በሙስና ወንጀል ተከሰው የነበሩት የሶማሌ ፕሪንቲንግ ፕሬስ ባለቤት አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ)ን ጨምሮ አራት ግለሰቦች፣ በፅኑ እስራትና በገንዘብ እንዲቀጡ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ የሙስና ወንጀሎች ችሎት መጋቢት 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ውሳኔ ሰጠ፡፡
ተከሳሾቹ ቅጣቱ የተወሰነባቸው ከክልሉ ተማሪዎች መጻሕፍት ኅትመት ጋር በተያያዘ ያላግባብ ፈጽመዋል በተባሉበት ከባድ የሙስና ወንጀል ነው፡፡ ተከሳሾቹ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1 ሀ እና ለ)፣33 እና የሙስና ወንጀል አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 13(1 እና ሐ (3)ን በመተላለፍ በቀረበባቸው በከባድ የሙስና ወንጀል፣ ዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን በማቅረብ እንደ ክሱ በማስረዳቱ ጥፋተኛ መባላቸውን ፍርድ ቤቱ በውሳኔው ላይ በዝርዝር አስቀምጧል፡፡ ተከሳሾቹም የመከላከያ ማስረጃዎቻቸውን ያቀረቡ ቢሆንም፣ የዓቃቤ ሕግን ማስረጃዎች ማስተባበል ባለመቻላቸው ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ እንዳላቸውም ውሳኔው ያስረዳል፡፡
የክርክር ሒደቱን የመረመረው ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች አንደ ተሳትፎ ደረጃቸው በተከሰሱበት አንቀጽ ወንጀሉን ስለመፈጸማቸው በማስረጃ በመረጋገጡ፣ የቀድሞ የኒያላ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማኅበር ጅግጅጋ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ አብዲ የሱፍ መሐመድ ማኅበራዊ ኃላፊነት በመወጣታቸው፣ የወንጀል ሪከርድ የሌለባቸው በመሆኑ፣ የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናቸው፣ የጤና እክል ስላጋጠማቸውና አገራዊ ልማት ተሳትፎ እንዳደረጉ ጠቅሰው ካቀረቧቸው አጠቃላይ 11 የቅጣት ማቅለያዎች መካከል ሰባቱን በማቅለያነት በመያዝ በአምስት ዓመታት ፅኑ እስራትና በ5,500 ብር እንዲቀጡ ወስኗል፡፡
የሶማሌ ፕሪንቲንግ ፕሬስ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ) ካቀረቧቸው ስምንት የቅጣት ማቅለያዎች ውስጥ ስድስቱን በመያዝ በስድስት ዓመት ፅኑ እስራትና በ8,000 ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ የተወሰነ ሲሆን፣ ሌሎቹ ሁለት ተከሳሾች የቀድሞው የሶማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ መሐመድ አህመድና አቶ አብዱላሂ ሁሴን ደግሞ በሌሉበት የተከሰሱ በመሆናቸው፣ እያንዳንዳቸው በስምንት ዓመት ፅኑ እስራትና በ30,000 ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ የፌዴራል ፖሊስም በሌሉበት ውሳኔ የተሰጠባቸውን ፍርደኞች አፈላልጎ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረከብና ማረሚያ ቤቱም እስራቱን አንዲያስፈጽም ትዕዛዝ በመስጠት መዝገቡን ዘግቷል።
የሶማሌ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ መሐመድ አህመድ መጋቢት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ከሶማሌ ፕሪንቲንግ ፕሬስ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ አዲሱ (ቴዲ ማንጁስ) ጋር ለመጀመሪያና ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መጻሕፍት አሳትሞ የማቅረብ የግዥ ውል ጋር በተያያዘ፣ ተከሳሹ የፌዴራል መንግሥት የተመዘገበ ሕዝባዊ ድርጅት የኒያላ ኢንሹራንስ አሠራርና መመርያ ውጪ ያለአግባብና ባልተገባ የውል ስምምነት፣ መጽሐፉ ታትሞ ገቢ ሳይደረግ ለአቶ ቴዎድሮስ (ቴዲ ማንጁስ) 15‚306‚803 ብር ክፍያ እንዲከፈል ማድረጋቸውን ዓቃቤ ሕግ በክሱ አስፍሯል፡፡ በሌሉበት የተፈረደባቸው ተከሳሾችም ገንዘቡ እንዲመለስ ወይም መጻሕፍቱ እንዲገቡ ባለማድረጋቸው፣ አቶ ቴዎድሮስ ደግሞ ከመንግሥትና ሕዝባዊ ድርጅት ኃላፊዎች ጋር ተመሳጥረው ያላግባብ ዋስትና እንዲሰጣቸው አድርገው ክፍያ በመውሰድ፣ መጻሕፍቱንም ባለማቅረባቸው፣ በሕዝብና በመንግሥት ገንዘብና በመማር ማስተማር ሒደት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ መሆናቸውን በመዘርዘር ዓቃቤ ሕግ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ መሆናቸውን ገልጾ ክስ እንደ ተመሠረተባቸው መዘገባችን ይታወሳል፡፡