Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናኢሰመኮ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ወንጀል ፈጻሚ ሆነው መገኘታቸው በእጅጉ እንደሚያሳስበው ገለጸ

ኢሰመኮ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ወንጀል ፈጻሚ ሆነው መገኘታቸው በእጅጉ እንደሚያሳስበው ገለጸ

ቀን:

  • ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል

ሁለት ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ውስጥ በተፈጸሙ ድርጊቶች፣ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ከዳኝነት ውጪ የሆነ ግድያ (Extra-Judicial Killing) በንፁኃን ላይ መፈጸማቸውን በሪፖርቶቹ ማረጋገጡን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፣ በእነዚህ ድርጊቶች የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ወንጀል ፈጻሚ ሆነው መገኘታቸው በእጅጉ እንደሚያሳስበው ገለጸ፡፡

‹‹በሌሎች ቦታዎች ላይም ያልተደረሰባቸው ተመሳሳይ ጥፋቶች ይኖራሉ፤›› የሚል እምነት እንዳለው አስታውቆ፣ ከቀናት በፊት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተፈጸመውን አሰቃቂ ድርጊት ዋቢ በማድግ በፀጥታ ኃይሎች የሚፈጸሙ እንዲህ ዓይነት ጥፋቶች ‹‹እየተስፋፉ የመሄድ አዝማሚያ እንዳላቸው ያሳያል፤›› ብሏል፡፡

በኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ የሪጅን ዳይሬክተር አቶ ይበቃል ግዛው፣ ከድርጊቱ አሰቃቂነት ባሻገር ሕግን የማስከበር ኃላፊነት ያለባቸው አካላት ራሳቸው፣ ‹‹እንዲህ ለየት ያለ ጭካኔን የሚያሳይ የወንጀል ድርጊት ውስጥ ተሳትፈው መገኘታቸው ጥፋቱን እጥፍ ድርብ ያደርገዋል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

ካለፈው ሳምንት ዓርብ መጋቢት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. አንስቶ በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ሲዘዋወር የነበረ የስድስት ደቂቃ ገደማ ቪዲዮ፣ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና ሌሎች ግለሰቦች አንድን ግለሰብ ከእነ ሕይወቱ እሳት ውስጥ ሲጨምሩ ማሳየቱ ብዙዎችን አስቆጥቷል፡፡ በቪዲዮ ላይ የሚታዩት ግለሰቦች እሳት ውስጥ የጨመሩት ግለሰብ ላይ ጭድ በመጨመር እሳቱ እንዲያያዝ ሲያደርጉ፣ እንዲሁም ሲሳሳቁ በስፋት በተዘዋወረው ቪዲዮ ላይ ታይቷል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት በማግሥቱ ቅዳሜ መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ ድርጊቱን ‹‹እጅግ አሰቃቂና ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ›› በማለት ኮንኖታል፡፡ አፋጣኝ ማጣራት አድርጎ ሪፖርት ያወጣው የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው ድርጊቱን፣ ‹‹ከሕግ አስከባሪ አባሎች የማይጠበቅ ግፍና ጭካኔ የተሞላበት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት፤›› ሲሉ ገልጸውታል፡፡

የሰብዓዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ የሪጅን ዳይሬክተር አቶ ይበቃል እንደሚያስረዱት፣ ኮሚሽኑ ቪዲዮው ከመውጣቱ በፊት ግለሰቦች በእሳት ስለመቃጠላቸው መረጃ ያልነበረው ቢሆንም፣ የመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ተፈጽሞ ሲቪል ሰዎችም ጭምር ሕይወታቸው ስለማለፉ መረጃ አግኝቶ ነበር፡፡ ቪዲዮው በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ላይ መዘዋወር እንደ ጀመረ ግን ኮሚሽኑ በአካባቢው ያሉትን የመረጃ ምንጮች በማግኘት፣ በምንጮቹ ዕገዛ ድርጊቱ ሲፈጸም የነበሩ የዓይን እማኞችን በአጭር ጊዜ ውስጥ ማነጋገሩን አስረድተዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ላይ ምርመራ የሚያካሂድባቸው ሁለት መንገዶች አሉ፡፡ የመጀመርያው መርማሪዎችን በአካል ልኮ ምስክሮችን በማነጋገርና ምልከታ በማድረግ የሚፈጸም ሲሆን፣ ሁለተኛውና የርቀት ምርመራ (Remote Investigation) የሚባለው ደግሞ ተደራሽ ባልሆኑ ቦታዎች አስቸኳይ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ጥቅም ላይ የሚውል ነው፡፡ የካቲት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን በጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ ውስጥ የተፈጠረውን ድርጊት በተመለከተ፣ የተካሄደው የርቀት ምርመራ መሆኑን አቶ ይበቃል ተናግረዋል፡፡

ኮሚሽኑ ድርጊቱን አስመልክቶ ያነጋገራቸው የዓይን ምስክሮች የሰጡት መረጃ እንደሚያሳየው፣ የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በመከላከያ ሠራዊት እጀባ የተደረገላቸው ተሽከርካሪዎች በመተከል ዞን ከሚገኘው ግልገል በለስ ከተማ ወደ ታላቁ ህዳሴ ግድብ፣ ወደ ማንኩሽና ወደ አሶሳ ከተማ ሲጓዙ ነበር፡፡ እነዚህ ተሽከርካሪዎች ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ገደማ በጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ አፍሪካ እርሻ ልማት ማኅበር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲደርሱ፣ ታጣቂዎች ተሽከርካሪዎቹ ላይ በከባድ መሣሪያ የታገዘ ጥቃት በመክፈታቸው ሦስት ሲቪል ሰዎች ተገድለዋል፡፡ መንገደኞቹን አጅበው በመጓዝ ላይ የነበሩት የመከላከያ ሠራዊት አባላት መኪናም በከባድ መሣሪያ በመመታቱ ሻለቃ አመራሩን ጨምሮ ቢያንስ 20 የመከላከያ ሠራዊት አባላት ሲሞቱ፣ 14 ያህሉ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው የኢሰመኮ ሪፖርት ያስረዳል፡፡

ይህንን ጥቃት ተከትሎ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና ጥቃቱን በፈጸሙ የታጠቁ ኃይሎች መካከል እስከ ማግሥቱ የቀጠለ ውጊያ ተደርጎ፣ 30 ያህል ታጣቂዎች ሲገደሉ ቀሪዎቹ ሸሽተዋል፡፡

ጥቃቱ የተፈጸመባቸው ተሽከርካሪዎች ተሳፋሪዎችና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ከቀኑ 6፡00 ሰዓት አካባቢ አይሲድ ከተማ ከደረሱ በኋላ የፀጥታ አባላቱ አግኝተናል ባሉት ጥቆማ መሠረት፣ በአካባቢው በነበሩ ተሽከርካሪዎችና በመኖሪያ ቤቶች ላይ፣ እንዲሁም ከግልገል በለስ ከተማ ወደ ማንኩሽና ባምዛ ይጓዙ የነበሩ ሲቪል ሰዎች ላይ ፍተሻ አካሂደዋል፡፡

አቶ ይበቃል እንደሚያስረዱት፣ የፀጥታ ኃይሎቹ “ጥቆማ ደርሶናል” በማለት ጥቅምት ወር ላይ ከተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ በመተከል ዞን እስር ቤት ታስረው የቆዩና የይለፍ ወረቀት በመያዝ ወደ ቤታቸው እየተመለሱ የነበሩ የትግራይ ተወላጆችን ለይተው ሲጓዙበት ከነበረ መኪና ላይ አስወርደዋል፡፡ በተደረገው ፍተሻም አንድ የወታደራዊ መገናኛ ሬዲዮ፣ የተለያዩ ፎቶግራፎችና ከ40,000 ብር በላይ ገንዘብ በመገኘቱ፣ የመንግሥት ፀጥታ አባላቱ ተጠርጣሪዎቹን እየደበደቡ ተጨማሪ መረጃ መጠየቅ መጀመራቸውን ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የዓይን ምስክሮች ገልጸዋል፡፡

ከተጠርጣሪዎቹ መካከል አንዱ፣ ‹‹በአካባቢው በተፈጸመው ጥቃት ላይ እጃችን አለበት፣ ባምዛ በሚባለውና በግልገል በለስ ቦታዎች ሰዎች አሉን፤›› ማለቱን ተከትሎ፣ ‹‹የመንግሥት የፀጥታ ኃይል አባላት ሁኔታውን የተቃወሙ ሁለት የጉሙዝ ተወላጆችን ጨምሮ አሥር ሰዎችን ተኩሰው ገድለዋል፤›› ማለቱን በመግለጫው አካቷል።

የፀጥታ ኃይሎቹ ግድያውን የፈጸሙት የጠረጠሯቸውን ሰዎች ከመኪና ያስወረዱበት ቦታ ላይ መሆኑን የተናገሩት አቶ ይበቃል፣ የፀጥታ ኃይሎቹ በመቀጠል ቃጠሎ ወደ ተፈጸመበት ቦታ አስከሬን ማጓጓዝ እንዳከናወኑ ተናግረዋል፡፡ ይህንን ማድረግ ከጀመሩ በኋላም፣ ‹‹ተሽከርካሪ ውስጥ ተሸሽጎ የነበረን ግለሰብ በጥቆማ አግኝተናል›› ተብሎ ይህንን ግለሰብ ሳይገድሉ ከእነ ሕይወቱ አጓጉዘው አስከሬን ወዳቃጠሉበት ቦታ ከወሰዱ በኋላ፣ የተገደሉት ሰዎች አስከሬን ሲቃጠል የነበረበት እሳት ውስጥ ከእነ ሕይወቱ እንደጨመሩት ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

አቶ ይበቃል የዓይን ምስክሮችን ጠቅሰው እንደገለጹት፣ ግለሰቦቹን ከመኪና ላይ በማስወረድ የግድያ ድርጊቱን በዋነኛነት የፈጸሙት የመከላከያ ሠራዊትና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ናቸው፡፡ የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል አባላት ተሳትፎ አስከሬን የማጓጓዝና ከእነ ሕይወቱ ተይዞ የመጣውን ግለሰብ ወደ እሳት መወርወር እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የኢሰመኮ ሪፖርት እንደሚያስረዳው በአካባቢው፣ የነበሩት የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የአማራ ክልል ልዩ ፖሊስ አባላትና የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል አባላት በቀጥታ ድርጊቱን በመፈጸም ወይም አስገዳጅ ተግባሮችን ባለመፈጸም (By Commission or Omission) የተለያየ የተሳትፎ መጠን ይኑራቸው ወይም አይኑራቸው በተጨማሪ የወንጀል ምርመራ ሊጣራ የሚገባው ነው፡፡

በሁለት ምክንያቶች የተነሳ ጉዳዩ የተለየ ክብደት ሊሰጠው እንደሚገባ የተናገሩት ዳይሬክተሩ አቶ ይበቃል፣ የመጀመርያው ምክንያት ድርጊቱ ‹‹እጅግ ከሰብዓዊነት ያፈነገጠ፣ ለመመልከትም፣ ለመስማትም የሚከብድ የድርጊት አፈጻጸም ያለው መሆኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ጉዳዩን ከባድ የሚያደርገው ሌላኛው ምክንያት ሕግና ሰላም የማስከበር ኃላፊነትን በመያዝ ሥልጠና ወስደው የተሠማሩ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ድርጊቱን መፈጸማቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እነዚህ ሕግ የማስከበር ኃላፊነት የተጣለባቸው አካላት ራሳቸው ሕግ ጥሰው ሲገኙ በኅብረተሰቡ ዘንድ በመንግሥት ላይና በሕግ የበላይነት ላይ ያለን አመኔታ እንደሚሸረሸር የገለጹት አቶ ይበቃል፣ በሒደት ሰዎች ሕግን በእጃቸው የሚያስገቡበት ወይም በራሳቸው ፍትሕ ለማግኘት የሚሞክሩበት ሥርዓተ አልበኝነት የነገሠበት ሁኔታ እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ኢሰመኮ እሑድ መጋቢት 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ያወጣው ሪፖርት መንግሥት አንድ ቀን አስቀድሞ ካወጣው መግለጫ በበለጠ ሁነቱን እንደዘረዘረ፣ በመንግሥት መግለጫ ላይ ያልተካተቱትን የተጎጂዎች ማንነትና ድርጊቱ የተፈጸመበት ዓውድ ማካተቱን አስረድተዋል፡፡ ምንም እንኳን ድርጊቱ በፍፁም ሊወገዝ የሚገባው ቢሆንም፣ በሪፖርቱ ላይ ፈጻሚዎቹ ድርጊቱን ለምን እንደፈጸሙት ማሳወቅ አግባብ እንደነበር አክለዋል፡፡

‹‹ተጎጂዎቹ መረጃ ሰጥተው የመከላከያ ሠራዊቱ ላይ ጥቃት እንዲደርስ አድርገውም ቢሆን፣ በሁሉም ላይ እንዲህ ዓይነት መሣሪያዎች ቀርቶ የጦር መሣሪያዎች ተገኝቶባቸውም እንኳን ቢሆን የእዚህን ጥፋት ዘግናኝነት፣ የሚወገዝ መሆኑንና የተጠያቂነትን አስቸኳይ አስፈላጊነት በምንም ቅንጣት አይቀንሰውም፤›› በማለት ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ኢሰመኮ የደረሰባቸውን ወይም በመገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ትስስር ዘዴዎች የወጡ መረጃዎችን እንደሚመረምር የገለጹት አቶ ይበቃል፣ ኮሚሽኑም ሆነ የመገናኛ ብዙኃን ያላገኟቸው ሌሎች ተመሳሳይ ድርጊቶች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል እምነት መኖሩን ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች እየሰፉ የመሄድ አዝማሚያ መታየቱን በመጥቀስም፣ መንግሥት በአስቸኳይ ጥብቅ ዕርምጃዎችን መውሰድ፣ ወደ ውስጥ መመልከትና የማስተካከያ ሥራ መሥራት እንዳለበት ዳይሬክተሩ አሳስበዋል፡፡

በተጨማሪም መንግሥት እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች እስኪፈጸሙ ድረስ ጠብቆ ዕርምጃ ከመውሰድ ባሻገር፣ አስቀድሞ ለመከላከል በሚያስችል ሁኔታ የአባላቱን ሥነ ምግባር ማስተካከልና የተጠያቂነቱን ሥርዓት ማጠናከር አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከኢሰመኮ ሪፖርት አስቀድሞ ባወጣው መግለጫ ድርጊቱን የኮነነው መንግሥት፣ ‹‹ይህ እኩይ ድርጊት መጠፋፋትን ያፈጥን ካልሆነ በቀር ሰላምንም ሆነ ፍትሕን ዕውን ሊያደርግ አይችልም፤›› ካለ በኋላ፣ ‹‹መነሻቸውም ሆነ ማንነታቸው ምንም ይሁን ምን መንግሥት ይህን ዓይነት ፍፁም ከሰብዓዊነት የራቀና ጭካኔ የተሞላበትን ድርጊት የፈጸሙ አካላትን አጣርቶ ሕጋዊ ዕርምጃ ይወስዳል፤›› በማለት አቋሙን አሳውቆ ነበር፡፡

ሪፖርተር ጉዳዩን አስመልክቶ ያነጋገራቸው በፍትሕ ሚኒስቴር የወንጀል ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ፈቃዱ ፀጋው ከመከላከያ ሚኒስቴርና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በጋራ ምርመራ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ምርመራው በአፋጣኝ መጀመሩን ያስታወቁት አቶ ፈቃዱ፣ ፍትሕ ሚኒስቴር በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ዓቃቤ ሕጎች ስለነበሩት ምርመራው ላይ እንዲሳተፉ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ባለው ሒደትም በመተከል ዞን የሚገኘው ኮማንድ ፖስት ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ የተወሰኑ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር በማዋል ምርመራ እያደረገ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ደኤታ ሰላማዊት ካሳ በበኩላቸው፣ አገልግሎቱ ምርመራውን ከሚያደርጉ አካላት የተጠናቀረ ሪፖርት እየጠበቀ መሆኑን ገልጸው በቀናት ውስጥ ምርመራውን የተመለከተ መግለጫ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...