በጦርነት እየታመሰች በምትገኘው የምሥራቅ አውሮፓዋ አገር ዩክሬን ውስጥ ስለሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ መንግሥት ግልጽ የሆነ መረጃ እንደሌለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) ሐሙስ መጋቢት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ፣ ‹‹በምሥራቅ አውሮፓ አገሮች ያሉ የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች ክትትል ያደርጋሉ ከሚባለው ውጪ፣ በተጨባጭ ምን ያህል ኢትዮጵያውን በየት በኩል በምን ሁኔታ ገቡ ወይም ወጡ የሚል መረጃ የለንም፤›› ብለዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት የተለያዩ አገሮች ዜጎች ከዩክሬን ለቀው ለመውጣት በሚሞክሩበት ወቅት፣ የዩክሬንና የፖላንድ የፀጥታ ኃይሎች በተለይም አፍሪካዊያንን በቆዳ ቀለም በመለየት የተለያዩ ጥቃቶችና መጉላላቶች እያደረሱባቸው መሆኑን ከሥፍራው የሚወጡ ሪፖርቶች ያመላክታሉ፡፡
በዩክሬን በትምህርት ላይ የሚገኙ ዜጎች ያሏቸው የአፍሪካ አገሮች ዜጎቻቸውን በተለያዩ መንገዶች ከአካባቢው እያወጡ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር ወ/ሮ ሙሉ ሰለሞን ከሳምንት በፊት ለአገር ውስጥ ሚዲያ በሰጡት ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያውያንን በፖላንድ ድንበር በኩል ኤምባሲያቸው ለማስወጣት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸው ነበር፡፡
በተመሳሳይ ዜና በሳዑዲ ዓረቢያ በእስር ቤቶችና በመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ከሚገኙ ከ100 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን መሀል፣ 35 ሺሕ ያህሉ ወደ አገር ቤት ለመመለስ መመዝገባቸውን ቃል አቀባዩ አስታውቀዋል፡፡
የተመዘገቡትን ዜጎች ወደ አገር ቤት ለመመለስ በሚደረገው ጥረት፣ የተቀሩትን ማንነት የማጣራት ሥራ አብሮ እንደሚከናወን አክለው ገልጸዋል፡፡
በቅርቡ የአምባሳደርነት ሹመት የተሰጣቸው ተሿሚዎች የተመደቡባቸው አገሮች ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ፣ አሜሪካ፣ ኬንያ፣ ግብፅ፣ ሩዋንዳ፣ ፖኪሲታን፣ ኳታር፣ ሞሮኮ፣ አውስትራሊያ፣ ስዊድን፣ ኤርትራ የሚገኙበት ሲሆን፣ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ በሆኑ አምባሳደሮች እንዲመሩ የሚደረጉ አገሮች ብራዚልና ኩባ፣ ኮትዲቯር፣ ኢንዶኔዥያ፣ ዚምባብዌ ናቸው ተብሏል፡፡
ለጋና፣ ለጀርመን፣ ለህንድ፣ ለኒውዮርክ፣ ለዋሽንግተን፣ ለቤልጅየም፣ ለኬንያ፣ ለእንግሊዝ፣ ለፓኪስታን ምክትል የሚሲዮን መሪ ሲመደበላቸው፣ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት የተመደበላቸው ደግሞ ገዳሪፍ፣ ዱባይ፣ ሃርጌሳና ባህሬን ናቸው፡፡
በሰኔ 2013 ዓ.ም. መጨረሻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ለአምስተኛው ዙር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማጠቃለያ ንግግር ሲያደርጉ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገና በከፍተኛ ሁኔታ ሪፎርም መደረግ እንዳለበት በመግለጽ፣ ‹‹ዶላር በየቦታው ከመበተን ለጊዜውም ቢሆን አገሪቱን በተለያዩ አገሮች ከወከሉ አጠቃላይ ኤምባሲዎችና የቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች 30 ያህሉን መቀነስ ያስፈልጋል፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡
ለአብነትም በኬንያ ያለ አንድ አምባሳደር በናይሮቢም ሆነ በአዲስ አበባ ስለአገሪቱ የሚያውቀው ጋዜጣ በማንበብ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ሆኖ ጉዳዩን በመከታተል ቀጠሮ ሲያዝለት ሊሄድና ጉዳይ ሊስፈጽም የሚችልበት አሠራር መፍጠር እንደሚቻል መናገራቸው አይዘነጋም፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ተከትሎ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አካሄድኩት ባለው ሪፎርም፣ የአገርን ጥቅም ሊያስከብሩ ይችላሉ ያላቸውን ዲፕሎማቶች መሾሙን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡