በገለታ ገብረ ወልድ
የተፈጠረ ስህተት ወይም የተፈጸመ ጥፋትን በሙሉ ወይም በከፊል አምኖ ይቅርታ መጠየቅ በሰብዓዊነትም ሆነ በሕግ ሰው ለሆነ ሁሉ ታላቅ መገለጫ ነው፡፡ የሚያኮራ የማንነት ማሳያ ነው፡፡ ይቅርታ መጠየቅ ትልቅነት ነው፡፡ በአንፃሩ ይቅርታን መቀበል ወይም ይቅርታ ማድረግ የተበደለው ወገን ጨዋነት ሚዛን ነው፡፡ በመላው ዓለም ሕዝቦች፣ እምነቶችና ባህሎች ውስጥ የሚገኝ ጠንካራው የማኅበራዊ ማንነት ማረጋገጫ ውል ይቅርታ ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ‹ይቅርታ› የሚለው ቃል ከ40 ጊዜ በላይ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ‹‹ምሕረት›› የሚለው ቃልም ከ50 ጊዜ በላይ አለ፡፡ ‹‹ኃጢያቴ ታላቅ ነውና ስለስምህ ይቅር በለኝ››፣ ‹‹ይቅር በለኝ እኔም የበደሉኝን ይቅር እንደምል››፣ ‹‹የሚሠሩትን አያውቁምና ይቅር በላቸው…›› የሚሉም ይታወቃሉ፡፡
እንዲሁም መንግሥት ሕዝቡን ይቅርታ ቢጠይቅ ነውር የለበትም፡፡ የመንግሥትን ትልቅነት፣ አርቆ አስተዋይነት፣ ለሕዝብ ተገዥነት፣ ለሕዝቡ ያለውን አክብሮት የሚያሳይ በመሆኑ እንደግፈዋለን፡፡ ይህ ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚመነጭ እንጂ፣ አምባገነን መንግሥታት የሚያደርጉት ቀርቶ የሚያስቡትም አይደለም፡፡ ይቅርታ የታላቅነት እንጂ የሽንፈት ምልክት አይደለም (በዚህ ረገድ በለውጡ መጀመርያ ሰሞን መሪዎቻችን ያሳዩት ትህትና በአርዓያነት የሚጠቀስ ነበር)፡፡
ይቅርታ መጠየቅ መልካም መሆኑን መካድ ባይቻልም ይቅርታው የተጠየቀበትን አግባብ ግን መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ ይቅርታው የተጠየቀው በየትኛው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ ወይም በየትኛው ደንብ ወይም መመርያ መሠረት ነው? ይቅርታ ጠያቂው ማነው? ፕሬዚዳንቱ? ወይስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ? በሕገ መንግሥቱ ሰነድ ውስጥ ‹‹ይቅርታ›› የሚል ቃል ያለው (ቢያንስ እኔ ያየሁት) አንድ ቦታ ላይ ብቻ ነው፡፡
እሱም ስለፕሬዚዳንቱ ሥልጣንና ተግባር በሚዘረዝረው አንቀጽ 71 ንዑስ አንቀጽ 7 ላይ የሰፈረው፣ ‹‹በሕግ መሠረት ይቅርታ ያደርጋል›› የሚለው ነው፡፡ ይህም ቢሆን ‹‹ይቅርታ ያደርጋል›› ይላል እንጂ፣ ‹‹ይቅርታ ይጠይቃል›› አይልም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥልጣንና ተግባር በዘረዘረው አንቀጽ 74 ውስጥም፣ ‹‹ይቅርታ ይጠይቃል›› የሚል ቃል ወይም አንደምታ ያለው ነገር የለም፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣንና ተግባር 13 ንዑስ አንቀጾች ባሉት አንቀጽ 77 ሥር ተዘርዝሯል፡፡ እዚህም ውስጥ የለም፡፡
በአጠቃላይ ይቅርታ መጠየቅም ሆነ ይቅርታ ማድረግ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠ ሥልጣንም ሆነ ተግባር አይደለም፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ (ሌላ እኔ የማላውቀው ደንብ ወይም መመርያ ወይም የሚኒስትሮች ምክር ቤት ቃለ ጉባዔ ከሌለ በስተቀር) ጠቅላይ ሚኒስትሩ በራሳቸው ተነሳሽነትና ካቢኔያቸውን አሳምነው የወሰዱት ዕርምጃ ከሆነ እጅግ በጣም የሚደነቅ ነው (በነገራችን ላይ ዕርምጃው ወደ ሥልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ ፖለቲከኞችን ከእስር በመፍታት፣ በመሪው ድርጅት ሕዝብ ለተፈጠረበት ቅሬታ ይቅርታ በመጠየቅ፣ አሁን ደግሞ ለብሔራዊ መግባባት መድረኩ ያመች ዘንድ በድጋሚ በሕግ ጥላ ሥር የነበሩ ፖለቲከኞችን ከእስር በመልቀቅ ታይቷል)፡፡
ካሳና ወገናዊ ድጋፍ
‹‹ይቅርታ ተጠየቀ›› ማለት ሁሉም ነገር አበቃለት ማለት አይደለም፡፡ ፋይሉ ተዘግቶ ወደ መዝገብ ቤት ተመላሽ ሆኗል ማለት ሊሆን አይችልም፡፡ ቀጥሎ የሚመጣ ሒደት አለ፡፡ የካሳ ጉዳይ አለ፡፡ አንዱ ካሳ የግድ መሆን ያለበት ነው፡፡ ሁለተኛው ካሳ ለድርድር የሚቀርብ ሊሆን ይችላል፡፡ ይቅርታ ለተጠየቀው ሕዝብ የመጀመርያው ካሳ የሚሆነው፣ ይህን ሁሉ ችግር የፈጠሩና በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እጃቸው ያለበት ሰዎች በሕግ ፊት ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡
ያጠፋ መቀጣት አለበት፡፡ ልጆቻቸውን ያጡ ወላጆች ማቅ ለብሰውና ዘመዶቻቸው ነጠላ ዘቅዝቀው ባሉበት አገር ወንጀለኛው ሱፉን ሽክ አድርጎ፣ ኪሱን ሞልቶ፣ ደረቱን ነፍቶ የሚንጎማለልበት ሁኔታ መኖር የለበትም፡፡ ጥፋተኞችን በሕግ መጠየቅ ተጎጂ ቤተሰቦችን ለማስደሰት ብቻ አይደለም፡፡ የአገሪቱ ሥርዓት ለወንጀለኞች ቦታ የሌለው መሆኑን ለማረጋገጥ ነው፡፡
ለሌላው መጪ ጊዜና ለሌላው ሰው ትምህርት እንዲሰጥ ነው፡፡ ተጠርጣሪዎችና ከጥፋት ድርጊት ያልታረሙ ኃይሎች ሁሉ በቁጥጥር ሥር መዋል አለባቸው፡፡ ታስረው ጉዳያቸው መጣራት አለበት፡፡ የሰውና የሰነድ ማስረጃ ተሰብስቦና ተጠናክሮ ለውሳኔ መቅረብና ፍርዳቸውን ማግኘት አለባቸው፡፡ በዚህ ላይ የምንደራደረው ነገር መኖር የለበትም (ምናልባት ለብዙዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት የነበሩ አንዳንድ የሁከት ፖለቲከኞችና አቦይ ስብሃትን የመሰሉ የአሸባሪው ሕወሓት ራሶች መፈታታቸው አብዛኛውን ቅር እንዳሰኘ የሚነገረው ከዚሁ እውነታ አንፃር ይሆናል)፡፡
ይህ የሚሆነው ከሁለቱም ወገን ነው፡፡ በመንግሥት ውስጥ ሆነው ጥፋት በሠሩ ሰዎችና በሕዝቡ ውስጥ ሆነው ሕዝቡን ባልተገባ ማነሳሳት ሁከቱ ወደ ኃይል ዕርምጃ እንዲያመራ ባደረጉ፣ ሰላማዊውን የሕዝብ ጥያቄ ወደ ድንጋይ ውርወራና ንብረት ማውደም በገፉና ባደረሱ የወንጀል አስተባባሪዎች ላይም ሕጋዊ ተጠያቂነት ሊኖር ይገባል፡፡ በተለይ ሕወሓት መራሹ ኃይል የለኮሰውን ጦርነትና የፍጅት ስትራቴጂ ተከትሎ በየትኛውም የአገሪቱ አካባቢ ንፁኃንን የገደሉ፣ ያሳደዱ፣ ሀብት ያወደሙና በአገር ላይ ወንጀል የፈጸሙ ሁሉ በምንም መለኪያ ከመጠየቅ ነፃ ሊሆን አይችሉም፣ አይገባም፡፡
ለሰላም ተልዕኮ በተሰማራው መለዮ ለባሽ ላይ ድምፅ ባለውና በሌለው መሣሪያ ጉዳት ባደረሱ፣ ቋጥኝና ግንድ በመካብና መንገድ በመዝጋት የሠራዊቱን እንቅስቃሴ ባስተጓጎሉ ሰዎች ላይ ተመጣጣኝ ቅጣት ሊጣልባቸው ይገባል፡፡ በተለይ በተለይ በትግራይ ክልል ከ20 ዓመታት ላላነሰ ጊዜ በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ አገርና ሕዝብን ሲጠብቅ በቆየው የሰሜን ዕዝ ወታደሮች፣ አዛዦች፣ ትጥቅና ንብረት ላይ የደረሰ ጥፋትና ውድመት ተጠንቶና በበቂ መረጃ ተረጋግጦ አጥፊዎች የእጃቸውን ካላገኙበት፣ እንደ ብሔራዊ ውርደት ይቆጠራል፡፡ የተጎጂዎቸንም ዕንባ በቀላሉ ማበስ አይቻልም፡፡
ከዚሁ ጋር መታየት ያለበት ‹‹ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ›› እንዳይሆን፣ በተቀሰቀሰው ሁከትና ወከባ ወይም በእርስ በርስ ጦርነቱ ምክንያት ተይዘው የታሰሩ ንፁኃን ሰዎች እንዳይኖሩ በአፋጣኝ እየተጣራ የሚለቀቁበት ሁኔታ መኖር አለበት፡፡ በተለይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመነሳቱ ጋር ተያይዞ ያለ ጥፋቱ የሚቀጣ ዜጋ እንዳይኖርና ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ እንዳይነካ፣ በጥንቃቄ መለየትና ማጥራት ያስፈልጋል፡፡ በሒደቱ ሕዝብ እንዲሳተፍበት ማድረግም ጠቃሚ ነው፡፡
መንግሥት መሃሪ እንደ መሆኑ መጠን በቀስቃሾች ተንኮል፣ በፖለቲካ ሴረኞች ግፊትና አስገዳጅነት ተገፋፍቶ በማያውቀው ድርጊት በተገኘ፣ ጓደኞቹ ወይም ሌሎች ሰዎች ሲያደርጉ ስላየ ብቻ ዘልሎ ለገባውና በጥፋት ላይ ለተገኘው ወጣት ምሕረት እየተደረገ የሚለቀቅበት የራሱ አሠራር እንደሚኖረው ተስፋ ያደረግን ብዙ ነን፡፡ እዚህ ላይ የሕወሓትም ሆነ የሸኔ አባልና ተዋጊ ሆነው በግንባር የተማረኩ በርካታ ወጣቶች አያያዝና የተሃድሶ ሙከራ ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን፣ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ጭምር ማረጋገጣቸው በበጎ የሚጠቀስ ነው፡፡ ለወደፊትም ተጠናክሮ መሄድ አለበት፡፡ ሁለተኛው ምንም ያህል አገራችን ደሃና ሕዝባችንም ታዳጊ ቢሆንም በተለያዩ ጊዜያት በተፈጸሙ ሁከቶችና ግጭቶች፣ እንዲሁም በሰሜኑ አደገኛ ጦርነት ንብረት ለወደመባቸው ባለሀብቶችና ለአገሬው ዜጎች የሚያግዝ ድጋፍ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ የገንዘቡ (የድጋፉ) መጠን እንደ መንግሥት አቅም፣ እንደ ድርጅቶችና አጋሮች አቅም፣ ብሎም እንደ ተጎጂዎች ሁኔታ በአገር ሽማግሌዎች፣ በሃይማኖት አባቶችና በመንግሥት የሚመለከታቸው አካላት እየታየ ሊወሰን የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡
እዚህ ላይ የድጋፉ ወይም የገንዘቡ መብዛት ወይም ማነስ አይደለም ቁምነገሩ፡፡ ይህ ጉዳይ በሐሳብ ደረጃ ሲታይ መልካም መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ነገር ግን አፈጻጸሙ ወደ መሬት ሲወርድ ችግር ሊፈጥር ስለሚችል በጥንቃቄ ማየት ያስፈልጋል፡፡ ለማን እንደሚሰጥ፣ ለምን ዓይነት ተሳትፎ እንደሚሰጥ፣ ምን ተግባር ውስጥ ለተገኘ እንደሚከለከል፣ የገንዘቡ መነሻና ጣሪያ መጠን ከየት እስከ የት እንደሚሆን የአገር ሽማግሌዎችና የሚመለከታቸው አካላት አጥንተው ለመንግሥት መዋቅሩ ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡
እዚህ ላይ መንግሥት ገንዘብ እንኳን ባይኖረው በቀጥታ ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩበት ሀብት የወደመባቸውን ዜጎች በየትኛውም አካባቢ እያጠና፣ ቤት በመሥራት፣ መሥሪያ ቦታ በማመቻቸት፣ የግብር ዕፎይታ በመስጠት፣ ማኅበራዊ ልማትና መሠረተ ልማቶችን ፈጥኖ በመመለስ፣ ተፈናቃዮችን በአመቺ ቦታዎች በማቋቋም፣ ወዘተ መታደግ አለበት፡፡ ግዴታውም ነው፡፡ ለተጎጂዎች ትኩረት መንፈጉና ከፊት ከፊት የመጣ ሥራ ላይ ብቻ ማተኮሩ የተዳፈነን ሐዘን መቆስቆስ እንዳይሆን፣ ወይም ‹‹የዘገየ ፍትሕ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል›› እንደሚባለው እንዳይተረትበት በተቻለ መጠን በተፋጠነ ሒደት ድጋፍና ዕገዛ ማጠናከር ይኖርበታል፡፡
ብሔራዊ መግባባት
ብሔራዊ መግባባት ሲባል ሁሉም ሰው በሁሉም ጉዳዮች ላይ ይግባባል ማለት አይደለም፡፡ በጉዳዩ ላይ የተወያየ ሁሉ ተመሳሳይ አቋም ይዞ ይወጣል ማለትም አይደለም፡፡ ቢሆንም በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ ግንዛቤ መጨበጥ የሚቻለው ስንወያይና ስንነጋገር በመሆኑ፣ ‹‹እንነጋገር እንግባባ›› በማለት መንግሥት ተነሳሽነትን ወስዶ የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሙ ትልቅ ዕርምጃ ነው፡፡
ይህንን ትልቅ አገራዊ ዕድልና ተስፋ በአግባቡ ለመጠቀም ግን በዋናነት መላው የአገራችን የፖለቲካ ኃይሎች፣ በተለይ በተለያዩ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ጫፍና ጫፍ የቆሙ አካላት የቀደመ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የሲቪክ ማኅበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት፣ የዴሞክራሲ ተቋማት መሪዎች፣ ምሁራን ብሎም መላው ሕዝብም ብሔራዊ ምክክሩን እንደ ዓይኑ ብሌን እየጠበቀ፣ በመደማመጥና አንዱ በሌላው ጫማ ውስጥ በመቆም ፍሬ እንዲያፈራ መረባረብ አለባቸው፡፡ የሚዲያ አካላትና ጦማርያን ሚናም በከፍተኛ ኃላፊነት መታጀብ ይኖርበታል፡፡
እዚህ ላይ ግን ብሔራዊ መግባባትን በተመለከተ መንግሥት በጥንቃቄ ሊያስተውላቸው የሚገቡ ጉዳዮች ናቸው የምላቸውን ነጥቦች ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ብሔራዊ መግባባት ማለት የነብር ጭራ እንደ ማለት ነው፡፡ ወይ ቀድመህ አትያዝ፣ ወይ ከያዝክ አትልቀቅ ዓይነት ነገር ውስጥ የሚገቡ አካላት ሊበረታቱ አይገባም፡፡ የምክክር መድረኮቹ ለአገር ሲባል ሰጥቶ የመቀበል ባህል የሚዳብርባቸው፣ ለአብሮነትና ለእኩልነት የሚያግዙ ዕሳቤዎች የበላይነት የሚይዙባቸው፣ ትውልዱ መቻቻልና መደማመጥን እየተላመደ የሚቀጥሉ መሆን አለባቸው፡፡
እዚህ ላይ ብሔራዊ መግባባትን በሚፈጥሩ ጉዳዮች ዙሪያ እንወያይ የሚለውን ክፍተት ወይም አጋጣሚ ለመጠቀምና የራሳቸውን ዓላማ ለማራመድ ወደኋላ የማይሉ የውስጥና የውጭ ኃይሎች መኖራቸውንም ከግንዛቤ ማስገባት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር በአዋጅ ለተቋቋመው የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ተገቢውን ኃላፊነት በመስጠትና የትኛውንም ዓይነት የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት በማስወገድ፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮን እየቀመሩ ለሕዝቡ የሚበጀውን መንገድ መከተል ይገባል፡፡ የግድም ነው፡፡
‹‹እንወያይ!›› የሚል ጥሪ ሲቀርብ መጀመርያ የሚመጣው ጥያቄ በምን፣ በምን ጉዳይ ላይ እንወያይ የሚለው ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እምብዛም ከማያግባቡና እስካሁንም ከሚያነታርኩ ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌዎች መነሳት ይቻላል፡፡ ዝርዝር ጥናቱና ውሳኔው የኮሚሽኑና ተመካካሪዎቹ ቢሆንም፣ ነገር ግን እንደ ሰንደቅ ዓላማ፣ የክልሎች አከላለልና ወሰን ጉዳይ፣ የቋንቋ፣ የመሬት፣ የትምህርት ፖሊሲ መነሻዎችና የጋራ የሕግ ማዕቀፎች ሥሪት፣ እንደ ክልል ልዩ ኃይሎችን የመሰሉ ባልተጻፉ ሕጎች የተገባባቸው አደገኛ ዝንባሌዎችና ድርጊቶች፣ ወዘተ ሊታዩ ይችላሉ ብሎ መገመት አያዳግትም፡፡
ለምሳሌ ብዙዎቹ ተቃዋሚዎች በአገራችን ለሚነሳው ግጭትም ሆነ የፖለቲካ ውዝግብ መነሻው፣ ለወደፊቱም የችግር ማባባሻ የሚሆነው ብሔር ተኮር የሆነው ‹‹ሕገ መንግሥት›› ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ እናም መሻሻል ብቻ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ መቀየር አለበት፣ ይዘቱ ብቻ ሳይሆን ከመግቢያው ጀምሮ ያለው ዓረፍተ ነገር፣ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች…›› የሚለው ራሱ፣ ‹‹እኛ የኢትዮጵያ ሕዝብ›› ተብሎ አንድነታችንን በሚያጠናክር አኳኋን ይቀየር እስከ ማለት አማራጭ በመምዘዝ መፍትሔ ያመላክታሉ፡፡
በተቃራኒው በሕገ መንግሥቱ ላይ መጠነኛ መሻሻያዎች ሊኖሩ ቢችሉም፣ ዘውግ ተኮሩ ፌዴራሊዝም ሊቀየር እንደማይችልና የአገራችን የፖለቲካ ሥልጣን ፍትሐዊነት ከማንነት ጋር ተጋምዶ መታየት እንዳለበት የሚከራከሩም አሉ፡፡ ይህን መንታ ስለት ከሌላው ዓለም ተሞክሮ (ትርፍና ኪሳራ ጋር) እያዘመደ፣ በአገራችን ሕዝብ ታሪክና ማኅበረ ኢኮኖሚያዊ መስተጋብር እየፈተሸ፣ የባህል፣ የእምነትና የልማድ ስብጥራችንን እየመረመረ ውይይቱን የሚያበስል ሚዛናዊና ምክንያታዊ ምሁር ሊበራከት ያስፈልጋል፡፡ ምክክሩም በጩኸትና ብዙ ድምፅ በማሳመት ሳይሆን፣ በሐሳብ ልዕልና ክፍተቱ እየተሞላ መቀጠል አለበት፡፡
አንዳንድ ተመካካሪዎች ‹‹የባህል ፌዴራሊዝም እንጂ የብሔር ፌዴራሊዝም አያስፈልገንም›› ሊሉም ይችላሉ፡፡ የሚጠበቀው ዝርዝር፣ ሰፊና ብዙ ጭብጥ የያዘ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰማይ ሥር ያሉ ሁሉንም አወዛጋቢ የትናንትና የዛሬ ጉዳዮች የሚመለከት መሆኑ አይቀርም፡፡ እኛ ዜጎች እንደ ሕዝብ ሒደቱን በትዕግሥትና በተስፋ መከታተልና በማንኛውም የሰላምና የዴሞክራሲያዊ ሒደት የመሳተፍ ታሪካዊ ኃላፊነት እንዳለብን መዘንጋት የለብንም፡፡ መንግሥት ደግሞ ምንም ዓይነት ጊዜ ሳያባክን የብሔራዊ ምክክርና መግባባት መድረኩን ሥራ ማስጀመር፣ መደገፍና ከፍፃሜ ማድረስ ታላቅ ኃላፊነቱ ይሆናል፡፡
አሁንም ከለውጡ ማግሥት ሥልትን በአቋራጭ ለማግኘት አልያም ሁሉንም ነገር ከዜሮ ለመጀመር የሚሹ ፖለቲከኞች እየተንጓለሉ መፈናጠራቸው አይቀርም፡፡ በተጨባጭ እየታየ ያለውም እሱ ነው፡፡ አረሩም መረሩም ባለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት የተደከመባቸው የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና የተቋማዊ ዕድገት ውጤቶች መና ይሁኑ፣ ሕገ መንግሥት ይፍረስ ዓይነት ከንቱ አካሄዶች ለማንምና ለምንም አይበጁምና ተቀባይነት አይኖራቸውም፡፡ ሒደቱ ሊያስገኙ የሚችሉት ውጤቶች ማሻሻል፣ ማረም፣ ማረቅ፣ መሙላት፣ መገንባት፣ ወዘተ ላይ እንዲያተኩር ይጠበቃል፡፡
ወደፊት በተግባር እንደሚታየው መቼም የመግባባቱ ውይይት አካሄድ በዘርፍ በዘርፉ በአደረጃጀት ተደግፎ የሚካሄድ ይመስለኛል፡፡ የወጣቶች፣ የሴቶች፣ የተማሪዎች፣ የመምህራን፣ የፓርቲዎች፣ የአማኞች፣ የማኅበራት፣ የነጋዴዎች፣ የአርሶ አደሮች፣ የአርብቶ አደሮች፣ ወዘተ እየተባለ ባለድርሻ አካላትን እያሳተፈ የሚካሄድ መሆኑ አይቀርም፡፡ ይህም ነገሮችን አስፍቶና የጋራ መፍትሔ እየሰጡ ለመሄድ ይረዳል፡፡ እንግዲህ ጅምሩን ለፍሬ ያብቃው፡፡
በመጨረሻ
ችግሮች አሉ፣ እኛም እንደ ዜጋ የምናውቃቸው፡፡ መንግሥትም ዛሬ ብቻ ሳይሆን ትናንትም ያመነባቸውና ‹‹እታገላቸዋለሁ›› ብሎ ቃል የገባላቸው ችግሮች አሉ፡፡ ‹‹እናውቃለን›› ወይም ‹‹ዘዴ አለን›› የምንል ዜጎች እነዚህ ችግሮች በሚፈቱበት አግባብ መንግሥትን ብቻ ሳይሆን፣ መላው የፖለቲካ ኃይሎችን አቅጣጫ በማስያዝና ወደ መፍትሔው ለመድረስ በማገዝ አብሮ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡
ለዚህ ታሪካዊና ወሳኝ ተግባር ግን ዶሯችን ታመመች ብንላቸው፣ ‹‹በሬያችሁን እረዱላት›› የሚሉ መካሪና አማካሪዎች አያስፈልጉንም፡፡ ለዶሮዋ መድኃኒት እንፈልግላታለን እንጂ፣ ምንም ቢሆን በሬ አናርድላትም፡፡ ችግሮቻችን በጊዜ ሒደት የሚፈቱ መሆናቸውንና ለዚህም እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በዓይናችን እያየን መምጣታችን ብቻ ሳይሆን፣ ብዙኃኑ ሕዝብ በአገሩ ህልውና እንደማይደራደር በትግበራ ሲያስመሰክር የታሪኩ አካል ሆነን በማየታችን ነው፡፡ እናም በይቅርታ፣ በመደጋገፍና በመደማመጥ ታጅቦ ወደ ብሔራዊ ምክክሩ መግባት ከተቻለ የጋራ ድል መገኘቱ አይቀሬ ነው፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡