Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  [ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን የተካሄደው የብልፅግና ጉባዔ መጠናቀቅን ተከትሎ ማኅበረሰቡ ምን እያለ እንደሆነ ሪፖርት እንዲያቀርብላቸው ካዘዙት አማካሪ ጋር እየመከሩ ነው] 

  [ክቡር ሚኒስትሩ ሰሞኑን የተካሄደው የብልፅግና ጉባዔ መጠናቀቅን ተከትሎ ማኅበረሰቡ ምን እያለ እንደሆነ ሪፖርት እንዲያቀርብላቸው ካዘዙት አማካሪ ጋር እየመከሩ ነው

  • ክቡር ሚኒስትር ስለጉባዔው ሳይሆን ስለችግሮች ነው እየተወራ ያለው። 
  • ምን እየተባለ ነው?
  • አንዳንዱ መንግሥት ይምራን፣ አይከተለን ይላል፡፡
  • ምን ማለት ነው? 
  • መንግሥት የያዘው እሳት ማጥፋት ነው፣ እየመራን አይደለም ማለታቸው ነው፡፡ ክቡር ሚኒስትር፣ ሌላ ደግሞ…
  • ሌላ ምን ይባላል?
  • በአገሪቱ ረሃብ ተከስቷል፣ ማኅበረሰቡ በየቦታው ተቸግሮ ተሠልፏል ይባላል።
  • የምን ሠልፍ?
  • የዘይት፣ የታክሲ፣ የነዳጅ፣ የዳቦ ሠልፍ ነው ይባላል።
  • እህህ…
  • ዳቦ መጋገሪያ ቤቶች ባዶአቸውን ናቸው፣ ትንሽ ዱቄት ያላቸው የተወሰኑትም የሚሸጡበት ዋጋ ንሯል፣ መንግሥት ግን…
  • መንግሥት ምን?
  • መንግሥት ግን ድግስ ላይ ነው፣ ድግስ አብዝቷል ይባላል። 
  • የምን ድግስ?
  • ፕሮጀክቶችን ለመመረቅ በየዕለቱ ድግስ ላይ ነው ይባላል።
  • ፕሮጀክቶች የሚመረቁት ለሕዝብ ጥቅም አይደለም እንዴ?
  • አይደለም ይባላል።
  • እንዴት?
  • የሚመረቁት ፕሮጀክቶች አብዛኞቹ ያላለቁ ናቸውም ይባላል፡፡
  • ባያልቁስ? አገልግሎት ከጀመሩ ቢመረቁ ምን ችግር አለው? 
  • ችግር የለውም፣ ግን ድግሱ በዛ… እንዲሁም ያላለቁ ፕሮጀክቶች ብቻ አይደለም እየተመረቁ ያሉት ይባላል። 
  • ሌላ ምን ሊመረቅ ይችላል? 
  • የተመረቁትም በድጋሚ ይመረቃሉ ይባላል፡፡
  • ወቀሳ… ወቀሳ… ሌላ የሚባል ነገር የለም? 
  • ወቀሳው ትንሽ በዛ አይደል ክቡር ሚኒስትር?
  • መብዛት ብቻ ሳይሆን፣ ሚዛኑም የተዛባ ነው እንጂ፡፡
  • እንዴት? 
  • ምን እንዴት አለው? ለምሳሌ ረሃብ በኢትዮጵያ ብቻ የተከሰተ ነገር ነው? አይደለም፡፡
  • ልክ ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • አዎ፣ ረሃብ የትም አገር ሊኖር ይችላል፣ በዚህ ደረጃ የሚያስወቅስ አይደለም፣ በዚያ ላይ ወቀሳ ብቻ መሰንዘር ሳይሆን ምሉዕ ሥዕሉን ማየት ያስፈልጋል። 
  • ምኑን ነው ማየት? 
  • ምሉዕ ሥዕሉን… ወቀሳ ብቻ ሳይሆን የአገሪቱን አጠቃላይ ሁኔታ ማየት ያስፈልጋል፣ ረሃብ ብቻ ነው እንዴ ያለው?
  • እ…?
  • ጠግቦ የሚያድር የለም? ቁጥሩ ይነስም ይብዛ ጠግቦ የሚያድር አለ፣ አይደለም እንዴ?
  • እሱስ ልክ ነው፣ ይኖራል፡፡
  • ደግሞ ረሃብ ቢኖርም ዘንድሮ 25 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ሰብስበናል፡፡
  • ከውጭ ነው?
  • ለምን? እዚሁ አምርተን ነው እንጂ!
  • ኦዎ… ጥሩ ዜና ነው፣ አሁን ያለውን ችግር ለመቅረፍ ይደርሳል ብዬ አስባለሁ፡፡ 
  • አሁን ባይደርስ ለሚቀጥለው ጉባዔ ይደርሳል፡፡
  • ጉባዔ?… በልግ ማለትዎ ነው ክቡር ሚኒስትር?
  • ጉባዔ አልኩ እንዴ?
  • ለነገሩ አልተሳሳቱም… ሁለቱም በአንድ ወቅት ነው የሚውሉት፡፡
  • ልክ ነህ፣ የዘንድሮ ጉባዔያችንን ልዩ የሚያደርገው በበልግ ወቅት መካሄዱ ነው። 
  • ክቡር ሚኒስትር የጀመርነውን እንቀጥል?
  • ጥሩ፣ እንዳልኩህ ተቺዎቹ ፖለቲካዊ ግብ ለማስቆጠር ፈልገው ካልሆነ በስተቀር ወቀሳው ሚዛኑን የሳተ ነው፡፡
  • እንዴት?
  • እያስረዳሁህ አልነበረም እንዴ? ወይስ አልሰማኸኝም?
  • ስለ25 ሚሊዮን ኩንታል ያሉትን ሰምቻለሁ፣ ግን…
  • ለምን ግን ትላለህ? ግን አትበል…፡፡
  • እሺ፣ ግን ከስንዴ ውጪ ሌላ ማሳያም ማቅረብ ይቻላል?
  • ግን አትበል አልኩህ እኮ!… ግን የሚል ቃል አፍራሽ ነው፡፡ 
  • ጥሩ፣ ሌላ ምን ዓይነት ማሳያ ማቅረብ ይቻላል?
  • ስለሳተላይቷ። 
  • ስለምኗ?
  • ሳተላይቷ፡፡
  • እህህ…
  • እሷን ማምጠቅ በመቻላችን ብዙ ጥቅም ነው ያገኘነው። 
  • ምን አገኘን?
  • አንዱ ገጽታ ግንባታ ነው። 
  • ሌላውስ?
  • ሌላው ወደፊት ከጠፈር በምትልከው መረጃ የግብርና ዘርፉን ትደግፋለች፡፡ 
  • ክቡር ሚኒስትር የሳተላይቷ እንኳ ቢቀርብን ይሻላል…
  • ለምን? 
  • ወቀሳውን ለመከላከል የሚጠቅመን አልመሰለኝም፡፡
  • ለምን? እንዴት?
  • ተቺዎቻችን በእሷ ነገር እያብጠለጠሉን ነው፣ እንዲያውም ለእኛም ስያሜ ሰጥተውናል፡፡
  • ምን ብለው?
  • ሳተላይቷ!
  • በትችት መልክ? በአድናቆት?
  • ኧረ ትችት ነው ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ምን ለማለት ፈልገው ነው?
  • ሳተላይቷ ከላይ ተቀመጠች እንጂ የሠራችው ነገር የለም ለማለት ፈልገው ነው፡፡
  • ይህ እንኳ ረብ የለሽ ትችት ነው፡፡
  • እንዴት?
  • በሁለት ምክንያት! 
  • እሺ… አንዱ ምንድነው?
  • በአገራችን ሳተላይት ያመጠቀ መንግሥት ኖሮን ያውቃል?
  • አያውቅም፡፡
  • ረብ የለሽ ትችት የሚያደርገው አንዱ ምክንያት እሱ ነው።
  • እንዴት? 
  • ቢያንስ የመጀመሪያው መንግሥት እኛ ነን፣ ቀደም ሲል የነበሩት መንግሥታት ስለሳተላይት ማምጠቅ አስበው አያውቁም፣ እኛ በዚህ እንለያለን። 
  • ትችቱ እኮ ከቀደሙት መንግሥታት ጋር በማወዳደር የተሰነዘረ አይደለም። 
  • አስጨርሰኝ። 
  • እሺ፣ ይቀጥሉ…
  • ሁለተኛው ምክንያት ባለማወቅ የተሰነዘረ ትችት ነው።
  • እንዴት ማለት?
  • ሳተላይቷ የምትሰጠውን ጥቅም የማያውቁ የሰነዘሩብን ትችት ነው፣ የምትሰጠውን ጥቅም ቢያውቁ ኖሮ እንደዚያ አይሉንም ነበር።
  • ግን ጥቅም እየሰጠች ነው? 
  • ማንን ማለትህ ነው?
  • ሳተላይቷ?
  • እንዴት ጥቅም አትሰጥም? 
  • ጥቅም ትሰጥ ይሆናል፣ እኔ ግን የማውቀው ነገር የለም፡፡ 
  • አየህ… ባለማወቅ የተሰነዘረ ትችት ነው ያልኩህ ለዚህ ነው፣ አሁን ገባህ?
  • አልገባኝም፡፡ 
  • ጥቅሟን ማንም አያውቅማ… አንተም አታውቅም አይደል?
  • አዎ፣ ምንም መረጃ የለኝም፡፡ 
  • እኮ! አሁን ገባህ አይደል?
  • አዎ፣ ልክ ነው፣ ረብ የለሽ ትችት ነው!

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በዕድሳት ምክንያት የተዘጋው የአዲስ አበባ ስታዲየም በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል

  የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ በሚፈለገው ልክ እየተከናወነ እንዳልሆነ ተገልጿል ከስፖርታዊ...

  የንብረት ታክስ ጉዳይ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባዔ ቀዳሚ አጀንዳ ይሆናል ተባለ

  መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚጀምረው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን...

  የኢትዮጵያ ባንኮችን የማዋሃድ አስፈላጊነት ፍንትው ያደረገው ዓመታዊው የአፍሪካ ባንኮች የደረጃ ምዘና ሪፖርት

  የአፍሪካ ባንኮችን በየዓመቱ በመመዘንና ደረጃ በመስጠት የሚታወቀው አፍሪካ ቢዝነስ...

  መንግሥት ለሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎችና የመንግሥት ሠራተኞች ሥልጠና ለመስጠት ቃል ገባ

  የኢትዮጵያ መንግሥት ለጎረቤት አገር ሶማሊያ የመንግሥት ሠራተኞችና የፀጥታ አካላት...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች