Sunday, March 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር ጨዋታና ጥንቃቄ የሚሻው የዳኞች ምደባ

የፕሪሚየር ሊጉ ሁለተኛ ዙር ጨዋታና ጥንቃቄ የሚሻው የዳኞች ምደባ

ቀን:

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ በአሁኑ ወቅት ፈታኝ ሆኖ እየተነሳ ያለው የእግር ኳስ ዳኞች የብቃት ጉዳይ ነው፡፡ ፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ ክለቦች በዳኞች ብቃት ላይ ቅሬታ አላቸው፡፡ ዳኞች በሚፈጽሟቸው ስህተቶች የተጎዱ ክለቦች ለመኖራቸው ድኅረ ጨዋታ በዳኞቹ የተላለፉት ቅጣቶችና እገዳዎች ማሳያዎች ናቸው፡፡ ብሔራዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ችግሩን ለማስወገድ በሚል ብቻ ሳይሆን፣ ዳኞቹ ራሳቸው ከጥቅማ ጥቅም ተፅዕኖ ነፃ ሆነው ለሙያቸው ታማኝ እንዲሆኑ ለማስቻል የሙያና የውሎ አበል ክፍያቸውን ከፍ እንዲል ካደረገ ቆይቷል፡፡ ይሁንና ችግሩ አሁንም አለመወገዱ እየተነገረ ነው፡፡ አንዳንዶቹ የእግር ኳስ ዳኞች (ረዳቶቹን ጨምሮ)፣ ስህተት የሚፈጽሙት ‹‹ጥቅማ ጥቅምን ከግምት በማስገባት ብቻ ሳይሆን የብቃት ጉዳይም መሆኑን›› የሚያነሱ አሉ፡፡ በሌላ በኩል የፌዴሬሽኑ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴም ጥፋት ፈጽመዋል ያላቸውን ዳኞች የጨዋታ ታዛቢ ዳኞችን ሪፖርት መነሻ በማድረግ የቅጣት ውሳኔዎችን አሳልፏል፣ እያሳለፈም ይገኛል፡፡ ፕሪሚየር ሊጉ የመጀመሪያ ዙር መርሐ ግብሩ ተጠናቆ ሁለተኛው ዙር መጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ለመጀመር በዝግጅት ላይ ነው፡፡ የክለቦቹ የደረጃ ሠንጠረዥ ሲታይ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ነጥባቸው ተቀራራቢ ከመሆኑ አኳያ፣ ክለቦቹ በሁለተኛው ዙር የሚያደርጉት እያንዳንዱ ጨዋታ ወሳኝ በመሆኑ በተለይ ከዳኝነት ጋር ተያይዞ ስህተቶች እንዳይፈጸሙ ጥንቃቄ ማድረግ የግድ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ስህተቶች እንዳይፈጸሙ የዳኞችን የሙያ ብቃት ከማሻሻል ጀምሮ ለሁለተኛው ዙር ያደረገውን ቅድመ ዝግጅት አስመልክቶ የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢና የካፍ ኮሚሽነር ከሆኑት አቶ ልዑል ሰገድ በጋሻው ጋር ደረጀ ጠገናው ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የእግር ኳስ ክለቦችና ቡድኖች ከዳኝነት ጋር ተያይዞ የተለያዩ ቅሬታዎችን ሲያቀርቡ ይደመጣል፡፡ የእግር ኳስ ዳኞችን በበላይነት የሚመራው በእርስዎ የሚመራው ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ እንደመሆኑ ምላሽዎ ምንድነው?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- በአሁኑ ወቅት በተመረጡ ከተሞች በተለያየ ደረጃ  የሚገኙ ክለቦችና ቡድኖች ውድድሮችን እያከናወኑ ይገኛል፡፡ ውድድሮቹ ከፕሪሚየር ሊግ ጀምሮ በወጣላቸው ፕሮግራም መሠረት እግር ኳሱን ዋናና ረዳት ዳኞች፣ እንዲሁም የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች፣ እንደየደረጃው ምደባ ተደርጎ መርሐ ግብሩ እየተከናወነ ነው፡፡ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት ውድድሩ ብዙ እንደመሆኑ መጠን ፕሪሚየር ሊጉን ለማሳያ ያህል እንመልከት ከተባለ፣ በመጀመሪያው ዙር ብቻ ወደ 120 ጨዋታዎች ተደርገዋል፡፡ ከፍተኛ (ሱፐር) ሊግና ብሔራዊ ሊግ አንደኛ ሊግና በየደረጃው በርካታ ውድድሮች በመካሄድ ላይ ናቸው፡፡ የሆነ ሆኖ ፕሪሚየር ሊጉን ስንመለከት በመጀመሪያው የውድድር ዓመት ከተደረጉት 120 ጨዋታዎች ዳኝነቱን በተመለከተ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ባደረገው ግምገማ ስድስት ጨዋታዎች በዳኝነት ስህተት ሲበላሹ ቀሪዎቹ በሚፈለገው ልክ በጥሩ የዳኝነት ብቃት የተጠናቀቁ ናቸው፡፡ በዳኝነት ስህተት ምክንያት ውጤት ያበላሹ ዋና አልያም ረዳት ዳኞች ሊሆኑ ይችላሉ እንደ ጥፋታቸው መጠን የዲሲፕሊን ዕርምጃ ተወስዷል፣ ወደፊት የሚወሰድ ይሆናል፡፡ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ውሳኔ ከማስተላለፉ በፊት እያንዳንዱን ጨዋታ የሚያጫውቱ ዳኞች ጨዋታ የመምራት ብቃታቸውን እንዲከታተሉ የተመደቡ ታዛቢዎች የሚያቀርቡትን ሪፖርት ብቻ ተመልክቶ ሳይሆን፣ ጨዋታው ምን እንደሚመስል ቪዲዮውን መላልሶ ከተመለከተ በኋላ እንደሆነ ሊወሰድ ይገባል፡፡ ዓለም አቀፍ ተሞክሮውም የሚያሳየው ይህንኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ክለቦች ለፌዴሬሽኑ የሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች የዳኝነት ስህተቶች በአብዛኛው ሲፈጸሙ የነበረው በዓለም አቀፍ ደረጃ ብቃት እንዳላቸው ሲነገርላቸው ከነበሩት ነው፡፡ ከእነዚህ ዳኞች አንዳንዶቹ አካባቢያዊ ተፅዕኖን በማንፀባረቅ ጭምር የሚታሙ እንዳሉበት ነው፣ ይህ በእውን የተደረገ ከሆነ እንዲህ ዓይነቱ ስህተት ሰውኛ ተብሎ ሊታለፍ የሚገባው ነው ብለው ያምናሉ?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- ከዳኝነት ሥነ ምግባር አኳያ ዳኞቻችን በእንዲህ ዓይነቱ ድርጊት ይሳተፋሉ የሚል እምነት የለኝም፡፡ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ ስህተት ሆን ተብሎ ሳይሆን ቅጽበታዊ ውሳኔ በሚወሰንበት ወቅት የሚያጋጥም እንደሚሆን ስለማምን ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በእኛ አገር ዳኞች ላይ ብቻ ሳይሆን እግር ኳስ በሚካሔድባቸው በሁሉም አገሮች የሚያጋጥም ክስተት ነው፡፡ ወደፊትም ፍፁም ይሆናል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ሁሉም እንደሚያወቀው በአሁኑ ወቀት ትልልቅ ዳኞች እንደ ባምላክ ተሰማ፣ ሊዲያ ታፈሰና ሌሎችም በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ጨዋታዎች በመምራት የተመሰከረላቸው የእግር ኳስ ዳኞች አሉን፡፡ ዳኞቻችን በእኛ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃ ከፍተኛ ከበሬታ የሚቸራቸው ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- ፕሪሚየር ሊጉ እርስዎም እንደሚያውቁት በቀጥታ ሥርጭት ጭምር የሚደረግ ነው፡፡ ውድድሩን ከዳኙት አንዳንዶቹ ኢንተርናሽናል ባጅ ያላቸው ናቸው፣ ስህተቱንም ሲፈጽሙ የታዩት እነዚሁ ዳኞች ናቸው፡፡ ምን ይላሉ?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ሁሉም አገር በሚመራበት ዓለም አቀፍ ሕግ የሚመራ ነው፡፡ ለዚያም ነው ዳኞች ስህተት ፈጽመዋል ተብሎ ሲታሰብ ዓለም አቀፍ ሕጎችን ከአገሪቱ የእግር ኳስ ሕግ ጋር በማጣጣም አንቀጽ ተጠቅሶ የቅጣት ውሳኔ የሚተላለፈው፡፡ ሌላው የብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ ስብስብ ቀደም ሲል በኢንተርናሽናል ደረጃ ውድድሮች በመምራት የሚታወቁ፣ ኢንተርናሽናል የካፍና የፊፋ ባጅ ባለቤት የነበሩ፣ እያዳንዱን የእግር ኳስ ሕግጋት ጠንቅቀው የሚያውቁ እንደመሆናቸው መጠን ከቅጣት በፊት ለዳኞች ተገቢው የአካል ብቃት የጤንነት ፈተና የሚሰጡ ጭምር ናቸው፡፡ በሚባለው ልክ ስህተት ይፈጽማሉ የሚባሉም እንዳልሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ሪፐርተር፡- ከቅጣት በፊት ከሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ጋር በተገናኘ ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ ለዳኞችና መሰል ሙያተኞች ምን ያህል ሙያዊ ድጋፍ ያደረጋል?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- ፕሪሚየር ሊጉን የሚዳኙ ቁጥራቸው ወደ 100 የሚጠጉ ነበሩ፡፡ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ውድድሮች ከመጀመራቸው በፊት የአካል ብቃት የጤና ፈተና ጨምሮ የተለያዩ የብቃት ማረጋገጫ ፈተናዎች እንዲወስዱ አድርጓል፡፡ በዚሁ መሠረት ፈተናውን ከወሰዱት መካከል 11 ዳኞች የአካል ብቃት ፈተናውን ማለፍ ያልቻሉ ነበሩ፡፡ ፈተናውን በብቃት ካለፉት ውስጥ ዋና ዳኞች 40 ሲሆኑ ረዳቶች ደግሞ 59 ናቸው፡፡ እነዚህ ናቸው ፕሪሚየር ሊጉ ሲጀመር ሐዋሳና ድሬዳዋ ላይ የተደረጉትን ጨዋታዎች እንዲመሩ ምደባ ያገኙት፡፡ ከዚህ ሁሉ ድጋፍና ክትትል በኋላ እንደ ተጨዋቾችና አሠልጣኞች ሁሉ ዳኞች ጥፋት ሲያጠፉ እንደ ጥፋቱ መጠን የሚያስቀጡ ቅጣቶች ይኖራሉ፣ ተግባራዊ የምናደርገው ይህንኑ ነው፡፡ በዚያው ልክ ባሳዩት የዳኝነት መጠን ሽልማትም እንዲሸለሙ ይደረጋል፡፡ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት በአሁኑ ወቅት ፕሪሚየር ሊጉ ተቋርጧል፡፡ ዳኞች ለሁለተኛው ዙር ውድድር ብቁ የሚያደርጋቸው ዕውቀት እንዳያገኙ፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) የዳኞች ኮሚቴ ሊቀመንበር ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ በማድረግ ሥልጠናውን እየሰጡ ናቸው፡፡ ሥልጠናው ዳኞቻችን በሁለተኛው ዙር ጨዋታ ምን ያህል ብቁ ሆነው እንደሚቀርቡ በግልጽ የሚያሳይ ነው፡፡    

ሪፖርተር፡- እስካለፈው ዓመት ድረስ ፕሪሚየር ሊጉን ጨምሮ ሁሉንም ውድድሮች በበላይነት የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነበር፡፡ አሁን ግን ራሱን ችሎ የራሱን ውድድር በራሱ እንዲመራ ኃላፊነት ወስዷል፡፡ ውድድሩን የሚመሩት ዳኞች ግን አሁንም በፌዴሬሽኑ ሥር የሚመደቡ ናቸው፡፡ ይህ ምናልባት ጨዋታዎችን ከመምራት አኳያ በተለይ በዳኝነት ሥርዓቱ ላይ ተፅዕኖ የለውም ይላሉ?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- አሠራሩ እንዲያውም ዳኞች ነፃ ሆነው ሙያዊ ነፃነታቸውን ጠብቀው ጨዋታዎችን ያለ ተፅዕኖ እንዲመሩ መልካም አጋጣሚ ነው፡፡ በነገራችን ላይ የዳኞች ኮሚቴ በዓለም አቀፉ ተቋም ሕግ መሠረት ተጠሪነቱ ለብሔራዊ ፌዴሬሽን ነው፡፡ ይህ የሚሆንበት ዋናው ምክንያት ዳኞችን ከማንኛውም ተፅዕኖ ነፃ ለማድረግ በሚል ነው፡፡ ከዚህ ይልቅ ዳኞች እንደ ክለቦች በሊግ ኮሚቴው ሥር ይተዳደሩ ቢባል ነው የጎላ ተፅዕኖ ሊኖር የሚችለው፡፡ አሁን ግን ዳኞች ጨዋታ ሲኖራቸው ካልሆነ ከክለቦችም ሆነ ሌሎች አካላት ጋር የሚገናኙበት ዕድል የለም፡፡ ከሆቴል ጀምሮ በቂ የሙያና የውሎ አበል ጭምር እንዲከፈላቸው ተደርጓል፣ ይህ ለፕሪሚየር ሊጉ ዳኞች ብቻ ሳይሆን በየደረጃ ለሚዳኙ ዳኞች ጭምር ተግባራዊ እየተደረገ ያለ ነው፡፡ የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች (ኮሚሽነሮች) ተጠሪነት ግን ለሊግ ኮሚቴው ነው፡፡ ምደባም የሚደረግላቸው በሊግ ኮሚቴው አማካይነት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ተጠሪነቱን ለያይቶ ማስቀመጡ ምክንያት ይኖረው ይሆን?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- ምንም ምክንያት የለውም፤ ከድሮም የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች ተጠሪነት ለፌዴሬሽኑ ውድድርና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ስለነበር ነው፡፡ የውድድርና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ በቀጥታ የሚመለከተው አወዳዳሪውን አካል ስለሆነ አሁንም ተጠሪነቱ ለሊግ ኮሚቴው በመሆኑ ነው የጨዋታ ታዛቢዎች ተጠሪነት ለሊግ ኪሚቴው እንዲሆን የተደረገው፡፡

ሪፖርተር፡- የጨዋታ ታዛቢ ዳኞች ጥፋት ሲያጠፉ የዲሲፕሊን ዕርምጃ የሚወስደው ግን ብሔራዊ የዳኞች ኮሚቴ ነው፣ የሚጣረስ አይሆንም?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- በአሠራር ደረጃ እስካሁን የሚጣረስ ነገር አልገጠመንም፡፡ ታዛቢ ዳኞች ውድድሮችን ለማጣጣም ሲባል ተጠሪነታቸው ለሊግ ኮሚቴው ይሁን እንጂ ጥፋቱን በሚመለከት ሕጉ በቀጥታ ተግባራዊ የሚደረገው ዳኝነት ስለሆነ በትይዩ ነው፡፡ ሁለቱን አካላት በዋናነት መለየት ያስፈለገበት ምክንያት ገለልተኛ ሆነው ውሳኔ እንዲሰጡ ለማድረግ ሲባል ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ምልከታ፣ ዳኞችና ረዳቶቻቸው በሁለተኛው ዙር ጨዋታ በጥቅማ ጥቅም ውጤት ሊያስቀይር የሚችል ውሳኔ እንደማያሳልፉ እርግጠኛ መሆን ይቻላል?

ከሚሽነር ልዑልሰገድ፡- ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ሆነ ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ይህን በሚመለከት የሚችለውን ሁሉ ጥንቃቄ ያደርጋል፣ እያደረገም ነው፡፡ ከዚህ አልፎ የሚሄድ አካል ካለ ግን ደግነቱ ፕሪሚየር ሊጉ ቀጥታ ሥርጭት ስላለው ጨዋታውን መልሰን በመመልከት ዳኛው በሚባለው ልክ ውጤት የሚያስቀይር ጥፋት አጥፍቷል ብሎ ካመነ የጥፋት ውሳኔ የመስጠቱ ጉዳይ ለድርድር አይቀርብም፡፡ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው ሁለተኛው ዙር ጨዋታ ልዩ ጥንቃቄ የሚደረግበት ነው፤ ምክንያቱም ክለቦች አሁን ካላቸው ነጥብ መረዳት የሚቻለው ልዩነቶቻቸው በጣም ጠባብ ነው፡፡ ምንም ዓይነት የዳኝነት ክፍተት እንዲፈጠር አንፈልግም፡፡ ክለቦች ቀጣይ ዕጣ ፈንታቸውን በራሳቸው እንዲወስኑ ነው ፍላጎታችን፡፡ የዳኞች ምደባውን ውስን የምናደርገው እንደነዚህ የመሰሉ ጥቃቅን ችግሮች እንዳይከሰቱ ከማሰብም ጭምር ነው፡፡ በተከታታይ በአንድ ከተማ ላይ ለሚደረጉ ውድድሮች የምንመድባቸው ዳኞች አሥር አልያም 11 ካልሆነ ሁሉንም አንመድብም፡፡ በእርግጥ ክለቦች በየትኛው አቅጣጫ እንደሚመጡ ባይታወቅም ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ በቂ የሆነ የራሱ የክትትልና የቁጥጥር ሥርዓት ስላለው ጉዳዩን እንዲህ በቀላሉ እንደማይመለከተው ዳኞቻችን ሊገነዘቡ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- በፕሪሚየር ሊግ ደረጃ ለሚዳኙ ዳኞች የሙያና የውሎ አበል ክፍያው ምን ያህል ነው?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- ቀድሞ ውሎ አበል 1,000 ብር የነበረው አሁን 2,000 ሲሆን፣ ለአንድ ጨዋታ ደግሞ እስከ 3,000 ብር ይከፈላቸዋል፡፡ ይህ ለአሥርና ከዚህም በላይ ተከታታይ ሳምንታት ጨዋታ የመዳኘት ዕድል የሚያገኝ ዳኛ ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያገኝ መገመት ይቻላል፡፡ በዚያ ላይ ወደ ኢንተርናሽናል ደረጃ ከፍ ለማለት በአገር ውስጥ ለሚደረጉ ውድድሮች የሚሰጠው ነጥብ ወሳኝ ነው፡፡ ለዚያም ነው ዳኞች በተራ ነገር መሸወድ የለባቸውም የምንለው፡፡

ሪፖርተር፡- በከፍተኛ፣ በብሔራዊና  በአንደኛ ሊጎች ውድድሮችን የሚመሩ ዳኞች በፕሪሚየር ሊጉ እንዳለው ከጥቅማ ጥቅም ጀምሮ ክትትልና ቁጥጥሩ አለ?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- ክፍያው ቢለያይም በከፍተኛው ወይም ብሔራዊ ሊግ አልያም አንደኛ ደረጃ ላይ የሚዳኙ ዳኞች፣ ከፕሪሚየር ሊጉ ዳኞች በተለየ ነው ለጨዋታው ክብደት ሰጥተው የሚዳኙት፡፡ ምክንያቱም ነገ አልያም ከነገ ወዲያ ወደ ላይ ማደግን የማይፈልግ ዳኛ ይኖራል የሚል እምነት ስለሌለ ማለት ነው፡፡ ልዩነቱ ከከፍተኛው ሊግ ጀምሮ ዳኞችንም ሆነ የጨዋታ ታዛቢ ዳኞችን የሚመርጠውም ሆነ የሚመድበው ብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ መሆኑ ነው፡፡ ውድድሮቹም የሚመሩት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ክፍያው ከፕሪሚየር ሊግ አንፃር አነስተኛ እንደሆነ የሚናገሩ ዳኞች አሉ፣ የሚሉት ይኖራል?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- መረሳት የሌለበት ፕሪሚየር ሊጉ ትልቅ የስፖንሰር ገቢ ያለው መሆኑ ነው፡፡ በተቻለ መጠን ዳኞች የማይጎዱበት ገቢን መሠረት ያደረገ ክፍያ እንደሚፈጸምላቸው ግን መናገር እወዳለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ከደኅንነት አኳያስ?

አቶ ልዑል ሰገድ፡- ቀደም ሲል ችግሮች ነበሩ፤ አሁን ግን ኮቪድም ስላለ ደጋፊዎችም ወደ ስታዲየም በብዛት ስለማይገቡ፣ በዚያ ላይ ጨዋታዎቹ የሚከናወኑት በተመረጡ ከተሞች በመሆኑ፣ እስካሁን ያን ያህል ችግር አልፈጠረብንም፡፡ ምናልባት ወደፊት የሚል ነገር ካለ ውድድር የሚካሄድባቸው ከተሞች ኃላፊነቱን እንዲወስዱ የሚደረግበት አሠራር ሊኖር ስለሚችል ሥጋቱ ያን ያህል ይሆናል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ውድድሮቹ በሐዋሳ፣ በባህር ዳርና በሌሎችም ትልልቅ ከተሞች ነው እየተካሄዱ ያሉት፡፡ በዚያ ላይ የፌዴሬሽኑ አመራሮች ከፕሬዚዳንቱ ጀምሮ ውድድሮች በሚኖሩበት ወቅት በቦታው በመገኘት ግምገማ ስለሚያደርጉ አስተናጋጅ ከተሞች ይጠነቀቃሉ፡፡ ሌላው እንደ ቀድሞ አጥር በሌለው ሜዳ ጨዋታ የማይታሰብ ነው፡፡ የፊፋና የካፍ ማስጠንቀቂያና ዕገዳ ምን ያህል ዋጋ እያስከፈለን እንደሚገኝ መዘንጋት ይኖርብናል ብዬ አላስብም፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለፋይናንስ ዘርፉ ብቃት ያለው የሰው ኃይል የማፍራት የቤት ሥራን የማቃለል ጅማሮ

የአገሪቱ የፋይናንስ ዘርፍ እያደገ ለመሆኑ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች ውስጥ  የግል...

የምድር ባቡርን የሚያነቃቃው የመንግሥት ውሳኔ

በኢትዮጵያ ወደብ አልባነት ላይ የተደመረውን የሎጀስቲክስ ችግር ለመፍታት ግዙፍ...

የፓርላማ አባላት ስለሰላም ስምምነቱ አፈጻጸም ግልጽ መረጃ የለንም አሉ

‹‹ሕወሓትን ለፍረጃ አብቅተውት የነበሩ ጉዳዮች በአብዛኛው መልክ ይዘዋል›› ሬድዋን...