Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከአምስት ቀናት በፊት በዋግ ኽምራ ቤላ ተራራ ላይ የተነሳው የሰደድ እሳት አልጠፋም

ከአምስት ቀናት በፊት በዋግ ኽምራ ቤላ ተራራ ላይ የተነሳው የሰደድ እሳት አልጠፋም

ቀን:

  • ክልሉ ለፌዴራል ከማሳወቅ ባለፈ ያደረገው ነገር የለም
  • ከ150 ሄክታር በላይ ደንና መሬት መቃጠሉ ተገልጿል

በአማራ ክልል የዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳዳር ሥር በሚገኘው ቤላ አምባ የማኅበረሰብ ጥብቅ ደን ላይ ከባለፈው ሳምንት ቅዳሜ መጋቢት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የተከሰተው ሰደድ እሳት ሳይጠፋ አምስተኛ ቀኑን ይዟል፡፡ የቤላ ተራራ እሳት ቃጠሎ ተራራው ካለው 953.96 ሔክታር መሬት ስፋት ውስጥ 150 ሔክታር የሚሆነውን ደንና መሬት አቃጥሏል፡፡

ከባህር ዳር ከተማ በ430 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የቤላ ተራራ ላይ የተነሳው ሰደድ እሳት፣ የተነሳበት ምክንያት ባይታወቅም እሳቱ ከተነሳበት ጊዜ አንስቶ የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ሚሊሻና ልዩ ኃይል አባላት ለማጥፋት ጥረት ማድረጋቸውን የዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽ መምርያ ኃላፊ አቶ ከፍያለው ደባሽ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ይሁንና አካባቢው ገደላማ በመሆኑ እሳቱን ሙሉ ለሙሉ በሰው ኃይል ማጥፋት አልተቻለም፡፡

ተራራው የሚገኝበት ጋዝጊብላ ወረዳ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ሰሎሞን መዓዛም እንደገለጹት፣ በተራራው ላይ የሚገኘው ጭዳ የተባለና በቶሎ የሚቀጣጠል ሳር ለሰደድ እሳቱ መባባስ መንስዔ ነው፡፡ እሳቱን በሰው ኃይል ለማጥፋት ተሞክሮ የተወሰነውን ለመቆጣጠር ቢቻልም፣ ምሽቱን በሙሉ የሚነሳው ንፋስ እሳቱን በድጋሚ እያቀጣጠለና ሰው ወደማይገባበት ቦታ እያስፋፋው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከባህር ጠለል 3500 ከፍታ ላይ የሚገኘውን የቤላ ተራራን አቀበት ለመውጣት፣ ከ2፡30 እስከ ሦስት ሰዓት እንደሚፈጅ የገለጹት ሰቶ ሰሎሞን፣ መሣሪያዎችን ተሸክሞ ይኼንን ያህል ርቀት መጓዝ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ ውኃ የሚገኘውም ተራራው ካለበት አካባቢ ከስድስት እስከ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ መሆኑን አክለዋል፡፡

ተራራው በውስጡ እንደ ድኩላ፣ ሚዳቋ፣ ሰስቀበሮ ያሉ እንስሳት የሚገኙበት ሲሆን፣ እንደ አስት፣ ጥቁር እንጨት፣ ፅድ፣ ኮሶ እና ወይራ ያሉ ዕፀዋትን ይዟል፡፡ በተጨማሪም የአካባቢው ወጣቶች በተራራው ዙሪያ የሚገኙ ዛፎች ላይ ንብ በማነብ የማር ምርት የሚያገኙበት መሆኑን አቶ ሰሎሞን አስረድተዋል፡፡ የተራራው ውስጣዊ ክፍል የዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዋና ከተማ ለሆነችው ሰቆጣም ጭምር የውኃ አቅርቦት ይገኝበታል ተብሎ የሚታሰብ ነው፡፡

የዞኑ አመራሮች ሰደድ እሳቱ እየተስፋፋ በመሆኑ በተራራው ላይ ወደሚገኙ መንደሮች ይስፋፋል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ እሳቱን በጊዜ መቆጣጠር ሳይቻል ቀርቶ በብዝኃ ሕይወቱ ላይ ጉዳት የሚደርስ ከሆነ ተስፋ የተጣለበትን የውኃ ሀብት ይጎዳል የሚል ፍራቻም ተፈጥሯል፡፡

ቦታው ገደላማና ወጣ ገባ በመሆኑ በሰው ኃይልም ሆነ በእሳት አደጋ መከላከያ መኪና እሳቱን ማስቆም እንደማይቻል በመግለጽ፣ ሄሊኮፕተር እንደሚያስፈልግ ለክልሉ ማስታወቃቸውን የሚናገሩት አቶ ሰሎሞን፣ ነገር ግን የክልሉ መንግሥት እስካሁን ምላሽ እንዳልሰጠ ገልጸዋል፡፡ ኃላፊው የክልሉ መንግሥት “ሄሌኮፕተር የለም” የሚል ምላሽ እንደሰጣቸውና ከትላንት በስቲያ ሰኞ ለሌላ ሥራ ወደ ወረዳው የመጡ አመራሮች ጋር ንግግር ቢደረግም መፍትሔ አለመገኘቱን አስታውቀዋል፡፡

የዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽ መምርያ ኃላፊ አቶ ከፍያለው በበኩላቸው፣ የአማራ ክልል የአካባቢ፣ የደንና የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለሥልጣን ስለ ተራራው ቃጠሎ ጥያቄ ሲቀርብለት በአፋጣኝ ምላሽ አለመስጡን በመጥቀስ፣ ‹‹የጉዳዩ ባለቤት ሆኖ እያለ በደብዳቤ አሳውቁን ማለቱ ተገቢ አይደለም፤›› የሚል ቅሬታ አንስተዋል፡፡

የአማራ ክልል የአካባቢ፣ የደንና የዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለሥልጣን በበኩሉ፣ ጉዳዩን ለፌደራል መንግሥት ማሳወቁንና ምላሽ እየተጠባበቀ መሆኑን አስረድቷል፡፡ የባለሥልጣኑ ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እሸቱ ባለሥልጣኑ ከማስተባባር በዘለለ ማድረግ የሚችለው ነገር እንደሌለ ከገለጹ በኋላ ባለሙያዎች ግን ወደ አካባቢው መላካቸውን አስረድተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ደን ልማት፣ ተራራው ላይ የደረሰውን ቃጠሎ አስመልክቶ መረጃ እንደደረሰው ያስታወቀ ሲሆን፣ እሳቱን የማጥፋት ሥራውን ለማገዝ የ500 ሺሕ ብር ድጋፍ ማፅደቁን አስታውቋል፡፡ በአፋጣኝ ይደርሳል የተባለው የድጋፍ ገንዘብ የፀደቀው ኅብረተሰቡን ለማንቀሳቀስና የተለያዩ መሣሪያዎችን ለሟሟላት እንዲያስችል ነው፡፡

የደን ጥበቃና እንክብካቤ ዳይሬክተር ጄነራል አቶ ካብታሙ ግርማ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የአየር ውኃ ርጭት ለማካሄድ የሚሆን ሄሊኮፕተር ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የአገሪቱም አቅም ይህንን ለማድረግ የማያስችል መሆኑን የተናገሩት አቶ ካብታሙ፣ ሄሊኮፕተር ለማግኘት ያለው ሒደትም ቢሆን ረዥም ጊዜን የሚፈጅ መሆኑን አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...