Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ድርጅት ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደገጠመው አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ድርጅት በተደጋጋሚ እየገጠመው ባለው የኬብል ዘረፋ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ እንደደረሰበትና በዚህም ሳቢያ ለትራንስፖርት አገልግሎት መቆራረጥ እየዳረገው መሆኑን አስታወቀ፡፡ የቀላል ባቡር ኃይል ማስተላለፊያ ኬብሎች እየተፈጸመ ያለው ተደጋጋሚ ዘረፋ መባባሱን ያስታወቀው ድርጅቱ፣ ባቡሮቹን ለማንቀሳቀስ፣ ለመቆጣጠርም ሆነ ለመምራት እክል እየገጠመው መሆኑን ገልጿል፡፡ በየጊዜው የሚፈጸሙ ዘረፋዎች በድርጅቱ ላይ ቀጥተኛ ኪሳራ ከማስከተል በተጨማሪ፣ በከተማው የትራንስፖርት አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል መፍጠራቸውን ድርጅቱ ለሪፖርተር አስረድቷል፡፡

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ድርጅት የትራንስፖርት ዘርፍ ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ሂቢሶ፣ በቅርብ ጊዜያት በደረሱ ተደጋጋሚ ዘረፋዎች ብቻ ድርጅቱ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ መክሰሩን ገልጸዋል፡፡ ድርጅቱ በየቀኑ በአማካይ ከ70 ሺሕ በላይ ለከተማው ሕዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚያቀርብ የገለጹት አቶ አክሊሉ፣ በዘረፋ ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎቱ ሲቋረጥ ተገልጋዮች ይጎዳሉ ብለዋል፡፡

‹‹ባቡሩን ለመቆጣጠር፣ ለመምራትና ለኮሙዩኒኬሽን የምንገለገልባቸው መሣሪያዎችና ኬብሎች ሲዘረፉ አገልግሎት መስጠት እናቆማለን፡፡ በዋናነት ተደጋጋሚ የዘረፋ ወንጀል እያጋጠመን የሚገኘው በአያት መስመር አካባቢ ነው፡፡ ሆኖም የባቡር መስመሩ በኃይል አቅርቦትም ሆነ በመገናኛ እርስ በርሱ የተሳሰረ በመሆኑ፣ የአንዱ አካባቢ ዘረፋ የሌላውን መስመር አገልግሎት ያቋርጠዋል፤›› በማለት አቶ አክሊሉ የችግሩን ውስብስብነት አስረድተዋል፡፡

ድርጅቱ በየቀኑ የሚሰጠው የትራንስፖርት አገልግሎት ሲቆራረጥ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚያጣው ሕዝብ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎቹ ይስተጓጎላሉ የሚሉት አቶ አክሊሉ፣ ከዚህ በተጨማሪ ድርጅቱ ከትኬት ሽያጭ በቀን ያገኝ የነበረውን 300 ሺሕ ብር ገቢ እንደሚያጣም ጠቁመዋል፡፡

‹‹በባቡሮቻችን ቁጥር መቀነስ የተነሳ በሙሉ አቅም አገልግሎት እየሰጠን አይደለም፤›› ያሉት አክሊሉ፣ ‹‹በውድ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ አገር ተገዝተው የሚመጡ ኬብሎቻችን ለዘረፋ መዳረጋቸው፣ በዚህ የተነሳ በሚከሰት የአገልግሎት መቆራረጥ በሕዝብና በአገር ላይ ጉዳት መድረሱ እንደ ተቋም ፈተና እየሆነብን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎትን ጨምሮ ኢትዮ ቴሌኮምን የመሳሰሉ ተቋማት የኬብል ዘረፋ እያጋጠማቸው መሆኑን ያስታወቁት አቶ አክሊሉ፣ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በተለይ ኅብረተሰቡ ለመሠረተ ልማት አውታሮች ጥበቃ ልዩ ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ በተደረገ ዕገዛ ከሰሞኑ የኬብል ዝርፊያው ጋብ ማለቱን ያወሱት አቶ አክሊሉ፣ የቀላል ባቡሩ ትራንስፖርት አገልግሎቱም ሥራ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

ከጦር ኃይሎች እስከ አያት 17 ኪሎ ሜትር የሚዘረጋውና ከፒያሳ እስከ ቃሊቲ 16 ኪሎ ሜትሮች ርዝማኔ ያለውና በድምሩ 31 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሁለት መስመሮች ያሉት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር 41 ጣቢያዎች እንዳሉት ይነገራል፡፡ ከቻይና በተገኘ 475 ሚሊዮን ዶላር ብድር እ.ኤ.አ. በ2015 ተመርቆ ሥራ የጀመረው ድርጅቱ፣ በየቀኑ 113 ሺሕ ለሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ፈጣን የከተማ ትራንስፖርት እንዲሰጥ ታስቦ መገንባቱ ይታወሳል፡፡

በተደጋጋሚ በሚገጥመው ብልሽት በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት ያልቻለው ድርጅቱ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በሚችለው አቅም አገልግሎት እንዳይሰጥ የዘረፋ ወንጀል እክል እንደሆነበት ነው የተነገረው፡፡ ከሰሞኑ በተደጋጋሚ የባቡር አገልግሎት ሲቋረጥ ታይቷል፡፡ ለዚህ ዋና ምክንያት እየሆነ ያለው ደግሞ የኬብል ዘረፋ መሆኑን ድርጅቱ አመልክቷል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች