Tuesday, March 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢዜማ ለአዲስ አበባ ፖሊስ መመልመል ያለበት ከከተማዋ ነዋሪዎች ብቻ መሆን እንዳለበት ተናገረ

ኢዜማ ለአዲስ አበባ ፖሊስ መመልመል ያለበት ከከተማዋ ነዋሪዎች ብቻ መሆን እንዳለበት ተናገረ

ቀን:

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አዳዲስ አባላትን ለመመልመል የሚሄድበት አካሄድ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዘነ ስለሆነ፣ የከተማው ፖሊስ ኃይል ከከተማው በተወጣጡ ዜጎች እንዲጠናከር መደረግ እንዳለበት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) ጥያቄ አቀረበ፡፡

ባለፈው ሳምንት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በከተማ ውስጥ ያለውን የነዋሪ ቁጥርና የፖሊስ ኃይል ምጥጥን ለማስተካከል፣ የከተማዋን ፖሊስ ቁጥር ወደ 50 ሺሕ ለማሳደግ መታቀዱን አስታውቆ ነበር፡፡ ኮሚሽኑ አክሎም የፖሊስ ኃይሉን ቁጥር ለማሳደግ ከትግራይ ክልል ውጪ በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች መልማዮችን መላኩን ገልጾ ነበር፡፡

ኢዜማ በሳምንቱ መጨረሻ ባወጣው ወቅታዊ የጋዜጣዊ መግለጫ፣ በከተማዋ ውስጥ ያለውን የነዋሪ ቁጥርና የፖሊስ ኃይል ምጥጥን ለማስተካከል በሁሉም ክልሎች መልማዮች መላካቸው የከተማዋን ነዋሪዎች መበት የሚፃረር ነው ብሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማን በዋናነት በፖሊስነት የሚጠብቋት ዘቦች የከተማዋ ነዋሪዎች መሆን ይኖርባቸዋል ያለው ፓርቲው፣ የከተማዋን ሁሉን አካታችነት ተገን በማድረግ ከሌሎች አካባቢዎች ፖሊሶችን መመልመል ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን አስታውቋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በሙሉ የከተማዋ ባለቤቶችና ባለመብቶች ሲሆኑ ከተማዋን የማስተዳደርና በፀጥታ ዘርፍ ተሰማርቶ መጠበቅ የከተማዋ ነዋሪ ኃላፊነት ነው ያለው ኢዜማ በመሆኑም የከተማዋ ፖሊስ ከከተማዋ በተውጣጡ ዜጎች እንዲጠናከር ጥያቄ አቅርቧል፡፡

 የኢዜማ የአዲስ አበባ ምርጫ ዘመቻ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ አማንይሁን ረዳ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ፓርቲው ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ ከሕግና መርህ ውጪ የሆነ አሠራር ሲኖር፣ ‹‹ትክክል አይደለም›› በማለት ሐሳቡን ያንፀባርቃል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የፖሊስ ምልመላ ሒደቱን ከዚህም ቀደም ሲሠራበት እንደቆየ ቢያሳውቅም፣ ከዚህ በፊት የነበረ አሠራር ነው ተብሎ መታለፍ እንደሌለበትና ስህተትም ከሆነ ስህተትነቱ ከግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከሕዝብ ቁጥር አንፃር የፖሊስ ቁጥርን ለማመጣጠን የሚያደርገው ሥራ ትክለለኛ አካሄድ ነው ያሉት አቶ አማንይሁን፣ ይህም በከተማዋ ውስጥ ከዕለት ወደ ዕለት እየተበራከተ ያለውን ወንጀል ለመቀነስ የፀጥታ ኃይልን ማጠናከር ተገቢና አስፈላጊ አጀንዳ ሆኖ በመገኘቱ ነው ብለው፣ ነገር ግን የፀጥታ ኃይሉን ለማጠናከር ተብሎ የሚደረገው የምልመላ ሒደት ተቀባይነት እንደሌለው ተናግረዋል፡፡

የፀጥታ ኃይሉን ከተለያዩ አካባቢዎች ለመመልምል የሚደረገው እንቅስቃሴ በቀጥታ ራስን በራስ ከማስተዳደር ጋር የሚገናኝን መብት የሚፃረር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከተማዋ ራሷን በራሷ የምታስተዳድር መሆን እንደሚገባት፣ አስተዳዳሪዎቹም ከሌላ ቦታ መጥተው ማስተዳደር እንደሌለባቸው ሁሉ፣ በፖሊስ መዋቅር ውስጥ ሆነው ሰላም ለማስጠበቅ የሚመለመሉ ዜጎችም ሊመለመሉ የሚገባው ከአዲስ አበባ ሊሆን እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡

‹‹የከተማዋ ወጣት በተደጋጋሚ ከተማውን ለመጠበቅ ፈቃደኛ አይደለም ተብሎ ቢነገርም፣ አገር ጭንቅ ውስጥ በገባችበት ወቅት 120 ሺሕ በላይ የከተማዋ ነዋሪዎች ከተማቸውን ሲጠብቁ እንደከረሙ ይታወሳል፤›› ያሉት አቶ አማንይሁን፣ ‹‹ከእነዚህ ወጣቶች ሥራ የሌላቸው በርካታ በመሆናቸው ከነዋሪዎች መካከል ብቃትና ፍላጎት ያላቸው ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የከተማውን ፖሊስ እንዲቀላቀሉ ማድረግ ይቻላል፤›› ብለዋል፡፡

በሌሎች ከተሞች ላይ የማይደረግ የምልመላ ሥርዓት በአዲስ አበባ የሚደረግበት አሠራር ግር የሚያሰኝ እንደሆነ ገልጸው፣ በከተማዋ ይህንን ኃላፊነት መወጣት የሚገባቸው የከተማዋን ባህል፣ ሥነ ልቦናና አጠቃላይ ሁኔታ የሚረዱ መሆን አለባቸው ብለዋል፡፡

ለባህር ዳር፣ ለጅግጅጋ ወይም ለአሶሳ ከተሞች ከሌሎች ክልሎች የፖሊስ ምልመላ እንደማይደረገው ሁሉ አዲስ አበባ ላይ የተለየ የምልመላ ሥርዓት ሊኖር እንደማይገባ አቶ አማንይሁን ተናግረዋል፡፡

ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ አካል የሕዝቡን ሰላም የሚያውኩና እረፍት የሚነሱ ተደጋጋሚ ትንኮሳዎች ሊቆሙ ይገባል ያሉት አቶ አማንይሁን፣ በመሆኑም ጭቅጭቅ የሚፈጥሩ ጉዳዮችን ማንሸራሸር ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሌሎች የክልል ከተሞች ከሥራ አስፈጻሚዎች አንስቶ የፀጥታ ኃይል ከአካባቢው በተወጣጡ ዜጎች እንደሚዋቀር ይታወቃል ያሉት አቶ አማንይሁን፣ የአዲስ አበባ ሕዝብ ሰላምና ደኅንነቱን መጠበቅ ያልቻለ ይመስል ከሌላ የኢትዮጵያ ክፍል ሰላምና ፀጥታ የሚያስጠብቅ የደኅንነት መዋቅር መመልመል የከተማውን ሕዝብ የሥራ ዕድል እንደ መንፈግ ተደርጎ ይወሰዳል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ፖሊስ ብቻም ሳይሆን በከተማው ሥር ካሉ የፍትህ ተቋማት ጋር ተያይዞ የሚደረገው ነገር ተመሳሳይ ጉዳይ እንደሆነ ያስረዱት የፓርቲው አባል፣ በሕግ በተቀመጠው መሠረት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራስን በራስ የማስተዳደር በተመለከተ የሚገኙ ሙሉ መብቶች መሸርሸር የለባቸውም ብለዋል፡፡

በርካታ ሥራ አጥ ባለበት ከተማ ውስጥ ከምልመላ ጋር ተያይዞና መሰል ተግባራትን መፈጸም፣ እነዚህ የከተማዋ ዜጎች የሥራ ዕድል መንፈግና ባይተዋር ማድረግ እንደሆነ ያስታወቁት የኢዜማ አባሉ፣ ከዚህ ባሻገርም የከተማውን ነዋሪ በከተማ አስተዳደሩ ውስጥ በንቃት እንዳይሳተፍ ማድረግ ጭምር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ የሚመለመሉ የፀጥታ አካላት የከተማዋን ነዋሪዎች መብትና ጥቅም ከማስጠበቅ ይልቅ የመጡበትን አካባቢና ብሔር እናስከብራለን ወደሚል፣ እንዲሁም የከተማውን ነዋሪን ክብር እስከ መንካት የሚያደርስ ክስተተ እንዲፈጠር ምክንያት እንደሚሆኑም አስረድተዋል፡፡

‹‹የከተማው ሕዝብ አገሪቱን ተሸክሞ ብዙ አስተዋፅኦ እያደረገ የሚገኝ የተከበረ ሕዝብ ነው፡፡ ይህንን ሕዝብ በማክበር የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎቹም ሊመለሱለት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...