Thursday, May 30, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ሰብዓዊነትን የሚገዳደረው ጭካኔ በሕግ መቆም አለበት!

ኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈጸሙ ያሉ ኢሰብዓዊ ጭካኔዎችና ወንጀሎች ገደባቸውን እያለፉ ነው፡፡ ከሰውነት ደረጃ የወረዱ አውሬያዊ ባህሪያት ሰው የመሆን ፀጋን እየገፈፉ ነው፡፡ በአደባባይ ሰብዓዊ ፍጡርን ዘቅዝቆ መስቀል፣ በጭካኔ መግደል፣ ማሰቃየት፣ ማፈናቀል፣ አስገድዶ መድፈርና የመሳሰሉት ነውረኛ ድርጊቶች ተባብሰው ቀጥለው የሰው ልጅን ከእነ ሕይወቱ እሳት ውስጥ መክተት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን ዘግናኝና አሳፋሪ ድርጊት በሰብዓዊነት ስሜት በአንድነት ማውገዝ ሲገባ፣ የማንነት ታፔላ በማንገብ የአውሬ ባህሪ ማሳየት ተለምዷል፡፡ በዚህ ዘመን እየተፈጸሙ ላሉ ጭካኔ ለተፀናወታቸው ድርጊቶች የጋራ ኃላፊነት መኖር ሲገባው፣ ለእያንዳንዱ ኢሰብዓዊነት ለተሞላበት አረመኔያዊ ተግባር በማንነት ላይ የተመሠረተ ባለቤት ይፈለግለታል፡፡ ይህ ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም፡፡ ሰብዓዊነት መክኖ ሕግና ሥርዓት በጠፋበት ሁኔታ ውስጥ እየተፈጸሙ ላሉ ወንጀሎች፣ ከመንግሥት ጀምሮ እያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነቱን ለመውሰድ መዘጋጀት አለበት፡፡ መንግሥት ሰሞኑን የተፈጸመውን የጭካኔ ድርጊት አልታገስም ብሎ መግለጫ ሲያወጣ፣ የድርጊቱ ተሳታፊዎችን በሙሉ ለቃቅሞ ሕግ ፊት ማቅረብ ግዴታው ነው፡፡ እውነተኛ ኢትዮጵያውያንም ማንነትና እምነት ሳይበግራቸው የድርጊቱን ፈጻሚዎች ማውገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ማንም ከማንም እንደማይበልጥ በተግባር መረጋገጥ አለበት፡፡ 

በማኅበራዊ የትስስር ገጾች በተለቀቀው ቪዲዮ በእሳት እንዲቃጠል የተደረገው ግለሰብ ማንም ይሁን ማን፣ ሀቀኛ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን ወደፊት ሊደርስባት ከሚችለው መከራ አኳያ በማገናዘብ በሰብዓዊነት የድርጊቱ ፈጻሚዎች ለሕግ እስኪቀርቡና መቀጣጫ እስኪሆኑ ድረስ በአንድነት መቆም አለባቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ፀያፍ ድርጊቶችን በሰብዓዊ ፍጡርነት መንፈስ አለማውገዝና የድርጊቱን ፈጻሚዎች አለመጋፈጥ፣ የታሪክና የትውልድ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ አረመኔያዊ ድርጊቶችን ከማንነት፣ ከእምነት፣ ከፖለቲካዊ ወገንተኝነትና ከተለያዩ ፍላጎቶች ህሊናን ነፃ በማድረግ መጋፈጥ የግድ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን መጀመሪያ ሰብዓዊ ፍጡራን መሆናቸውን መገንዘብ አለባቸው፡፡ ሰው መሆን ያስፈልጋል፡፡ የጋራ ማንነትና ዕጣ ፈንታ ባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ ራሳቸውን ልዩ ፍጡር አድርገው የሚመለከቱ ሕገወጦችን መመከት የሚቻለው፣ እየተፈጸሙ ያሉ የጭካኔ ወንጀሎችን በአንድነት ለመፋለም የሚያስችል ሞራላዊ ልዕልና በመታጠቅ ነው፡፡ ከሴራ፣ ከሸፍጥና ከምግባረ ቢስ አስተሳሰቦች መላቀቅ ተገቢ ነው፡፡ በሞራላዊ ዝቅጠትና በእኩይ ምግባር ደንዝዘው አገርን ተስፋ የሚያስቆርጡትን ለመጋፈጥ፣ የኢትዮጵያዊነት ትልቁ ምሥል አመልካች የሆነውን አለመበገር በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህም ሲባል ለሰብዓዊነት የሚፈለገውን መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀት የግድ መሆን አለበት፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት አስመልክቶ በቅርቡ ያወጣው ሪፖርት ኢትዮጵያ ያለችበትን አስፈሪ ነባራዊ ሁኔታ በጨረፍታ የሚያሳይ ቢሆንም፣ የጥቃት ሰለባ በሆኑ ወገኖች ላይ የደረሰው የማይሽር ጠባሳ ግን ይህንን ትውልድ አንገቱን የሚያስደፋ እንደሆነ መተማመን ተገቢ ነው፡፡ ጦርነቱ በተካሄደባቸው ሥፍራዎች ተሳታፊ በነበሩ ተፋላሚ ኃይሎች በሰላማዊ ሰዎች (ሕፃናት፣ ሴቶች፣ አዛውንቶች፣ አቅመ ደካሞች) ላይ የተፈጸሙ አስነዋሪ ግድያዎች፣ ጥቃቶችና ድርጊቶች ኢትዮጵያ ያለችበትን አደገኛ ጊዜ አመልካች ናቸው፡፡ ይህ ትውልድም በማንነት፣ በእምነት፣ በፖለቲካ ዝንባሌና በመሳሰሉት ጭንብሎች ውስጥ ተደብቆ ጣት መጠቋቆም አይችልም፡፡ ምክንያቱም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለፈሰሰው የንፁኃን ደምም ሆነ ዕንባ ተጠያቂነት ይኖርበታል፡፡ ይህንን ድርጊት የፈጸሙት እነ እከሌ ናቸው ተብሎ ማምለጥ አይሞከርም፡፡ አሁንም በተለያዩ ሥፍራዎች እየደረሱ ላሉ አረመኔያዊ ድርጊቶች ባለቤት ፍለጋ የሚባዝኑ ግለሰቦችም ሆኑ ስብስቦች፣ ከጭካኔ ድርጊቶቹ ጀርባ ያላቸውን አስተዋፅኦ አጢነው ከድርጊታቸው ቢቆጠቡ መልካም ነው፡፡ የሰብዓዊነት የመጀመሪያው መርህ የጭካኔ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ መከላከል መቻል ነው፡፡ ድንገት ሲያጋጥሙም ዘር፣ እምነት፣ ቀለም፣ ፆታና የመሳሰሉ ተፈጥሯዊ ልዩነቶችን ወደ ጎን በማለት በአንድነት መቆም ነው፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ ግን ሰብዓዊነት ታግቷል፡፡

ሰሞኑን በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል ዞን በጉባ ወረዳ በአይሲድ ቀበሌ ከሕግ ውጪ የተፈጸመ ግድያ፣ እንዲሁም የሟቾችን አስከሬን በሕይወት ከነበረ ግለሰብ ጋር የማቃጠል ድርጊት የመንግሥት የፀጥታ አባላትና ሌሎች ሰዎችም ተሳትፈውበት መከናወኑን የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ማረጋገጡን አስታውቋል፡፡ ለዚህ ክስተት መነሻ የሆነውም ድርጊቱ ከመፈጸሙ አንድ ቀን አስቀድሞ፣ ቢያንስ በ20 የመንግሥት የፀጥታ አባላትና በሌሎች ግለሰቦች ላይ የተፈጸመ ግድያ መንስዔ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ እንደሚታወቀው ሥራ ላይ ያሉ ሕግ አስከባሪዎችን መተናኮልም ሆነ ከዚያ ያለፈ ድርጊት መፈጸም ሕገወጥነት ነው፡፡ ሕግ አስከባሪዎችም በቁጥጥር ሥር ያሉ ጥፋተኞችን ወይም ተጠርጣሪዎችን ሕግ ፊት ማቅረብ እንጂ፣ ከሕግ ውጪ በራሳቸው ዕርምጃ መውሰድ የለባቸውም፡፡ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እንዳለውም ሕግ ፊት መቅረብ ያለባቸውን ተጠርጣሪዎች በእሳት አቃጥሎ መግደል፣ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት የሰብዓዊ መብት ጥሰት ነው፡፡ መንግሥት ይህንን ጉዳይ በፍጥነት ተከታትሎ ምርመራ በማድረግ፣ ሕግ ፊት ማቅረብና ውጤቱንም ለሕዝብ ይፋ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ሕዝብ ደኅንነቴን ይጠብቁልኛል የሚላቸው ሕግ አስከባሪ አካላት በዚህ ሁኔታ ላይ ሆነው በሕግ ሊተማመን አይችልም፡፡

ኢትዮጵያውያን ፈሪኃ ፈጣሪ ያደረባቸው መሆናቸው ለዘመናት በሚነገርባት አገራቸው ውስጥ አረመኔያዊ ድርጊቶች ሲፈጠሩ፣ መርጦ ማዘንና ማልቀስ በብዙዎቹ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች አጋፋሪ ልሂቃን እየተለመደ መሆኑን መገንዘብ አለባቸው፡፡ ለዘመናት በተገነቡት የጋራ ማኅበራዊ እሴቶች ውስጥ የማይታወቁ እነዚህን መሰል የጭካኔና የግፍ ድርጊቶች ሲፈጸሙ፣ ልሂቃኑ ግራና ቀኝ ሆነው የሚፋለሙት አብረው ለሚያኗኑሩት ዘለቄታዊ እሴቶች ሳይሆን ለፋይዳ ቢስ የፖለቲካ ቁማር መሆኑ ያስተዛዝባል፡፡ በዚህ በሠለጠነ ዘመን አንድም ሰው ጥቃት እንዳይደርስበት ወይም ሕይወቱ ደመ ከልብ እንዳይሆን በጋራ መቆም የሚገባቸው ብዙዎቹ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ልሂቃን፣ ከሰብዓዊነት ደረጃ ወርደው የብሔራቸውን ወይም የእምነታቸውን ተጋሪ ሊከላከሉ ሲዋደቁ ማየት ሰው መሆናቸው ያጠራጥራል፡፡ ብዙኃኑ ሕዝብ አሁንም እርስ በርሱ ተዛዝኖና ተደጋግፎ በሚኖርባት ኢትዮጵያ፣ ሰው መሆን ዋጋው ወርዶ በብሔርና በመንደር ሲመነዘር ከመቼውም ጊዜ በላይ ሊያሳስብ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያውያን አገራቸውን እያደር ቁልቁል የሚያንሸራትታትን ኢሰብዓዊነት የተሞላው ጭካኔ በጋራ የማስቆም ታሪካዊ ግዴታ አለባቸው፡፡ መጪው ትውልድ የሚረከባትን ኢትዮጵያ ከግፈኞችና ከጨካኞች አስተሳሰብ ማፅዳት ካልተቻለ፣ ይህ ትውልድ በታሪክ እንደሚጠየቅ ማወቅ አለበት፡፡

አሁንም ደግሞ ደጋግሞ ማሳሰብ የሚያስፈልገው ሕግና ሥርዓት እንዲከበር ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በመረጡበት ሥፍራ መዘዋወር፣ መኖር፣ መሥራት፣ ሀብት ማግኘት፣ ትዳር መሥርተው ቤተሰብ ማፍራት የሚችሉት የሕግ የበላይነት ሲከበር ብቻ ነው፡፡ መንግሥት በሕግ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት ሕግ አክብሮ ማስከበር ይጠበቅበታል፡፡ ዜጎችም መብቶቻቸውን ሲጠይቁ ሕግ የማክበር ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ሕግና ሥርዓት እንዲኖር ደግሞ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ያስፈልጋል፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የያዘው አካል በሥልጣኑ መባለግ የለበትም፡፡ ሥልጣን ለመያዝ የሚፎካከረውም ሰላማዊና ሕጋዊ መሆን አለበት፡፡ የዜጎች መብቶች የሚከበሩት የሕግ የበላይነት መኖሩ ሲረጋገጥ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ያለው ሴረኝነት አገር አውዳሚ ነው፡፡ ሕግና ሥርዓት ሲጠፋ ሥርዓተ አልበኝነት ይነግሣል፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት አይኖርም፡፡ የተመቸው ሁሉ እየተነሳ ውድና ክቡር የሆነውን የሰው ሕይወት በቀላሉ ያጠፋል፡፡ ሕግና ሥርዓት በሌለበት ሰብዓዊነት ወደ ጎን እየተገፋ ግፍና ጭካኔ ይበዛል፡፡ በኢትዮጵያ በብዙ ሥፍራዎች እየተስተዋለ ያለው ሰብዓዊነትን የሚገዳደር ጭካኔ በሕግ መቆም አለበት!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

[የክቡር ሚኒስትሩ ባለቤት የኬንያው ፕሬዚዳንት ያስተላለፉትን መልዕክት ተመልክተው ባለቤታቸውን በነገር ይዘዋቸዋል]

የኬንያው ፕሬዚዳንት ከሕዝባቸው ለቀረበባቸው ቅሬታ የሰጡትን ምላሽ ሰማህ? እንኳን ምላሻቸውን...

የኢትዮ ኤርትራ ሰሞነኛ ሁኔታና ቀጣናዊ ሥጋቱ

“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩን እንገንባ” የሚል ፖለቲካዊ መፈክር ጎልቶ በሚሰማበት፣...

ኦሮሚያ ባንክ ከተበዳሪ ደንበኞቼ ውስጥ 92 በመቶ የሚሆኑት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ናቸው አለ

ኦሮሚያ ባንክ ለደንበኞቹ ከሰጠው ብድር ውስጥ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች...

ሽቅብና ቁልቁል!

ጉዞ ከመገናኛ ወደ ሲኤምሲ ጀምረናል። ተሳፋሪዎች የዕለት ጉርሳቸውን መሸፈን...

እኛ ኢትዮጵያውያን ከየት መጥተን ወዴት እየሄድን ነው?

በአሰፋ አደፍርስ ኢትዮጵያውያን ከየትም እንምጣ ከየት እስከ 1445 ዓ.ም. እስላማዊና...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዲጂታል ቴክኖሎጂው የዜጎችን መብትና ነፃነት ለማስከበር ይዋል!

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ አካባቢ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የዲጂታል ሪፎርም ሥራን አስመልክቶ በተዘጋጀ ሥነ ሥርዓት፣ የፌዴራል ፖሊስ ባለፉት ስድስት ዓመታት...

ለዘመኑ በማይመጥን ዕሳቤ አገር ማተራመስ ይብቃ!

ዘመኑ እጅግ ድንቅ የሚባሉ የሥልጣኔ ትሩፋቶችን በረቀቁ ቴክኖሎጂዎች እያቋደሰ ነው፡፡ ለልማትና ለዕድገት የሚማስኑ የኑሮን ጫና ቀለል የሚያደርጉ ቴክኖሎጂዎችን በብዛትና በስፋት ሲጠቀሙ፣ ያላደላቸው ደግሞ እርስ...

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...