሆኑና በአፍሪካ ሕዝብ ስም ከመሰየሙ አንፃር የሚመጥን አገልግሎት እየሰጠ አይደለም፡፡

በመናፈሻው ልጆቻቸውን ይዘው ከመጡ ወላጆች መካከል ልጆቻቸው የሚጫወቱበትና ቀልባቸውን የሚስብ ነገር ባለመኖሩ ‹‹ለመዝናናት መንገላታት›› ሲሉ  ሁኔታውን የገለጹልንን እናት አናግረናል፡፡

ዕለቱ ቅዳሜ የካቲት 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ነው፡፡ እኚህ እናት ልጆቻቸው የመጀመርያ መንፈቅ ዓመት አጋማሽ ትምህርት ስለጨረሱ ለማዝናናት ብለው ነበር የመጡት፡፡ የገና ሰሞን አካባቢ በሥፍራው ሲያልፉ ያስደመማቸውን ፏፏቴና በውስጡም ብዙ መጫወቻ ሊኖር ይችላል የሚለውን ግምታቸውን ይዘው ከሥፍራው ቢገኙም እንዳሰቡት አልሆነም፡፡

‹‹አዲስ አበባ›› በመባል የሚጠራው ሥፍራ ለሕፃናት ሊሆን የሚችል ሦስት ዥዋዥዌ፣ አቧራ የጠገቡ የፕላስቲክ መጫወቻዎችና የካፌ አገልግሎት ከሚሰጠው ዋው በርገር በስተቀር ሌላ አገልግሎት የለውም፡፡

ወደ መናፈሻው ለመግባት ከአሥር ዓመት በታች ያሉ ልጆች የማይከፍሉ መሆኑንና ከዚያ በላይ ላሉት 100 ብር በመክፈል እንደሚገባ፣ በዚህ ብር የአፍሪካ ሕዝብ መናፈሻ አጠቃሎ የያዛቸውን አዲስ አበባና ኢትዮጵያ የተባሉትን የመናፈሻው ክፍሎች መጎብኘት እንደሚቻል መረጃ እንዳላቸው የገለጹት እኚህ እናት፣ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሠረት መሪዎች ዛፍ በተከሉባቸው ሥፍራዎች ያለውን ሥፍራ ጨምሮ በአዲስ አበባም ሆነ በኢትዮጵያ ስም ከተሰየሙት ሥፍራዎች እንደጓጉለት አገልግሎት እንዳላገኙ ነግረውናል፡፡

የአፍሪካ መሪዎች ዛፍ የተከሉበት ሥፍራ ከላይ ካሉት ከሁለቱ የመናፈሻው ክፍሎች  የተሻለ ቢሆንም፣ የሚሰጠው አገልግሎት ግን ይቀረዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ›› በሚል በሚጠራው ክፍል ያሉት በጣት የሚቆጠሩ መጫወቻዎች ፀሐይ ቀጥታ የሚያርፍባቸውና የሚግሉ በመሆኑ ለልጆች ጨዋታ አመቺ አይደሉም፡፡  መናፈሻው ሁሉንም የዕድሜ ክልል ያማከለ አገልግሎት እየሰጠም አይደለም፡፡

መጫወቻዎቹ ሕፃናትን ብቻ መሠረት ያደረጉ በመሆናቸው በታዳጊ ወጣትነት ዕድሜ ላይ ሆነው ከወላጆቻቸው ጋር የመጡ ልጆች ሲሰላቹ ተመልክተናል፡፡ ለዕድሜያቸው የሚመጥን ንባብን ጨምሮ ሌሎች መዝናኛዎች የሉም፡፡ መናፈሻው በአጠቃላይ እንደ ስሙ አገልግሎት እየሰጠም አይደለም፡፡

ዳያስፖራው በመጣ ሰሞን ደምቆ ይታይ የነበረው ይኸው መናፈሻ፣ አሁን ላይ በሰንበት ቀናት እንኳን ፏፏቴው ሲለቀቅ አይስተዋልም፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ፣ ‹‹መናፈሻው የሕፃናት መጫዎቻዎች፣ ካፌ፣ የተለያዩ ልብን የሚያርዱ ቀለማማ ፋውንቴኖች፣ ሰው ሠራሽ ወንዞች፣ ልዩ ልዩ የመዝናኛ አረንጓዴ ቦታዎችና ሌሎችንም አገልግሎቶች በውስጡ አካቶ ልጆች ልደታቸውን፣ ወጣቶች ሠርጋቸውን በልዩ ሁኔታ የሚያከብሩበት በከተማችን ውስጥ ካሉ የሕዝብ መናፈሻዎች ከፊት ተርታ የሚጠቀስ ሆኗል፤›› ብሎ በገለጸው ልክ መናፈሻውን ማግኘት አይቻልም፡፡

ይህንን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገርናቸው የአስተዳደሩ የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ አደባባይ ሰንደቅ እንደገለጹት፣ በውስጡ የአዲስ አበባና የኢትዮጵያ የሚሉ መናፈሻዎችን አጠቃሎ የያዘው የአፍሪካ  የሕዝብ መናፈሻ ሲመሠረት ያካተታቸው ነገሮች ቢኖሩም፣ ስሙንና ይዘቱን ባሟላ መልኩ አገልግሎት እየሰጠ ባለመሆኑ ይህንን ለማስቻል በቀጣይ የሚሠሩ ሥራዎች አሉ፡፡

እንደ አቶ አደባባይ፣ በሚድሮክ ኢትዮጵያ በዘመናዊ መልኩ ከተገነባ በኋላ ለጥቂት ዓመታት አገልግሎት ሰጥቶ በመቋረጡ በውስጡ የነበሩ ፏፏቴዎችን ጨምሮ የተለያዩ ቁሶች ተበላሽተው ነበር፡፡ በመሆኑም በ2014 ዓ.ም. የተበላሹትን የማስተካከል፣ የማዘመን፣ አጥሩን የማጠር፣ በፓርኩ ውስጥ የነበሩ አረንጓዴ ቦታዎችን የማዘመን፣ በአበባዎች ገጽታውን ውብ የማድረግ፣ ቀድሞ የተተከሉ አገር በቀል ጥላማ ዛፎች እያረጁ ስለሆኑ እነሱን የሚተኩ ዛፎች የመትከልና ሌሎችም ዕድሳቶች ተከናውነዋል፡፡ መናፈሻው ተዘግቶ በመክረሙ በብልሽት ምክንያት አገልግሎት የማይሰጡ ቁሶችን የመተካትና የማሳመር ሥራም እንዲሁ፡፡  

ነገር ግን ሪፖርተር በቅርቡ በሦስት ግቢ ተከፋፍሎ የሚገኘውን የአፍሪካ ሕዝብ መናፈሻ እንደቃኘው፣ መናፈሻው እንደ ስሙ ያህል አገልግሎት እየሰጠ አይደለም፡፡

ፋውንቴኖች ቅዳሜና እሑድ እንኳን አይከፈቱም፡፡ በቂ መጫወቻና መዝናኛ እንዲሁም ሁሉንም ያማከለ አገልግሎት የለም፡፡ ሥፍራው አነስተኛ ቤተ መጻሕፍት፣ ስለ አፍሪካ መሪዎች የተጻፉ መረጃዎችና ሌሎች የአፍሪካ ባህልና እሴት የሚገልጹ መጻሕፍት ቢኖሩበትና መናፈሻውን ከስሙ ጋር ለማስተሳሰር ቢሠራ መልካም ቢሆንም ይህ አሁን ላይ የለም፡፡

አቶ አደባባይ እንደሚሉትም፣ የአፍሪካ ሕዝብ መናፈሻ ተነሳ እንጂ በከተማዋ ያሉ አብዛኛዎቹ መናፈሻዎች በቂ አገልግሎት እየሰጡ አይደለም፡፡ የሕዝብ መናፈሻዎች አረንጓዴ ከመሆናቸውና ውስን መርሐ ግብሮች ከመስጠታቸው ባሻገር ‹‹የሕዝብ መናፈሻ ናቸው›› ብሎ ለመናገር አያስደፍርም፡፡ ሁሉንም የዕድሜ ክልልና ፆታ የሚያማክል አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎም አይታሰብም፡፡

የአፍሪካ የሕዝብ መናፈሻ ቦታ ከብሔራዊ ቤተ መንግሥት አካባቢ እንደመኖሩ የተጀመሩ ሥራዎች ቢኖሩም፣ በቂ ናቸው ለማለት ስለማያስደፍር በቀጣይ ስሙን የሚመጥን አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል በዕቅድ የተያዙ ሥራዎች አሉ፡፡

የተለያዩ የአፍሪካ አገሮችን ባህላዊ ምግቦች የማቅረብ አገልግሎት የሚሰጥበት፣ ባህላዊ የሙዚቃ ዝግጅት የሚካሄድበት፣ የተለያዩ የማንበቢያ ማዕዘናት፣ ነፃ ዋይፋይና ሌሎች አገልግሎቶችን በውስጡ ለማካተት በዕቅድ ተይዞ የተሻለ የሕዝብ መናፈሻ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡

ሌሎች የሕዝብ መናፈሻዎችንም ከበፊቱ በተለየ መልኩ ለመሥራት መታቀዱን፣ የአምባሳደር ፓርክ ጥቂት የሚቀሩት ነገሮች ቢኖሩም፣ የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ተደርጎ መሠራቱን አስታውሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...