Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

የ ሳ ም ን ቱ ገ ጠ መ ኝ

ቀን:

እኔ በበኩሌ በዚህ ዘመን የሚገጥሙንን አስፈሪ ነገሮች ችላ ማለታችን ያሳስበኛል፡፡ ፍትሕ ፍለጋ የሚባዝኑ ነፍሶች በሞሉባት አገራችን መሰንበቻውን የሰማነው አሰቃቂ ድርጊትም ዕረፍት ይነሳኛል፡፡ ከዓመታት በፊት የገጠመኝ ከሰሞኑ ሁኔታችን ጋር ቢገጥምብኝ እንዲህ አቅርቤዋለሁ፡፡ ጊዜው ራቅ ቢልም ትዝ የሚለኝና የሚያስገርም ያልኩት ነገር ይኼ ነው፡፡ እንደተለመደው ከኢንተርኔት የዓለም ወሬዎችን ስቃርም ድንገት ዓይኔ አንድ አስገራሚ ዜና ላይ አረፈ፡፡ ዜናውን ይዞት የወጣው ‹‹ ጄሩሳሌም ፖስት›› የተባለ የእስራኤል ጋዜጣ ሲሆን፣ ምንጭ ያደረገው ናይሮቢ ውስጥ የሚታተመውን ‹‹ናይሮቢያን›› የተባለ ጋዜጣ ነበር፡፡ የዚህ አስገራሚ ዜና ርዕስ፣ ‹‹ኬንያዊው ጠበቃ በኢየሱስ ክርስቶስ ግድያ የእስራኤል መንግሥትንና አይሁዳውያንን ሔግ ችሎት ከሰሱ›› ይላል፡፡ ይህ ርዕስ ሲታይ ለጊዜው ግራ መጋባት ቢፈጥርም፣ ጠበቃው ሚስተር ዶላ እንዳዲስ መቀመጫውን በሔግደረገው ዓለም አቀፍ የፍትሕ ችሎት፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ሕገወጥ ፍርድ በማስተላለፍ ስቅላት የፈጸሙና ያስፈጸሙ ሊዳኙ ይገባቸዋል ብለው ነበር ክስ ያቀረቡት፡፡

በወቅቱ ኬንያዊው ጠበቃ እንዳሉት የእስራኤል መንግሥት የበለጠውን የኃላፊነት ድርሻ ሲወስድ፣ ከክርስቶስ ልደት በፊት 42 እስከ ክርስቶስ ልደት በኋላ 37 ድረስ የነበረው የሮማ ንጉሥ ታይቤሪየስ፣ ጲላጦስ፣ የተወሰኑ የአይሁድ ሽማግሌዎች፣ ንጉሥ ሔሮድስ፣ የጣሊያን መንግሥትና የእስራኤል መንግሥት ተጠያቂ ናቸው፡፡ እንደ ዘገባው ከሆነ፣ ጠበቃው እነዚህ የተጠቀሱት ተከሳሾች በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በፈጸሙት ሕገወጥ ፍርድና ስቅላት በቂ ማስረጃ ይጠቀስባቸዋል፡፡ ‹‹ዛሬ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ የሚገኝ ማስረጃ አለ፡፡ የመጽሐፍ ቅዱስን ማስረጃ ደግሞ ማንም ሊያጣጥለው አይችልም…›› በማለት ጠበቃው ለጋዜጣው መናገራቸው በዘገባው ተካቶ ነበር፡፡ ጠበቃው ከሁለት ሺሕ ዓመታት በፊት ለተፈጸመው ድርጊት ተጠያቂ የነበሩ ሰዎች በሕይወት ባይኖሩም፣ እነሱ ይወክሉዋቸው የነበሩ መንግሥታት ኃላፊነቱን ይወስዳሉ ማለታቸውም በጊዜው ተሰምቷል፡፡ በብዙዎች ዘንድም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡

ኬንያዊው ጠበቃ የኢየሱስ ክርስቶስ ክስ፣ ችሎት፣ ክርክርና ውሳኔ ሕገወጥ ከመሆኑም በላይ የተፈጸመበት ድብደባ፣ ማሰቃየትና ስቅላት ወንጀል ነው ብለዋል፡፡ እሳቸውም ይኼንን ጉዳይ ከመረመሩ በኋላ የተጠቀሱትን ወገኖች የሚከሱት በዚያን ዘመን ስላልተፈጠሩ መሆኑን ገልጸው፣ በአሁኑ ዘመን ግን እንደ አንድ የኢየሱስ ወዳጅ ክስ መመሥረታቸውን ተናግረዋል፡፡ ክሳቸው በናይሮቢ ፍርድ ቤት ውድቅ ቢደረግባቸውም፣ እሳቸው ግን ወደ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤት ለመሄድ መገደዳቸውን በጊዜው ተናግረዋል፡፡ ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቱም ይኼንን ጉዳይ የማየት ሥልጣን እንደሌለው መግለጹን አስታውሳለሁ፡፡

- Advertisement -

ብዙዎች በጠበቃው ድርጊት ተገርመዋል፣ ግራ ተጋብተዋል፣ አሹፈዋል፡፡ ዘመናችን በርካታ የሚያስገርሙና የሚያስደነግጡ ጉዳዮች የሚከሰቱበት ቢሆንም፣ በበኩሌ የጠበቃውን ምልከታ አከብራለሁ፡፡ አንድ ሰው የመሰለውን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ ሲያቀርብ የመቀበልና ያለ መቀበል መብቱ የእኛ ሲሆን፣ ግለሰቡ ወይም ግለሰቧ ሐሳባቸውን በማቅረባቸው ምክንያት ሊሳቅባቸው ወይም ሊጣጣሉ አይገባም፡፡ የጠበቃው ሐሳብ ያስኬዳል ወይም አያስኬድም የሚለው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ሕገወጥነትን በሕጋዊ መንገድ አደብ ለማስገዛት የሚነሱ ሰዎች ሲኖሩ አስደሳች ነው እላለሁ፡፡

እስኪ ዙሪያችንን እንመልከት፡፡ ኃይለኞችና ጉልበተኞች ሕግ ባለበት አገር ውስጥ እንዳሻቸው እየፈነጩ የማፊያ ተግባር ሲፈጽሙ፣ ‹‹ጎመን በጤና›› እየተባለ ይታለፍ የለም ወይ? በሀብቱ የሚመካ ሕገወጥ በሌብነት ከተካኑ ባለሥልጣናት ጋር ሰምና ወርቅ ሆኖ ድሆችን ሲያስለቅስ፣ መሬታቸውን ወይም ንብረታቸውን ሲነጥቅ፣ በአጃቢዎቹ አማካይነት የሰው ሚስት ሲቀማ፣ በኮንትሮባንድ አገር እየዘረፈ ሲበለፅግ ማን ደፍሮ ይናገራል? ማን ይደፍርስ ነበር? ደፈር ብለው የሚጠይቁ ሲነሱ ‹‹ታፔላ›› ተለጥፎላቸው የደረሰባቸው ሥቃይ ይታወቃል፡፡ ከዚህ የባሰ ወንጀል የሚፈጽሙ እየተፈጠሩ ያሉት እኮ ጠያቂ በመጥፋቱ ነው፡፡ ጠያቂ ሲጠፋ የሰው ልጅ ከእነ ሕይወቱ እሳት ውስጥ ይጣላል፡፡

በወቅቱ የኬንያውን ጠበቃ አስገራሚ ዜና የነገርኩዋት ጓደኛዬ የሚገርም ነገር ነበር የነገረችኝ፡፡ ይኼንን ጉድ አንብቡ፡፡ ከዓመታት በፊት አንድ የምታውቀው ሰው የንግድ ድርጅቱን የሚመራበትን የመንግሥት ቤት ድንገት ‹‹ለቀህ ውጣ…›› ይባላል፡፡ ምክንያቱን ሲጠይቅ፣ ‹‹ልቀቅ ተብለሃል እንጂ ምክንያት ጠይቅ አልተባልክም…›› የሚል አስፈሪ ምላሽ ያገኛል፡፡ ማስጠንቀቂያው በተሰጠው በአሥረኛው ቀን ቤቱ ይታሸጋል፡፡ 30 ዓመታት በላይ በሕጋዊ መንገድ ተሰጥቶት የሚሠራበትን የንግድ ቤት ተቀምቶና ንብረቱ የትም ተጥሎ በመጨረሻ ለሌላ ባለጊዜ ግለሰብ ይሰጥበታል፡፡ የደረሰበትን ኢፍትሐዊ ድርጊት በፍርድ ቤት ለመከራከር ይወስናል፡፡ ሦስት ዓመት ሙሉ ተከራክሮ በሐሰተኛ ፍርድ በተሠራበት ደባ ይረታል፡፡ ይግባኝ ቢልም አይቀናውም፡፡ በመጨረሻ ጭንቅላቱን ነካ ያደርገዋል፡፡ ብቻውን ማውራት ሲጀምርም ‹‹አበደ…›› ይባላል፡፡ እንዴት አያብድ?

አንድ ቀን የተወረሰበት የንግድ ቤት ግድግዳ ላይ፣ ‹‹ዛሬ በኃጢያት የተቀማሁትን ቤቴንና ንብረቴን የሚያስመልስ ጀግና የሆነ ደፋር ዜጋ እስኪመጣ እጄን ሰጥቻለሁ…›› ብሎ ጻፈ አለችኝ ጓደኛዬ፡፡ ለፍትሕና ለርትዕ የሚቆሙ ነፍሶች የተባረኩ ሲሆኑ፣ በተቃራኒው በሰው ዕንባና ደም የሚቀልዱ ደግሞ እኩያን ናቸው፡፡ ለማንኛውም ፍትሕን እየረገጡ ወንጀል ከሚፈጽሙ ይልቅ፣ ፍትሕን ከወንጀል የሚታደጉ ብፁዓን ናቸው፡፡ እኔ ሳስበው ያንን ምስኪን ሰው ፈጣሪ የሰማው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም አይነኬ የሚመስሉ ስማቸው የገዘፈ ዘመነኞች ከአስፈሪው ሥልጣናቸው ተገፈትረው የተጣሉ ሲሆን፣ ለጊዜው ከፍትሕ ያመለጡ የሚመስላቸው እንደማይቀርላቸው ወቅቱ እየነገረን ይመስለኛል፡፡

ፍትሕ እንደ ሸቀጥ በሚቸበቸብበት አገር ውስጥ ተጠያቂነት ሲመጣ ወንጀል የሠሩ ብዙ በመሆናቸው፣ ተገቢውን ፍትሕ ማግኘታቸው ነገ ለሚታሰበው ብሔራዊ ምክክር አመቺ ይሆናል፡፡ ይህ በተግባር ካልታየ ግን እንደ ኬንያው ጠበቃ ፍትሕ ፍለጋ የሚነሱ ሚሊዮኖች እንዳሉ መዘንጋት አይገባም፡፡ የትናንት ሥቃይ የሚሽረው ፍትሕ ሲሰጥ እንጂ ሲነፈግ አይደለም፡፡ ለቂምና ለበቀል በር አንክፈት፡፡ ወንጀል ሠርቶ መደበቅም ሆነ የወንጀለኛ ተከራካሪ ሆኖ ፍትሕን መጋፋት ካሁን በኋላ የሚሠራ አይመስለኝም፡፡ ያዋጣናል የሚሉ ካሉ ለጊዜው ነው እንጂ የትም መድረስ እንደማይችሉ መተማመን ይኖርብናል፡፡ ሰሞኑን ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ውስጥ ለተፈጸመው አረመኔያዊ ድርጊት ተጠያቂነት ያለባቸው ሕግ ፊት ቀርበው ፍትሕ የሚሰፍነው፣ ሁላችንም ለፍትሕ ተሟጋች መሆን ስንችል ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ከጎጠኝነት ተላቀን ሰው መሆን መቻል አለብን፡፡

(ነጋሽ የበጋእሸት፣ ከአራብሳ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...