Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ የመሸጥ ኃላፊነት ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ተላለፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የጨረታ ሒደቱ ተቋርጦ ለሌላ ጊዜ ተላልፏል

የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ለውጭ ኩባንያዎች ለመሸጥ የተያዘው ዕቅድ፣ በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ለተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ መተላለፉ ታወቀ። 

የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለውጭ የቴሌኮም ኩባንያ የማስተላለፍ ሒደት፣ በገንዘብ ሚኒስቴርና በእሱ ሥር በተደራጀው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ሲመራ የነበረ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ የቴሌኮም ኩባንያውን ድርሻ ለመሸጥ በመስከረም 2014 ዓ.ም. ወጥቶ የነበረው ጨረታ እንዲቋረጥ መንግሥት ውሳኔ አሳልፏል።

የገንዘብ ሚኒስቴር ዓርብ መጋቢት 9 ቀን 2014 .. ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ የወጣው ጨረታ ተቋርጦ አጠቃላይ ሒደቱ ወደ ሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ መወሰኑን አስታውቋል።

መንግሥት ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው በኢትዮጵያም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየታዩ ባሉ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ለውጦች ምክንያት እንደሆነ መግለጫው ጠቁሟል።

በፍጥነት እየተለወጠ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታ፣ እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያዳገ የሚገኘውን የኢትዮ ቴሌኮም የፋይናንስ አፈጻጸም ጊዜ ወስዶ ማስተናገድ የተሻለ ዋጋ የሚያስገኝ መሆኑን መንግሥት እንዳመነበት መግለጫው ያመለክታል።

በመሆኑም ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ለመሸጥ የወጣውን ጨረታ በማቋረጥ እየታዩ ያሉ መፃኢ መልካም ዕድሎች ተካተው፣ ወደፊት ሒደቱ በድጋሚ እንዲቀጥል ማድረግ የተሻለ ዋጋ እንደሚያስገኝይህም ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት በተለይም ለኢትዮጵያውያን ጠቃሚ እንደሚሆን መንግሥት እንዳመነበት መግለጫው አስታውቋል።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት የፕራይቬታይዜሽን ሒደቱን ለማጠናቀቅ ቁርጠኛ መሆኑን፣ ኩባንያውን ለመግዛት ፍላጎት ያሳዩ ነባርና ተጨማሪ አካላትን ወደፊት በድጋሚ የማሳተፍ ፍላጎት እንዳለው አስታውቋል።

ይህንን የመንግሥት ውሳኔ አስመልክቶ ለሪፖርተር መረጃ የሰጡ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊ፣ ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ለመሸጥ የተጀመረው የጨረታ ሒደት እንዲቋረጥ ምክንያት ናቸው ተብለው የተገለጹት አመክንዮዎች ትክክለኛ መሆናቸውን ገልጸውበዋናነት መንግሥት የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ሽያጭም ሆነ አጠቃላይ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ፕራይቬታይዜሽን በተመለከ አዲስ ሥልት ለመከተል መወሰኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻየኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ ኃላፊነት የተሰጠው ለመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ የነበረ ቢሆንምለኤጀንሲው የተሰጠው ይህ ኃላፊነት ቀሪ ሆኖ በምትኩ የሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ ታኀሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ባፀደቀው ደንብ መሠረት ለተቋቋመውኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ መተላለፉን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ የመሸጥ ኃላፊነት እንደ አዲስ ለተመሠረተው ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ መተላለፉን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ የኢትዮ ቴሌኮምን ከፊል ድርሻ ለመሸጥ የተጀመረውን ሒደት ከተቋረጠበት የማስቀጠልም ሆነ፣ እንደ አዲስ የሽያጭ ሒደቱን የማስጀመር ኃላፊነት እንደተሰጠው ገልጸዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም 40 በመቶ ድርሻ የመሸጥ ሒደትን የመምራት ብቻ ሳይሆን፣ የታቀደውን 40 በመቶ ድርሻ ሽያጭ ማስቀረት ወይም መከለስ ለሆልዲንግ ኩባንያው የተሰጠ ኃላፊነት መሆኑንም ተናግረዋል።

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ የተጠየቁት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶብታሙ ኃይለ ሚካኤልከዚህ በኋላ የሚኖረው የኤጀንሲው ዋና ኃላፊነት ከድኀረ ፕራይቬታይዜሽን ጋር የተገናኘ እንደሚሆን ጠቁመዋል። ኢትዮ ቴሌኮምን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ መስጠት የሚችለው የገንዘብ ሚኒስቴር መሆኑን በመጠቆም፣ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል። ሪፖርተር ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የገንዘብ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉት ከፍተኛ ባለሥልጣን ግን በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ የሆልዲንግ ኩባንያው ኃላፊነት በኢትዮ ቴሌኮም ከፊል ሽያጭ ላይ የሚወሰን አለመሆኑንከዚህ በኋላ በአጠቃላይ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችን የመሸጥም ሆነ የማፍረስ፣ እንዲሁም የማዋሀድ ኃላፊነት የዚህ ኩባንያ እንደሆነ ጠቁመዋል። 

በመንግሥት ልማት ድርጆቶች ውስጥ የሚገኝን የመንግሥት የአክሲዮን ድርሻ ከመሸጥና ከማስተላለፍ በተጨማሪ፣ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ የግል አልሚዎች ጋር የሽርክና ድርጅት የመመሥረትና የጋራ የኢንቨስትመንት ኩባንያ የማቋቋም መብት እንደተሰጠውም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ተጠሪነቱ በቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ሕፈት ቤት ሲሆን፣ የቦርድ ሰብሳቢውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሆኑና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚሾሙ ስድስት የቦርድ አባላት እንደሚኖሩትም ታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅርቡ በሰጡት ሹመትም የዓለም ንግድ ድርጅት ዋና ተደራዳሪና የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ማሞ ምሕረቱ (/)፣ የመጀመሪያው ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተሹመዋል። 

በአገሪቱ የሚገኙ የመንግሥት ልማት ድርጅቶችሆልዲንግ ኩባንያው ሥር የሚገኙ ተቀጥላ ተቋማት ሆነው በተቋቋሙበት መንገድ የሚቀጥሉ መሆኑንሆልዲንግ ኩባንያው የንግድ እንቅሰቃሴያቸውን የማዘመን፣ ትርፋማ ሆነው እንዲቀጥሉ የመከታተልና፣ የተቀጥላ ተቋማቱን አመራሮች የመሾምና የማንሳት ኃላፊት እንዳለው ለመረዳት ተችሏል።

ሆልዲንግ ኩባንያው በዋናነት የሚመለከተው በመንግሥት ልማት ድርጅቶች ውስጥ ያለውን የመንግሥት ሀብትና የኢንቨስትመንት ድርሻ ማስተዳደር ብቻ እንደሆነ የገለጹት ኃላፊው፣ ከዚህ ውጪ የመንግሥት ልማት ድርጅቶቹን አጠቃላይ እንቅስቃሴና አስተዳደር በራሳቸው በተቋማቱና በመንግሥት ልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ሥር እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ነገር ግን በመንግሥት ልማት ድርጅቶቹ ላይ ያለውን የመንግሥት ሀብት በተሻለ ሁኔታ ለማስተዳደር፣ ትርፋማ ለማድረግ፣ ወይም ወደ ሌላ ሀብት ቢቀየር የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እንደሚኖረው ካመነ አንድ የመንግሥት የልማት ድርጅት ከሌላ ጋር እንዲዋሀድ ወይም እንዲፈርስ፣ ወይም በከፊል አልያም ሙሉ በሙሉ እንዲሸጥ ወይም በአንድ የመንግሥት ልማት ድርጅት ውስጥ ያለ ቁሳዊ ሀብት ሕንፃን ጨምሮ እንዲሸጥ፣ ሊወስን እንደሚችል አስረድተዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ታኅሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. የሆልዲንግ ኩባንያውን ማቋቋሚያ ደንብ ካፀደቀ በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ ኩባንያው እንዲቋቋም የተፈለገበትን ምክንያት ገልጿል። 

በዚህ መግለጫውም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ የተቋቋመበት ዓላማ በአገሪቱ ውስጥ ያሉ በርካታ የመንግሥት ሀብቶችን ወደ አንድ ተቋም በመሰብሰብና ውጤታማ የአስተዳደር ሥርዓት በመፍጠር፣ ከእነዚህ ሀብቶች የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በከፍተኛ ደረጃ በማሻሻልና ሀብቶቹን አሟጦ በመጠቀም የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትና ተወዳዳሪነት የሚያሳድግ ስትራቴጂካዊ የልማትና የኢንቨስትመንት መሣሪያ ለማድረግ መሆኑን አስታውቋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች