ዘንድሮ ለ18ኛ ጊዜ የሚካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ዓርብ መጋቢት 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ይጀመራል፡፡ በሻምፒዮናው የሚሳተፈው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ባለፈው ሰኞ በቤል ቪው ሆቴል ከተሸኘ በኋላ ወደ ሥፍራው አቅንቷል፡፡ ሻምፒዮናው እሑድ መጋቢት 11 ፍፃሜውን እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡
በሰርቢያ ቤልግሬድ በሚካሄደው የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና፣ ኢትዮጵያ በመካከለኛ ርቀት በ800 ሜትር፣ በ1,500 ሜትርና በ3,000 ሜትር ሴቶች፣ እንዲሁም በወንዶች በ1,500 ሜትርና በ3,000 ሜትር ትሳተፋለች፡፡
በሴቶች 800 ሜትር ሀብታም ዓለሙ (ተጋባዥ)፣ ፍሬሕይወት ዓለሙና ትዕግሥት ግርማ ሲሆኑ፣ በ1,500 ሜትር ጉዳፍ ፀጋይ (ተጋባዥ)፣ አክሱማዊት አምባዬና ሒሩት መሸሻ ናቸው፡፡ በ3,000 ሜትር በወንዶች ደግሞ ሳሙኤል ተፈራና ታደሰ ለሚ ሲሆኑ፣ በሴቶች ለምለም ኃይሉ፣ ዳዊት ሥዩምና እጅጋየሁ ታዬ ናቸው፡፡ በወንዶች ደግሞ ለሜቻ ግርማና ሰሎሞን ባረጋ (ተጋባዥ) እና በሪሁ አረጋዊ መሆናቸው ታውቋል፡፡
በሽኝት ሥነ ሥርዓት የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ መስፍን ቸርነትን ጨምሮ፣ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራቱ ቱሉና ሌሎች የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ዘንድሮ ለ17ኛ ጊዜ የምትሳተፍበት የዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና እ.ኤ.አ. ከ1985 ጀምሮ በሽፍን ስታዲየም በትራክና በሜዳ ተግባራት አትሌቶች በየሁለት ዓመቱ የሚሳተፉበት የውድድር ዓይነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ እስካሁን ባደረገችው ተሳትፎ 26 የወርቅ፣ ስምንት የብር፣ አሥር የነሐስ፣ በድምሩ በ44 ሜዳሊያዎች፣ በሻምፒዮናው የደረጃ ሰንጠረዥ ከቀዳሚዎቹ ተርታ ከአሜሪካና ከሩሲያ በመቀጠል ሦስተኛ ደረጃ ላይ መሆኗ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ 44ቱ ሜዳሊያዎች፣ በ11 ሴቶችና በ14 ወንዶች፣ የተገኙ መሆናቸውን ፌዴሬሽኑ ሻምዮናውን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ተመልክቷል፡፡
በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርካታ የወርቅ ሜዳሊያ ካስመዘገቡት አትሌቶች ገንዘቤ ዲባባ አምስት በማጥለቅ በቀዳሚነት ስትጠቀስ፣ መሠረት ደፋርና ኃይሌ ገብረ ሥላሴ አራት፣ አራት በማስመዝገብ በሻምፒዮናው ስማቸውን በወርቅ መዝገብ አስመዝግበዋል፡፡
መሠረት ደፋር በተለይ ከአራት ወርቅ ሌላ፣ ሁለት የብርና አንድ የነሐስ በድምሩ ሰባት ሜዳሊያዎችን አስመዝግባለች፡፡ ደረሰ መኮንን መሐመድ አማንና ዮሚፍ ቀጀልቻ ሁለት፣ ሁለት ወርቅ፣ ብርሃኔ አደሬ አንድ ወርቅና አንድ ብር፣ ገለቴ ቡርቃ አንድ ወርቅና ሁለት ነሐስ፣ ቁጥሬ ዱለቻ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ታሪኩ በቀለ፣ ቃልኪዳን ገዛኸኝ (በአሁኑ ወቅት ለባህሬን የምትሮጥ)፣ ሳሙኤል ተፈራ እያዳንዳቸው አንድ፣ አንድ የወርቅ ሜዳሊያ በስማቸው አስመዝግበዋል፡፡
በስማቸው አንድ፣ አንድ የብር ሜዳሊያ ካስመገቡ አትሌቶች መካከል መሰለች መልካሙ፣ አማን ወጤ፣ አክሱማዊት አምባዬ፣ ዳዊት ሥዩምና ሰለሞን ባረጋ ሲገኙበት፣ አንድ፣ አንድ የነሐስ ሜዳሊያ ያጠለቁት አትሌቶች ደግሞ ሚሊዮን ወልዴ፣ ማርቆስ ገነቴ፣ አብርሃም ጨርቆሴ፣ ስንታዬሁ እጅጉ፣ መኮንን ገብረ መድኅን፣ ደጀን ገብረ መስቀልና ጉዳፍ ፀጋይ መሆናቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡