በኢትዮጵያ ከ300 በላይ የበሽታ ዓይነቶችና ከ80 የሚበልጡ የጤና አጋላጭ መንሥዔዎች ላይ የተደረጉ ጥናቶችን የያዘ የጤና አትላስ ይፋ ሆነ።
በአትላሱ የጥናት ግኝቶች ሞትና ልደት፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ጉዳዮች፣ የትምህርት ደረጃ እንዲሁም ለሞት መንሥኤ የሆኑ የበሽታ ዓይነቶች ተካተውበታል። በተጨማሪ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችና የሰዎች አማካይ የመኖር ዕድሜ ጣሪያ በሚገባ ተጠንቶ አካትቶ መያዙን የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ከፍተኛ አማካሪና የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር አወቀ ምስጋናው (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ጥናቱን የመሩት የኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ መረጃ ማደራጃ ማዕከል አስተባባሪና ከፍተኛ አማካሪ እንደገለጹት፣ የጤናን መረጃ ለማግኘትና ለመለዋወጥ የሚያስችለው መመርያ የጤና መረጃን መጋራት፣ አሰጣጥና ቅብብሎሽን ለማሳለጥ ከፍተኛ የሆነ ዕገዛን ያበረክታል፡፡ የሕክምና አሠራር ባህልን ከፍ ያደርገዋል ተብሎ ይታሰባል፡፡
የጤና አትላሱ እ.ኤ.አ. ከ1990 እስከ 2019 በሁሉም ክልሎች፣ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች የተከሰቱ በሽታዎችን እና ሥርጭታቸውን ያሳያል፡፡
በኢትዮጵያ የጤናው ሥርዓት ታሪክ ውስጥ ፋና ወጊ እንደሆነ የተነገረለትና ለአምስት ዓመታት የተደረጉትን ጥናቶች ያካተተው ብሔራዊ የጤና አትላስ የወጣው መጋቢት 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ነው፡፡
በጥናቱ ከ800 በላይ የአገር ውስጥ ተመራማሪዎች መሳተፋቸውን፣ በዓለም ከፍተኛ ዕውቅና ባገኘውና ‹‹ላንሴት›› በተባለው ጆርናል እንደታተመ፣ ሕትመቱም በክልልና በአገር አቀፍ ደረጃ ለመጠቀም በሚያስችል መልክ ቀለል ተደርጎ መዘጋጀቱንም አስተባባሪው ገልጸዋል።
ከአንድ ሺሕ በላይ ከሚሆኑ ተቋማት ከተሰበሰቡ መረጃዎች ላይ የተሠራው የትንተና ውጤት የያዘው የጤና አትላስ በዋናነት አምስት ምዕራፎች እንዳሉት ገልጸው፣ ከእነዚህም መካከል የመጀመርያው ምዕራፍ ስለሞትና ስለውልደት የሚተነትን መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ይህም ማለት ባለፉት 30 ዓመታት በፆታ፣ በዕድሜና በሞት ዙሪያ ይካሄድ የነበረው አሠራር ምን እንደሚመስል ከማመላከቱም በላይ በጤናው ዘርፍ የሚታዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ማካተቱን ከከፍተኛ አማካሪ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡
ሁለተኛው ምዕራፍ ለሞት መንስዔ የሆኑ ከ300 በላይ በሽታዎችን እንዳካተተ፣ አካል ጉዳተኞችንና ሕሙማንን ማሰብ እንደሚያስፈልግና ሰው ታሞ አልጋ ላይ በመተኛቱና አካል ጉዳተኛም በመሆኑም የተነሳ የሚደረሰው ችግር ምን ያህል ሊሆን ይችላል የሚለውም ዝርዝር ሁኔታ የተካተተበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሦስተኛው ምዕራፍ የበሽታ አጋላጭ መንስዔዎች ምን ያህል ሞት አስከትሏል የሚለው የታየበት ሲሆን አማካይ የዕድሜ ስሌትንም ማካተቱን ተናግረዋል፡፡
በስሌቱም መሠረት በሐረሪ ክልል፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች አማካይ የዕድሜ ደረጃ ከ70 እስከ 77 ሲሆን፣ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች የሚታየው አማካይ የመኖር ዕድሜ ከ64 እስከ 65 ዓመት ሆኖ መቀመጡን፣ እንደነዚህ ዓይነቶቹ መረጃዎች ለልማትና ለጤና ሥራዎች ስኬታማነት ያላቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱን ነው የገለጹት፡፡
ይኼው ብሔራዊ አትላስ የተዘጋጀው በጤና ሚኒስትር፣ በኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ብሔራዊ የጤና መረጃ አስተዳደር ቅመራና ትንተና ማዕከል፣ በዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ኢንስቲትዩት ፎር ሄልዝ ሜትሪክስ ኤንድ ኢቫሉዌሽን ትብብር ሲሆን፣ ቢል ኤንድ ሚሊንዳ ጌት ፋውንዴሽን ደግሞ ለሥራው የሚያስፈልገው ፋይናንስ በመሸፈን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ረዳት ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡
በጤና ሚኒስቴር የፖሊሲ፣ ዕቅድ ክትትልና ምዘና ምክትል ዳይሬክተር አቶ መስዑድ መሐመድ፣ ‹‹በመደበኛው አካሄድ የሚወጡት መረጃዎች የጤናው አትላስ ከያዛቸው መረጃዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነትና ልዩነት ምን ያህል ነው የሚለውን ማየት በእጅጉ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ ልዩነቱ ከ15 በመቶ በላይ ከሆነ ይኼኛው መረጃ የጥራት ክፍተት አለበት ተብሎ እንደሚጠበቅና በአጠቃላይ የጤናው መረጃ የኅብረተሰቡን ፍላጎት በሚያሟላ መልኩ መዘጋጀት እንዳለበት ነው የተናገሩት፡፡
የኢትዮጰያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ተወካይ አሰፋ ደሬሳ (ዶ/ር) የጤናው ዘርፍ ብዙ የምርምር ጥናቶች እንደሚያስፈልገው፣ ለዚህም ዕውን መሆን ኢንስቲትዩቱ የተለያዩ ጥናትና ምርምር በማካሄድ ለዘርፉ ግብዓት ሊሆኑ የሚችሉ ሳይንሳዊ መረጃዎች በማመንጨት ረገድ የጎላ ሚና በመጫወት ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመጋቢት 5 ቀን ጀምሮ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እየተከበረ ያለው የጤና መረጃ ሳምንት መከበር ዋና ዓላማ በጤናው ዘርፍ ያሉ የመረጃ አያያዝ ሥርዓትን ማሻሻልና ከአጋር አካላት ጋር ያለውን ትብብር ለማጠናከር መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡