Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባለፉት ስምንት ወራት ኤክስፖርት ከተደረገ ቡና 746 ሚሊዮን ዶላር ተገኘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በበጀት ዓመቱ መጨረሻ አንድ ቢሊዮን ዶላር ገቢ እንደሚገኝበት ከሚጠበቀው የቡና ኤክስፖርት፣ ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ 746.8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የገበያ ልማትና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክትር አቶ ሻፊ ዑመር ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ አገሪቱ በስምንት ወራት ውስጥ 157 ሺሕ ቶን መጠን ያለው ቡና ወደ ውጭ በመላክ 527 ሚሊዮን ዶላር ገቢ የማግኘት ዕቅድ ነበራት፡፡

ባለሥልጣኑ ከዕቅዱ ከፍተኛ ብልጫ የተገኘበት የውጭ ምንዛሪ ገቢና ምርት በስምንት ወራቱ ውስጥ እንዳገኘ ያስረዱት አቶ ሻፊ፣ 183,155 ቶን ቡና በመላክ 746.8 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል ብለዋል፡፡

በ2014 ዓ.ም. በስምንት ወራት ውስጥ የተላከው ቡና ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ከተላከው 119,498 ቶን የ63,656 ቶን ብልጫ የተመዘገበበት እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ ከገቢ አኳያም ተመዝግቦ ከነበረው የ405 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በ341 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ ያለው ገቢ እንደተገኘ ተገልጿል፡፡

 በየካቲት ወር ብቻ 19,954 ቶን ቡና ለመላክ ታቅዶ 20,337 ቶን ቡና ወደ ተለያዩ አገሮች እንደተላከ ያስታወቀው ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ፣ በወሩ ይገኛል ተብሎ ከተጠበቀው 75 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ዕቅድ ከፍተኛ የቁጥር ብልጫ ያለው 101.7 ሚሊዮን ዶላር ገቢ በአንድ ወር ውስጥ እንደተገኘ አስታውቋል፡፡

ዓምና በተመሳሳይ ወር ኢትዮጵያ 15,690 ቶን ቡና ወደ ውጭ ልካ 59.5 ሚሊዮን ዶላር እንዳገኘች ያስታወሱት አቶ ሻፊ፣ ዘንድሮ በየካቲት ወር የተገኘው ገቢ በ42 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ እንደታየበት አስታውቀዋል፡፡

የቡናና ሻይ ባለሥልጣን ከቡና ኤክስፖርት ይገኛል ተብሎ ያስቀመጠውን የአንድ ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ገቢ ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችል አፈጻጸም ላይ እንደሚገኝ ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ የተገኘው ገቢ አመላካች ነው ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ በቀሪዎቹ አራት ወራት ውስጥ የሚገኘው ገቢ በዕቅዱ ልክ ቢሄድ እንኳን ከተቀመጠው አኃዝ በላይ አፈጻጸም እንደሚመዘገብ ለመገመት ይቻላል ብለዋል፡፡

ባለሥልጣኑ ሁለት ስትራቴጂዎችን ነድፎ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ያስታወቁት አቶ ሻፊ፣ የመጀመርያው ነባሩ የኢትዮጵያ ቡና መዳረሻ ገበያዎች ላይ በተወዳዳሪነት መቆየት ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ አዳዲስ የቡና ገበያ መዳረሻ አገሮችን ማፈላለግ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አዳዲስ የቡና መዳረሻ አገሮች ከሆኑት ውስጥ ሩሲያ፣ ቻይናና ታይዋን ተጠቃሾቹ እንደሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ከእነዚህ ከፍተኛ የኢትዮጵያ የቡና ገዥ አገሮች ምድብ ውስጥ እየገቡ ካሉ አገሮች ጋር ያለውን ገበያ ይበልጥ ለማጠናከር በርካታ ሥራዎች እንደሚከናወኑ አቶ ሻፊ ገልጸዋል፡፡

የቡና ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ እየጨመረ መምጣቱ በዘርፉ እየተገኘ የሚገኘው ገቢ ለመጨመሩ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ በሻገር በተለያዩ አገሮች በሚደረጉ ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽኖች ላይ ምርቱን ለማስተዋወቅ የሚደረጉት ጥረቶች ሚና እንዳላቸው ተነግሯል፡፡

ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም ከነበራት የሦስተኛ ደረጃ የቡና ገዥነት ምድብ ሁለት ደረጃዎችን ሸርተት ብትልም በዚህ ወቅትም አሜሪካ ከፍተኛ የቡና ገዥ አገሮች ምድብ ውስጥ እንደምትገኝ የተናገሩት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ ሌሎች የእስያ አገሮች ፍላጎታቸው እየጎላ ቢመጣም የአሜሪካንን ገበያ አሁንም ለማጠናከር በሚደረጉ ኤግዚቢሽኖች ለማስተዋወቅ እየተሠራ እንደሆነ አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያን ቡና ከሚገዙት አገሮች መካከል ጀርመን በቀዳሚነት ስትቀመጥ፣ ሳዑድ ዓረቢያና ጃፓን ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ አገሮች ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች