Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህል‹‹የኢትዮጵያ ሙዚቃ የራሱ ቀለም ያለውና ለሌሎች አገሮች የሙዚቃ ባለሙያዎች የማይታይ ነው›› ...

‹‹የኢትዮጵያ ሙዚቃ የራሱ ቀለም ያለውና ለሌሎች አገሮች የሙዚቃ ባለሙያዎች የማይታይ ነው›› የኢትዮ ጃዝ አርቲስት ዳዊት ፍሬው ኃይሉ

ቀን:

ዳዊት ፍሬው ኃይሉ የኢትዮ ጃዝ አርቲስት፣ የበኩር ድምፃዊና ሙዚቀኛ ፍሬው ኃይሉ ልጅ ነው፡፡ ነፍስ ኄር ፍሬው 1940ዎቹ  መጨረሻ ጀምሮ ዝነኛ ከሆኑ ድምፃውያንና የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች መካከል ይጠቀሳል፡፡ ‹‹ልጅም እንደ አባት››እንዲሉ የአባቱን ፈለግ የተከተለው ዳዊት ፍሬው ወደ ሙዚቃው የተሳበው በለጋ ዕድሜው ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ   በኋላ ያቀናው ወደ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ሲሆን፣ በዚያው በዋና ትምህርት (ሜጀር) ክላርኔት፣ በንዑስ ትምህርት (ማይነር) ፒያኖ እና ማሲንቆን በማጥናት ተመርቋል፡፡ በሥራ ዓለም ከተሰማራ በኋላ የመጀመሪያው ቤቱ ለአሥር ዓመታት ያህል ያገለገለበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ነው፡፡ በጣይቱ ሆቴል የጃዝ ሙዚቃን ያቀርቡ በነበሩት አዲስ አኩስቲክ ስብስብ ውስጥም ከመጀመሪያው ረድፍ ከሚቆመጡት ውስጥ ይገኝበታል፡፡ ዳዊት አራት አልበሞችን ያወጣ ሲሆን የመጨረሻው ሥራው በሙዚቃ መሣሪያ የተቀነባበረው ‹‹የኢትዮጵያዊነት አሻራ›› አልበምን ለታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብና የዓድዋ ድል በዓል መታሰቢያ አድርጎታል፡፡ የሙዚቃ ሕይወቱን አስመልክቶ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሮታል፡፡  

ሪፖርተር፡- አንተን በሙያህ ኢትዮ ጃዝ አርቲስት እያሉ ይጠሩሃል ምን ማለት ነው?

አርቲስት ዳዊት፡- በአጋጣሚ ሆኖ ኢትዮ ጃዝ የሚል ስያሜ ያለው አዲስ አኩስቲክ የሚል ግሩፕ በወቅቱ ተፈጥሮ ነበረ፡፡ ግሩፑም የ1950ዎቹ እና 60ዎቹ የኢትዮጵያ ወርቃማ ዘመን የሚባሉት ዜማዎችን በጃዝ አሬንጅመንት አሬንጅ ለማድረግ ከግሩፑ ጋር ልንጫወት ችለናል፡፡ ይህንንም ከነሔኖክ ተመስገንና ከሌሎቹ አርቲስቶች ጋር እንጫወት ነበር፡፡ በዚያ የተነሳ እንጂ የሙዚቃ ትምህርቴን የጨረስኩት የክላሲካል የሙዚቃ ትምህርት ነው፡፡ በእርግጥ ከዚህ ግሩፕ ጋር የጃዝ ሙዚቃን ልጫወት እንጂ ትክክለኛ የሙዚቃ መንገዴ ጃዝ ነው ብዬ መናገር ትንሽ ይከብደኛል፡፡

- Advertisement -

ሪፖርተር፡- ወደ ሙዚቃ ለመግባት ያነሳሳህ ምንድነው? ከመቼ ጀምሮ ወደ ሙያው ገባህ?

አርቲስት ዳዊት፡- የእኛ ቤተሰብ በአጠቃላይ የሙዚቃ ቤተሰብ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ የመጀመርያ ከምንላቸው የሙዚቃ አርቲስቶች መሐል የእኔ አባት የመጀመርያው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከልጅነቴም ጀምሮ የአባቴን ሙያ ስለምወደው ወደ ዘርፉ በቀላሉ ልቀላቀል ችያለሁ፡፡ አባቴም የሙዚቃ ሥራዎቹን በሚሠራበት ወቅት እያየሁ ማደጌና ሙያው በከፍተኛ ደረጃ ውስጤ ሠርፆ በመግባቱ ምክንያት የዘርፉ ተዋናይ እንድሆን ረድቶኛል ብዬ አምናለሁ፡፡ ትምህርቴንም እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ካጠናቀቅኩ በኋላ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ልገባ ችያለሁ፡፡ ትምህርት ቤትም ከገባሁ በኋላ ክላርሌትን መጫወት ትችላለህ የሚል ነገር ስሰማ ክላርሌትን ምርጫ አድርጌአለሁ፡፡ በወቅቱም ፈለቀ ኃይሉ ክላርሌትን እንደሚያስተምረኝ ቃል ገባልኝ፡፡ የሙዚቃ ትምህርት ቤትም የገባሁት በ1987 ዓ.ም. ሲሆን ሜጀር ያደረግኩት ክላርኔት ነው፡፡ ማይኔሬ ደግሞ ሁሉም ተማሪ እንደሚማረው ፒያኖ ነበረ፡፡ የሙዚቃ ትምህርቴን በአግባቡ በመማርና ዕውቀቴን በማዳበር በ1989 ዓ.ም. ላይ ልመረቅ ችያለሁ፡፡ ትምህርት ቤት ከመግባቴ በፊትም ከልጅነቴ ጀምሮ ክራር እጫወት ነበር፡፡ ወደ ሙዚቃም እንድመጣ ያደረገኝ ዋናው ነገር የአባቴ የኪነ ጥበብ ውጤት ነው ብዬ በሙሉ ልቤ ለመናገር እችላለሁ፡፡ አባቴም በ1950ዎቹ ስመጥር ከሚባሉ ሙዚቀኞች መካከል ስለነበር ሙያውን በጥልቀት እንድወድ አስተዋጽኦ አበርክቶልኛል እላለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በሙዚቀኛነትም ሆነ በድምፃዊነት ትታወቃለህ፡፡ አንተ ለየትኛው ቅድሚያ ትሰጣለህ?

አርቲስት ዳዊት፡- ለእኔ በሙዚቃ መሣሪያ መጫወቴን ቅድሚያ እሰጣለሁ፡፡ ነገር ግን በድምፃዊነት የተጫወትኳቸውን ሥራዎቼንም እወዳቸዋለሁ፡፡ በእርግጥ አብዛኛዎቹ ሥራዎቼ በሙዚቃ መሣሪያ የተጫወትኳቸው ናቸው፡፡ በዚህም የተነሳ አራት ሲዲዎችን ለአድማጭ ጆሮ ማድረስ ችያለሁ፡፡ አልበሞቼን በየቦታው ሲሰሙ ሥራዎቼ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆኑ ያስታውሰኛል፡፡ ከሥራዎቼ መካከልም ፍሬው፣ ጥላ ከለላዬ፣ ኢትዮጵያዊቷ፣ የዳዊት ፍሬው ክላርኔት፣ ለታላቁ ህዳሴ ግድብና ለዓድዋ ድል መታሰቢያነት ያደረስኩት ‹‹ዓባይ ልብ ገዛ የኢትዮጵያዊነት አሻራ›› ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ አልበሞች የተለያዩ ቁም ነገር አዘል መልዕክቶችን የያዙ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ለየት የምትለው ሙዚቃን በልምድ ብቻ ሳይሆን በትምህርት መታጀቡ ነው፡፡ የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ቆይታህ እንዴት ነበር?

አርቲስት ዳዊት፡- የያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ቆይታዬ የተሳካ ነው ብዬ በሙሉ ልቤ መናገር እችላለሁ፡፡ በተለይ ደግሞ ክላርኔትን ሜጀር ያደረግኩት እዚያ መሆኑ የተሳካ ያደርገዋል፡፡ በአጋጣሚም ሆኖ የገጠመኝ አስተማሪዬ ፈለቀ ኃይሉ ጥሩ ሙዚቀኛ በመሆኑ በቂ የሆነ ልምድ እንድቀስም ረድቶኛል፡፡ ክላርኔትም በመጫወት በተለያዩ ኮንሰርቶች ላይ ማቅረብ ችያለሁ፡፡ አርቲስት ፈለቀም ክላርኬትን በአግባቡ እንድማር ስለረዳኝ ውጤታማ ልሆን ችያለሁ፡፡ የሙዚቃ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎች ትምህርት ቤት እያሉ ሙዚቃዎችን ቢጫወቱ ተተኪ ትውልዶችን መፍጠር ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ሙዚቃም የራሱ የሆነ ቀለም ያለውና ለሌሎች አገሮች የሙዚቃ ባለሙያዎች የማይታይ ነው ብዬ ደፍሬ መናገር እችላለሁ፡፡ ይኼንንም ስንቶቻችን በአግባቡ ተጠቅመናል የሚለው ለራሴ ጥያቄ ፈጥሮብኛል፡፡ በወቅቱም አምባሰልን፣ ትዝታን ስጫወት የበፊቱ የሙዚቃ አርቲስቶችን እንዳስታውስ ያደርጋል፡፡ ይኼም ለእኔ ልዩ ቦታ ይሰጠኛል፡፡ የሙዚቃ ትምህርት ቤቱ ወደፊት ለኢትዮጵያ ዜማዎችና ለሙዚቃ ጥናቶች ጊዜ መስጠት ይኖርበታል ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖም የአንደኛውንም ሆነ የሁለተኛውን የሙዚቃ ቅንብሮቼን የሠራልኝ አርቲስት ፈለቀ ኃይሉ ነው፡፡ የፈለቀ ኃይሉ መኖር ለእኔ ከክላርኔት የሙዚቃ ስታይል ጋር ለመጓዝ ትልቅ ጉልበት ሆኖኛል፡፡

ሪፖርተር፡- በብሔራዊ ቴአትር የነበረህ ቆይታህ እንዴት ትገልጸዋለህ?

አርቲስት ዳዊት፡- በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አልቶ ሳክስፎን የተሰኘ የሙዚቃ ሥልት ነበር የምጫወተው፡፡ በሰዓቱም አብረውኝ ከነበሩ የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት ሙከራ አድርገናል፡፡ ዜማ ባንድ፣ ሙዚቃዊ ድራማም ለመሥራት ችለናል፡፡ ነገር ግን በወቅቱ ስሜትን የሚነኩ ነገሮችን በማየቴ ብሔራዊ ቴአትር መሥራት ለማቆም ተገድጃለሁ፡፡ እንደዚህ ዓይነት ነገሮችንም ሙያህን እንድትጠላና ከዘርፉ እንድትወጣ ስለሚያደርጉ መተውን አማራጭ አድርጌያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- በብዙ ባንዶች ተጫውተሃል፡፡ በተለይ የሚጠቀሰው አዲስ አኩስቴክ ሬኔሳንስ ግሩፕ ፕሮጀክት ነው፡፡ ስኬቱን እንዴት ትገልጸዋለ?

አርቲስት ዳዊት፡- አዲስ አኩስቲክ ሬኔሳንስ የ1950ዎቹ እና 60ዎቹን የኢትዮጵያ ዜማዎች መነሻ በማድረግ አሬንጅመንታቸውን ወደ ጃዝ አሬንጅመንት በመቀየር ከሥራ ባልደረባዎቼ ጋር መጫወት ችያለሁ፡፡ በጣይቱ ሆቴልና በአሊዜ ክለብም በምንጫወትበት ጊዜ በጣም ብዙ ተመልካች ነበሩ፡፡ በወቅቱም ማኅበረሰቡ ለቀድሞ ሙዚቃዎች ያለው አመለካከት ከፍተኛ ስለነበር በጊዜ አዳራሾች ይሞሉ ነበር፡፡ በእነዚህ ወቅት የነበሩ ዜማዎችን በጃዝ አሬንጅመንት ተሠርተው የሰውን ቀልብ እንዲስቡ ማድረጋችን ጉዟችን ላይ መነቃቃትን ሊፈጥርልን ችሏል፡፡ በዚህም ወቅት ነፍሱን ይማረውና አርቲስት አየለ ማሞ፣ ሔኖክ ተመስገንና ሌሎች ባለሙያዎች ስለነበሩ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነትን አግኝቷል፡፡ ከግሩፑ ጋርም ዘመን የሚሻገር ትውስታ የሚል አልበም መሥራት ችለናል፡፡ ይኼም ለብዙዎች አርቲስቶች ትልቅ ትዝታን ፈጥሯል፡፡

ሪፖርተር፡- በትውስታ አልበምህ ያንተ የክላርኔት ዕውቀት ልዩ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ እሱን ብታብራራልን?

አርቲስት ዳዊት፡- በእርግጥ እኔ እንደዚህ ይሆናል ብዬ አይደለም የተጫወትኩት፡፡ ነገር ግን ዜማዎቹ እንደ ኢትዮጵያ አድርጌ መጫወቴ ብዙ የውጭ አገር ሚዲያዎች የጻፏቸው አስተያየቶች ለእኔ ግርምትን ፈጥሮብኛል፡፡ አስተያየታቸውም ክላርኔትን አውቄ በደንብ አድርጌ መጫወቴን የሚጠቁሙና የኢትዮጵያን የሙዚቃ እውነተኛ ዓለም የሚያንፀባርቅ ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ ይኼም ለእኔ ትልቅ መነቃቃትን ፈጥሮልኛል፡፡ ወደፊትም የአገርን ህልውና የሚያስጠሩ ሥራዎች በደንብ እንድሠራ ረድቶኛል፡፡ ለዚህም ክብር ምሥጋና ለፈጣሪዬ ይሁን በርካታ ሥራዎችን እንድሠራ ረድቶኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ከውጭ አገር ሙዚቀኞች ጋር የመጫወት ዕድል አግኝተሃል፡፡ ምን  ቀስመሀል?

አርቲስት ዳዊት፡- እንዳልከው ከውጭ አገር የሙዚቃ ባለሙያዎች ጋር የመጫወት ዕድሉን ማግኘት ችያለሁ፡፡ በተለይም ደግሞ አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ ከአንድም አሥር ጊዜ የኢትዮጵያ የሙዚቃ ፌስቲቫልን አዘጋጅቷል፡፡ በፌስቲቫሉም የልምድ ልውጦችንም እንድቀስም ረድተውኛል ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም የተለየ ምሥጋና ይገባቸዋል፡፡ ይኼ የሙዚቃ ፌስቲቫል የእኛ አገር የጥበብ አካላት እንዲያስቡበት ጭምር መንገድ ሰጥቷል፡፡ እስካሁን ባደረጋቸው ፌስቲቫሎች በዘርፉ የተሰማሩ የኢትዮጵያ ባለሙያዎች ከነሱ ጋር ለመሥራት እንኳን ሲሯሯጡ አይታዩም፡፡ ይኼም ዘርፉ ላይ ምን ያህል ችግር እንዳለ ያሳያል፡፡ ፌስቲቫሉ በተዘጋጀ በአንድ ወቅትም የክላርኔትን ጨዋታ የምትጫወተው የውጭ አገር ዜጋ መሐል ላይ ያለውን ቀለም ማምጣት ከብዷት፣ እኔ ገብቼ የሠራሁበትን ጊዜ አስታውሳለሁ፡፡ ይኼ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት የኢትዮጵያ የሙዚቃ ቀለም የተለየ በመሆኑ ነው፡፡ ከአፍሪካም ሆነ ከአውሮፓ ክላርኔት ተጫዋች ኢትዮጵያውያን ለየት የሚያደርገው የሙዚቃ ቀለሙ ነው፡፡ ይህንንም የሙዚቃ ቀለሞች በትክክለኛ መንገድ መሥራት ከተቻለ ብዙ የክላርኔት ተጫዋቾችን በኢትዮጵያ ማፍራት ይቻላል ብዩ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ስላወጣሃቸው አልበሞች ብትገልጽልኝ፤ የመጀመርያው ‹‹ፍሬው›› በታላቁ ሙዚቀኛውና ድምፃዊው አባትህ የሰየምከው ነው፡፡ ለአንተም ሆነ ለኢትዮጵያ ምን ማለት ነው?

አርቲስት ዳዊት፡- አብዛኛውን ጊዜ ሥራዎቼ በራሳቸው መናገር ይችላሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ የኢትዮጵያ ኪነ ጥበብም መነሻው ሀገር ፍቅር መሆኑ አገር ያወቀው፣ ፀሐይ የሞቀው ነው፡፡ በሀገር ፍቅርም ሲጀመር ከነበሩት ሰዎች መካከል ግንባር ቀደሙ ፍሬው ነው፡፡ ፍሬው በኢትዮጵያ ሙዚቃ ስም ያለው ‹‹ኢትዮጵያ ሀገሬ›› ሲል የኖረ ዘመናዊ ሙዚቃን በራሱ ጥረት ተምሮ ቆሞ የዘፈነ ሰው ነው፡፡ የመጀመርያው አልበሜ ፍሬው የተባለበት ምክንያት ‹‹ፍሬው ፍሬ›› ለማለት ተፈልጎ ነው፡፡ ሁለተኛው ‹‹ጥላ ከለላዬ›› የሚል መጠሪያ ያለው ሲሆን፣ መታሰቢያነቱ ለአርቲስት ጥላሁን ገሠሠ  ነው፡፡ ሦስተኛው ሲዲም ‹‹ኢትዮጵያቷ የዳዊት ፍሬው ክላርኔት›› የሚል ሲሆን ይህም ኢትዮጵያዊ ዜማዎችን የምትይዝ ለማለት የታሰበ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በሙዚቃ መሣሪያ ብቻ የተቀነባበረው አልበምህ ‹‹የኢትዮጰያዊነት አሻራ›› ለህዳሴ ግድብና ለዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚል ነው፡፡ ይኼንን መልዕክት እንዴት ልታስተላልፈው ቻልክ?

አርቲስት ዳዊት፡- የታላቁ ህዳሴ ግድብም ሆነ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የአገራችንን ገጽታ ማሳያ ናቸው፡፡ ሁለቱም የኢትዮጵያ አሻራ በመሆናቸው ከዚህ በላይ ሌላ ለመግለጽ አልችልም ብዬ መናገር እችላለሁ፡፡ በሲዲ ውስጥም የሁለቱን ዜማ በደንብ ማግኘት ይቻላል፡፡ በአንድ ወቅትም የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጽሕፈት ቤት ሲዲውን ሰምቶ ከምሥል ጋር እንድሠራ አድርጎኛል፡፡ ዛሬም ከሠራኋቸው ሲዲዎች በላይ ይኼ ሲዲ ለእኔ ለየት ያደርገዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...