Friday, March 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ከመንግሥት ሹማምንት የሚፈለገው ሕግ ማክበር ብቻ ነው!

የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ጉባዔ ለተመረጡት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በሰጡት ማብራሪያ፣ አባላቱ በአራት ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ መናገራቸው ይታወሳል፡፡ እነሱም ሕግ፣ ታሪክ፣ ህሊና፣ እንዲሁም ፈጣሪ ናቸው፡፡ የገዥው ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በፌዴራልና በተለያዩ ክልሎች ውስጥ በኃላፊነት ወንበር ላይ የሚቀመጡ በመሆናቸው፣ ደግሞ ደጋግሞ ሕግ እንዲያከብሩ ማሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ በመንግሥት ሥልጣን ላይ የሚቀመጥ ማንም ሰው (ሁለቱንም ፆታዎች ይወክላል) ከምንም ነገር በፊት ሰላማዊና ሕግ አክባሪ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ይኸው ሰው ለተሰጠው ኃላፊነት ግልጽነትና ተጠያቂነት ሊኖርበት ይገባል፡፡ ሥራውን ሲያከናውን ከብሔር፣ ከእምነት፣ ከፆታ፣ ከቋንቋ፣ ከባህል፣ ከፖለቲካ አቋምና ከመሳሰሉ መድሎዎች የፀዳ መሆኑን በተግባር ማሳየት ይኖርበታል፡፡ ለተሰጠው ኃላፊነት የሚመጥን የትምህርት ዝግጅት፣ ብቃትና ሥነ ምግባርም መላበስ አለበት፡፡ በግሉ የሚከተለው ሃይማኖት፣ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም፣ የኑሮ ዝንባሌ ወይም የሕይወት ፍልስፍና ሊኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን የመንግሥት ኃላፊነት ሲቀበል ደግሞ ግራና ቀኝ ከሚጎትቱት ስሜቶች ራሱን ነፃ ማውጣት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ቁመና ላይ ሳይገኙ ሥልጣን ላይ መውጣት ተገቢ አይደለም፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ከመጠን በላይ እየተስፋፋ ያለው ፅንፈኝነት የመንግሥት ተቋማትን እየተገዳደረ ነው፡፡ ጠንካራና ራሷን በሁሉም መስኮች የቻለች አገር ለመገንባት ከሚጣጣሩ ይልቅ፣ በመንደርተኝነት አስተሳሰብ እያደር ቁልቁል የሚንደረደሩ ሹማምንት ማየት ከተለመደ ቆይቷል፡፡ ኢትዮጵያ ማለት እየተረሳ ብሔሬ፣ ክልሌ፣ ዞኔ፣ ወረዳዬ፣ ሠፈሬና ጎጤ የሚሉ ፅንፈኞች ተበራክተዋል፡፡ በትልቋ ኢትዮጵያ ማዕቀፍ ውስጥ ክልልንም ሆነ ጎጥን ማሳደግ እየተቻለ፣ ለሕዝብ ፋይዳ ለማይኖረው ፍላጎት ሲባል ቁልቁል መውረድ ፋሽን ሆኗል፡፡ በዚህ ዘመን ትውልዱንና ራስን የሚያስከብር ታሪክ መሥራት ሲገባ፣ ወደኋላ ዘመን እየተንሸራተቱ በሙታን መንፈስ ላይ መነታረክ የዕለት ተግባር መሆኑ ያሳዝናል፡፡ በዚህ ዓይነቱ መናኛ ተግባር ውስጥ የገዥውን ፓርቲና የመንግሥትን ሹመት ደራርበው የያዙ ሰዎች መገኘታቸው፣ ለዚህ ትውልድም ሆነ ለመጪው ጭምር የሚያሳፍር ታሪክ ነው፡፡ በልዩነት ውስጥ አማካይ ሥፍራ ፈልጎ አገርን ከአሳፋሪው ተመፅዋችነት ማላቀቅ የማይችል ፅንፈኝነት ውስጥ መዳከር፣ ለጊዜው ይምሰል እንጂ አንገት የሚያስደፋ አሳፋሪ ድርጊት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ በብሔርና በእምነት በማለያየት አገር ለማፍረስ ማድባት፣ የፓርቲም ሆነ የመንግሥት ኃላፊነት ከተቀበሉ ሰዎች የማይጠበቅ ወራዳ ድርጊት መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ 

ሌላው ከፓርቲና ከመንግሥት ሹማምንት መሀል ከደረጃቸው ወርደው የሚገኙ ቁጥራቸው እየጨመረ ነው፡፡ የማይገባቸውን ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ብቻ ባለሀብት ተብዬዎች ሥር የሚርመጠመጡ ሹማምንት፣ ለዚህች የተከበረችና የታፈረች አገር የማይመጥኑ ስለሆኑ መላ ሊፈለግላቸው ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ለኃላፊነት የማይመጥኑ ሰዎች ውሎአቸውን ከደላሎችና በአቋራጭ ለመክበር እንቅልፍ አጥተው ከሚያድሩ ባለሀብት ተብዬዎች ጋር ሲያደርጉ፣ አገርና ሕዝብ ከማሳፈራቸውም በላይ ከእነሱ ብዙ እጠብቃለሁ የሚለውን ፓርቲም እያስገመቱ መሆናቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡ በዚህች አገር ውስጥ ከሚፈጸሙ ሕገወጥ ድርጊቶች መካከል የመሬት ወረራ፣ የግብርና የቀረጥ ሥወራ፣ ያለ ጨረታ ፕሮጀክቶችን መስጠት፣ ከመንግሥት መመርያ ውጪ ግዥዎችን ማከናወን፣ ከቀረጥ ነፃ ዕድሎችን ለማይገባቸው ማደል፣ የባንክ ብድሮችና የውጭ ምንዛሪ በትውውቅ መልቀቅና ሌሎች እኩይ ድርጊቶች የሚከናወኑት ከደላሎች ጋር በመመሳጠርና ከባለሀብት ተብዬዎች ጋር በመወዳጀት ነው፡፡ እዚህ ላይ አስገራሚው ነገር ራሳቸውን ከእንዲህ ዓይነት አሳፋሪ ድርጊቶች ያራቁ ሰዎች፣ ለምን በሕገወጥነት የተዘፈቁትን እንደማያጋልጡ ነው፡፡ ብዙዎቹ የጥፋት አቀናባሪዎች ስማቸው በአደባባይ በስፋት እየተነሳ፣ የፓርቲም ሆነ የመንግሥት ዋና ሹማምንት ዝም ሲሉም ያስደንቃል፡፡

በፌዴራልም ሆነ በክልሎች ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት የፅንፈኞች ጥቃቶች ሰለባ ሲሆኑ፣ ከጥቃቶቹ በስተጀርባ ያሉ ቱባ ሹማምንትና ተከታዮቻቸው ማንነት እየታወቀም “አለባብሶ ማረስ” እየተለመደ ነው፡፡ ሕግን፣ ታሪክን፣ ህሊናን፣ እንዲሁም ፈጣሪን መፍራት መልካም ቢሆንም፣ ሥልጣን ላይ የሚወጡ ሰዎች የመንግሥትና የፓርቲ ሥራ ሳያደባልቁ ሕግ አክብረው ኃላፊነታቸውን ከተወጡ በቂ ነው፡፡ መንግሥት በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ሕግ ማስከበር ሲያቅተው፣ ፓርቲም በሕገ ደንቡ መሠረት አባላቱን ማረም ወይም መቅጣት ሲሳነው፣ ዜጎች ዕንባቸውን እያዘሩ የፍትሕ ያለህ ሲሉ አዳማጭ ሲጠፋና በአጠቃላይ ሕገወጥነት በየቦታው ተስፋፍቶ መንቀሳቀስ ሲያስቸግር በአገር ላይ ምፅዓት መቃረቡን መረዳት ይገባል፡፡ ሕግ ማክበርና ማስከበር ተቀዳሚ ኃላፊነታቸው የሆኑ ሹማምንት ድብቅ ዓላማ ያላቸው ይመስል አደገኛ ድርጊት ውስጥ ሲገኙ፣ ይህንን አገር አጥፊ ዓላማ ማጋለጥ የሚገባቸው ሌሎች ዓይተው እንዳላዩ ሲሆኑ አደጋው ግዙፍ ነው፡፡ በፓርቲም ሆነ በመንግሥት ኃላፊነት ላይ የተቀመጡ ግለሰቦች ራሳቸውን ከሕግ በታች አድርገው፣ አገርን ለሚያሻግር ታሪካዊ ተግባር ራሳቸውን ካላዘጋጁ በአደባባይ የሚሰበከው ሁሉ ተረት ይሆናል፡፡ ለታይታ የሚደረግ ዲስኩርና መውረግረግ ፋይዳ የለውም፡፡

እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚያስፈልገው ገዥው ብልፅግና ፓርቲ የውስጥ ጉዳዩ እንዳለ ሆኖ፣ ነገር ግን የአገሪቱን መንግሥት እስከ መራ ድረስ ሹማምንቱ ለመሪነት የሚመጥን ቁመና ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በዚህም መሠረት ኢትዮጵያ ያወጣቻቸውንና ተቀብላ ያፀደቀቻቸውን ዓለም ሕጎች ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡ ሕጎቹ ሥራ ላይ መዋላቸውንም ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ ተቀዳሚ ተግባራቸውም የኢትዮጵያን ሕዝብ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ማስከበር፣ የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ነው፡፡ ኃላፊነት የተቀበሉባቸው ተቋማት የፓርቲ ሥራ ማስፈጸሚያ ሳይሆኑ ሕዝባዊ አገልግሎት የሚሰጡ መሆን አለባቸው፡፡ ተቋማቱ በነፃነት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ዘመኑ ከደረሰበት ሥልጣኔ አኳያ ተደራጅተው፣ ነፃነታቸውና ገለልተኝነታቸው በተግባር መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ በሠለጠነ የሰው ኃይል፣ በተለያዩ ቁሳቁሶችና በቴክኖሎጂ ተደግፈው ብቁ አመራር ማግኘትም አለባቸው፡፡ ከሌብነት፣ ከአድልኦ፣ ከሕገወጥነት፣ ከሥርዓተ አልበኝነትና ከመሰል አስነዋሪ ድርጊቶች መፅዳት ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ ደረጃ ላይ ሊገኙ የማይችሉ ተቋማትን ይዞ አገር መምራት አይቻልም፡፡ በፅንፈኛ አስተሳሰብ ተጀቡኖ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አስተዋጽኦ ማበርከት አይታሰብም፡፡ በአደባባይ ኢትዮጵያዊነትን በአፍ እየዘመሩ፣ ከበስተጀርባ ሴራ በማጠንጠን ወደፊት መራመድ አይሞከርም፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርቲያቸውን አመራሮች ሕግን፣ ታሪክን፣ ህሊናቸውንና ፈጣሪን እንዲፈሩ ሲያሳስቡ፣ በፍትሕ ዕጦት የሚሰቃየው ሕዝብ ደግሞ የመንግሥት ሹማምንት ሕግ ካከበሩለት በቂ እንደሆነ በተለያዩ መንገዶች እየተናገረ ነው፡፡ በገዛ አገራቸው በማንነታቸው ምክንያት እንደ አውሬ እየታደኑ የሚገደሉ ወገኖች የመጀመሪያ ጥሪያቸው “በሕግ አምላክ” ስለሆነ ሕግ ይከበር፡፡ በገዛ አገራቸው በፈለጉት ሥፍራ ተዘዋውረው መሥራት፣ መኖርና ሀብት ማፍራት ያልቻሉ ዜጎች ልመናቸው ሕጋዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው ነው፡፡ በሚኖሩበት አካባቢ በብሔራቸው ምክንያት እንደ መጤ የሚታዩ ኢትዮጵያውያን ማሳሰቢያ፣ በእኩልነት መኖርና በሕግ ፊት እኩል መሆን ነው፡፡ በዚህ ዘመን የብዙዎች አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሥጋት፣ በፅንፈኛ ብሔርተኞች ምክንያት አገራቸው ፈራርሳ ለዕልቂትና ለስደት እንዳይዳረጉ ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን የተቆናጠጡ ግለሰቦችም በዚህን ያህል መጠን ለአገር ማሰብ ከተሳናቸው፣ የእነሱ ሕዝብና አገር መሪነት ፋይዳው ምንድነው መባል አለበት፡፡ ሁልጊዜ የሕዝብ አቤቱታ፣ ቅሬታ፣ እሮሮና ዋይታ ከሚቀድማቸው ይልቅ እነሱ ቀድመው መፍትሔ አመንጪ ሊሆኑ ይገባ ነበር፡፡ ነገር ግን ቀድመው መገኘት ስላልቻሉ አገርና ሕዝብ እየተሰቃዩ ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ አሳሳቢ ጊዜ ከመንግሥት ሹማምንት የሚፈለገው ሕግ ማክበር ብቻ እንደሆነ ይታወቅ!     

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

አሜሪካ ሕወሓትን በማሳመንና በመጫን በሰላም ሒደቱ ትልቅ ሚና መጫወቷን የኢትዮጵያ ዋና ተደራዳሪ አስታወቁ

የተመድና የአውሮፓ ኅብረት አበርክቶ አሉታዊ እንደነበር ጠቁመዋል በመንግሥትና በሕወሓት መካከል...

መንበሩ ካለመወረሱ በስተቀር መፈንቅለ ሲኖዶስ መደረጉን ቤተ ክህነት አስታወቀ

ቅዱስ ሲኖዶስ ከነገ ጀምሮ ውይይት እንደሚጀምር ተነገረ ‹‹እኛ ወታደርም ሆነ...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ኩባንያ አስተዳደር ለኢትዮጵያ ባንኮች ውጤታማነት

የጠቅላላ ጉባኤ፣ የጥቆማና ምርጫ ኮሚቴ፣ የተቆጣጣሪ ቦርድ፣ የዳይሬክተሮች ቦርድና...

ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አቶ ጌታቸው ረዳን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አድርገው ሾሙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ(ዶ/ር) አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የምግብ ችግር ድህነቱን ይበልጥ እያባባሰው ነው!

በአገር ውስጥና በውጭ የተለያዩ ተቋማት የሚወጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ከ22 ሚሊዮን በላይ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡ እነዚህ ወገኖች በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣...

መብትና ነፃነትን የሚጋፉ ድርጊቶች ይወገዱ!

ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የመዘዋወር፣ የመኖር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት ሕጋዊ መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት በግልጽ የተደነገገው በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት ሲሆን፣ አሁንም ሕገ...

የዜጎች ሰላምና ደኅንነት አስተማማኝ ጥበቃ ያስፈልገዋል!

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደው ዘግናኝና አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ቢገታም፣ በተለያዩ አካባቢዎች አሁንም የዜጎች ሰቆቃዎች በስፋት ይሰማሉ፡፡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር...