በአገር ውስጥ ያለው የሥጋ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት፣ ሥጋ ላኪዎች የዋጋ ጭማሪ ሊያደርጉ መሆኑን የኢትዮጵያ ሥጋ አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር አስታወቀ።
በኦሮሚያ ክልል በቦረናና በጉጂ ዞኖች በተከሰተው ድርቅ ምክንያት የአገር ውስጥ ሥጋ ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት ለዓለም አቀፍ ገበያ በሚያቀርቡት የሥጋ ምርት ላይ የዋጋ ጭማሪ ሊያደርጉ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ሥጋ አምራቾችና ላኪዎች ማኅበር ዋና ጸሐፊ አቶ አበባው መኮንን ለሪፖርተር ተናግረዋል።
ስድስት ወራት ያስቆጠረው ድርቅ በቦረና ዞን ብቻ እስካሁን 7.3 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ ከ500 ሺሕ በላይ ከብቶችን መግደሉን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ለኤክስፖርት የሚፈለግ ሥጋ አብዛኛው ከዚህ አካባቢ የሚገኝ በመሆኑና በርካታ ከብቶች በመሞታቸው፣ በአገር ውስጥ የሥጋ ዋጋ ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ገልጸዋል።
በኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ የቢሾፍቱ ኤክስፖርት ቄራ ዳይሬክተር ሳለአምላክ አብነው (ዶ/ር)፣ በአገር ውስጥ ለሥጋ ላኪዎች የሚቀርበው የሥጋ መጠን ቅናሽ ማሳየቱን ገልጸው በዋጋም ላይ ጭማሪ መታየቱን ተናግረዋል። ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የሚባለው የዋጋ ጭማሪ በኪሎ ሦስት ብር እንደነበር ገልጸው፣ አሁን የታየው ጭማሪ በአንድ ወር ውስጥ 30 ብር መድረሱን ጠቁመዋል። በአገር ውስጥ የአንድ ኪሎ የኤክስፖርት ሥጋ መግዣ ዋጋ 260 ብር እንደነበረ፣ በአሁኑ ወቅት ግን 290 ብር ደርሷል ብለዋል።
በአገር ውስጥ የሥጋ ዋጋ መወደድና የአቅርቦት መጠን ማነሱ ቄራዎችን ያልተገባ ውድድር ውስጥ እንዲገቡ ከማድረግም በላይ፣ ገበያ ውስጥ ለመቆየት አስቸጋሪ እንደሚያደርግባቸው ተናግረዋል። ለዚህም ትርፍ ለማግኘት ባይቻል እንኳን፣ ድርጅቶቹ ሳይዘጉ ለመቆየት የሚያስችላቸውን የዋጋ ማሻሻያ መደረግ እንዳለበት ገልጸዋል።
ሥጋ ላኪዎች ከሚጠቀሟቸው እንስሳት መካከል ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከቦረና፣ ከባሌና ከሶማሌ አካባቢዎች የሚገኙ መሆናቸውንና በተቀባይ አገሮችም የበለጠ ተፈላጊነት ያላቸው እነዚህ አካባቢዎች የሚገኝ ሥጋ መሆኑን አቶ አበባው ገልጸው፣ በዋጋው መጨመር ምክንያት የሚከሰት የላኪዎች ኪሳራ ለመቀነስ የዋጋ ማስተካከያ ሊደረግ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት አንድ ኪሎ ሥጋ ለተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ (በዋናነት ዱባይ) በ6.5 ዶላር የሚሸጥ ሲሆን፣ ለሳዑዲ ዓረቢያ የሚቀርበው ሥጋ ደግሞ በኪሎ 6.8 ዶላር ነው። በዚህም መሠረት የሌሎች አቅራቢ አገሮችን ዋጋና አቅርቦት መሠረት በማድረግ ተቀባይ አገሮችን የማያሸሽ የዋጋ ጭማሪ እንደሚደረግ አቶ አበባው ገልጸዋል። በአንድ ቶን የሥጋ ምርት ላይም ቢያንስ 200 ዶላር እንደሚጨመር ጠቁመዋል።
በቦረና አካባቢ ከሚገኙ ቆላማ ቦታዎች ከሚገኙ እንስሳት በተጨማሪ፣ የሌሎች አካባቢ እንስሳትን መጠቀም አይቻልም ወይ በማለት ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት አቶ ሳለአምላክ አብነው (ዶ/ር)፣ የእንስሳት አቅርቦት በድርቁ ምክንያት እየቀነሰ በመምጣቱ ትኩረታቸውን ወደ ደቡብ ክልል አካባቢዎች ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ከአርባ ምንጭ፣ ከጂንካና ከኮንሶ አካባቢ የሚገኙ እንስሳት በሥጋ ጣዕምም ሆነ በሳቢነት የተሻሉ ከመሆናቸው ተጨማሪ የአቅርቦት አማራጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስተድተዋል።
ሥጋ ላኪ ቄራዎች ዓመታዊ የማምረት አቅማቸው ከ200,000 ቶን በላይ ቢሆንም፣ በእንስሳት አቅርቦት እጥረት ምክንያት እያመረቱ የሚገኙት ከ20,000 ቶን በታች መሆኑን ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወሳል። በ2014 በጀት ዓመት የመጀመርያ ስድስት ወራት ውስጥ 10,000 ቶን ሥጋ ምርት ወደ ውጭ አገር የተላከ መሆኑን፣ በዚህም 50 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን የሥጋና የወተት ልማት ኢንስቲትዩት መረጃ ያመለክታል።