ከዓለም ጤና ድርጅት በዕርዳታ የተለገሰው 95 ሜትሪክ ቶን መድኃኒት ወደ ትግራይ ክልል እንዲጓጓዝ ለቀረበው ጥያቄ የማረጋገጫ ፈቃድ መሰጠቱን፣ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
የዓለም ጤና ድርጅት ከአጋር አካላት ጋር በመሆን ወደ ትግራይ ክልል ለሚልከው 95 ሜትሪክ ቶን መድኃኒትና የሕክምና ቁሳቁስ ፈቃድ ለማግኘት ለኮሚሽኑ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ መጋቢት 8 ቀን 2014 ዓ.ም. ፈቃድ መሰጠቱን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ተናግረዋል።
ኮሚሽነር ምትኩ እንዳስረዱት፣ የዓለም ጤና ድርጅት ከጤና ሚኒስቴር ፈቃድ ማግኘቱን አረጋግጦ፣ ኮሚሽኑም ፈቃድ እንዲሰጠው መጋቢት 6 ቀን 2014 ዓ.ም. በላከው ደብዳቤ ጠይቆ፣ መድኃኒቶቹንና የሕክምና ቁሳቁሶቹን ከመጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. እስከ ሚያዚያ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ባለው አንድ ወር ውስጥ እንደሚያጓጉዝ ገልጿል። በድርጅቱ ጥያቄ መሠረትም ኮሚሽኑ የተጠቀሰውን መድኃኒትና የሕክምና መገልገያ ማጓጓዝ እንደሚችል፣ የፈቃድ ደብዳቤ ኢትዮጵያ ለሚገኘው የድርጅቱ ቢሮ መላኩን ኮሚሽነሩ አስረድተዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴድሮስ አድሃኖም (ዶ/ር) ባወጡት መግለጫ፣ ‹‹ወደ ትግራይ ክልል መድኃኒቶችና የሕክምና መሣሪያዎች ለመላክ ጥያቄ ብናቀርብም ምላሽ ልናገኝ አልቻልንም፤›› የሚል ስሞታ አቅርበው ነበር። ይህንን ተከትሎም ኮሚሽነር ምትኩ በሰጡት ምላሽ፣ ቅሬታው ተገቢ አለመሆኑንና ደብዳቤው ከሚጠይቀው ጊዜ በፊት ፈቃድ መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡
ቴድሮስ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ በትግራይ ክልል ለ500 ቀናት የተለያዩ አገልግሎቶች ተዘግተው መቆየታቸውን ገልጸው፣ 2200 ቶን አስቸኳይ የሕክምና ግብዓቶች ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡ እስካሁንም ማድረስ የተቻለው 117 ሜትሪክ ቶን ብቻ መሆኑን፣ በየካቲት ወር የተላከው 33 ሜትሪክ ቶን የሕክምና ግብዓት መድረስ የቻለው ለ300 ሺሕ ሰዎች ብቻ ነው ሲሉ አክለዋል።
አቶ ምትኩ በበኩላቸው፣ እስካሁን በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ከ250 ሺሕ ኪሎ ግራም በላይ መድኃኒትና የሕፃናት ምግቦች ወደ ትግራይ ክልል መላካቸውን ተናግረዋል፡፡