Monday, March 20, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዋሽ ወንዝ ፏፏቴን ለበለጠ የቱሪስት መስህብ ማዋል

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ ጉልህ አሻራቸውን በማሳረፍ ከሚጠቀሱት አገር በቀል ኩባንያዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፖ የአዋሽ ወንዝ ፏፏቴን አስታኮ የገነባውን ልዩ ሪዞርት በይፋ ሥራ ሲያስጀምር፣ ቀጣዩ መዳረሻው አርባ ምንጭ እንደሆነ አስታወቀ፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ በ210 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የአዋሽ ብሔራዊ ፓርክን መሠረት በማድረግ የተገነባው አዋሽ ኩሪፍቱ ሪዞርት ከሌሎች ሪዞርቶች በተለየ አገልግሎት እንዲሰጥ መታሰቡም ታውቋል፡፡ 

የአዋሽ ኩሪፍቱ ሪዞርት መጋቢት 7 ቀን 2014 ዓ.ም. በተመረቀበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ሪዞርቱ የአዋሽ ፏፏቴን ከሥር እንዲያሳይ ተደርጎ የታነፀ መሆኑን የኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፖ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ታዲዎስ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

ሪዞርቱ አሥር የመኝታ ክፍሎች እንዳሉት ይህ የተደረገበት ዋነኛ ምክንያት ወደ ሪዞርቱ የሚመጡ ቱሪስቶችና ሌሎች ተገልጋዮች በስም ጭምር በመጥራት ልዩ መስተንግዶ እንዲደረግላቸው በማሰብ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ዓይነ ግቡ የሆኑ ተፈጥሯዊ ገጽታዎችን በመመልከት ለቱሪስቶች ምቹ በሆነው ሥፍራ የተገነባው ኩሪፍቱ አዋሽ ሪዞርት፣ ከመኝታ ክፍሎቹ ባሻገር ሁለት የዋና ገንዳዎችና ሬስቶራንቶች፣ ለቱሪስቶች ያስፈልጋሉ የተባሉ አዳዲስ አገልግሎቶችንም አካቷል፡፡ የስፓና የጃኩዚ አገልግሎቶችንም ለመስጠት የሚያስችሉ ሥፍራዎች የተሰናዱለት ይህ ሪዞርት፣ የተራራ ጉዞና ዝላይ፣ የግመል ጉዞ፣ እንዲሁም በቀላሉ የተለያዩ አዕዋፋትና ሌሎች የዱር እንስሳትን ለመመልከት የሚያስችል አገልግሎቶችንም ይሰጣል፡፡

በሪዞርቱ ምርቃት ላይ የተገኙት የቱሪዝም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሌሊሴ ጫሊ፣ በአቶ ታዲዎስ የተገነባው ሪዞርት የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን አጉልቶ በማውጣት ውብ የቱሪዝም መዳረሻ መገንባት እንደሚቻል የታየበት ነው ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዋ ወ/ሮ ሰዓዳ ኡስማንም፣ ብዙ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን በይበልጥ ለማሳየትና እንዲህ ባለ መንገድ የቱሪስት ማረፊያ ቦታዎችን መሥራት እንደሚቻል በተግባር በመመልከት የአቶ ታዲዎስን አበርክቶ አወድሰዋል፡፡

ሌሎች የግል ባለሀብቶችም በተመሳሳይ ራቅ ባሉ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች ኢንቨስት ደርጉ ዘንድ ጠይቀዋል፡፡ አቶ ታዲዎስ በበኩላቸው፣ የኩሪፍቱ አዋሽ ሪዞርት ሥራ መጀመር አካባቢው ተጨማሪ የቱሪስት ማረፊያ ሥፍራዎች እንዲኖሩት ያስችላል ብለዋል፡፡

አዋሽ ፓርክን ተከትሎ ሰዎች ከእኛ በተሻለ እያሳመሩ ሚሄዱበት ጊዜ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በአጠቃላይ እየተቀየረ እንዲሄድ ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸውም አክለዋል፡፡

በቢሾፍቱ ኩሪፍቱ ላይ እንደሆነው እዚህም የቱሪስት ማረፊያዎች በሰፊው እንዲታይ እፈልጋለሁ ያሉት አቶ ታዲዎስ፣ ከዚህ በመቀጠልም እጅግ ሰፊ የሆኑ የቱሪስት መስህቦች ወዳሉበት አፋር ክልል ተመሳሳይ ግንባታዎች እንዲካሄዱ እንደሚረዳም ገልጸዋል፡፡

 በቱሪዝም ያልተነካ ሀብት ያለውና በጣም ውብና ሰዎች የማያውቋቸው የተለዩ የቱሪዝም ሥፍራዎች ያሉበት የአፋር ክልል ይህንኑ ቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ተከትሎ አምስትና አሥር ሪዞርቶች ሲሠሩ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ያድጋል የሚል እምነት አላቸው፡፡

በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አገራዊ አሻራዎች ባረፉበት የግንባታ ስልት ሪዞርቶችን በመገንባት የሚታወቀው ኩሪፍቱ ሪዞርት፣ ይህንን አገልግሎት ከጀመረ 20 ዓመቱን ይዟል፡፡ በዚህ የ20 ዓመታት ጉዞው ውስጥ የተገልጋይ አገልግሎት ልቀቱን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ አሁን ላይ ደርሷል የሚሉት አቶ ታዲዎስ፣ ከዚህም በኋላ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ፍላጎት እስኪሞላ ድረስ በዚሁ መንገድ የሚጓዙ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ቀጣይ ማረፊያቸው ደግሞ አርባ ምንጭ እንደሆነ የገለጹት አቶ ታዲዎስ፣ ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን በአርባ ምንጭ አዲስ ሪዞርት ግንባታ በቅርቡ እንደሚጀምሩ ገልጸዋል፡፡ በሰሜን ተራሮች ላይም አይናቸውን አሳርፈዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያን ልዩነት በሚያሳይ ቦታ፣ በጣም የተሻለ ደረጃ ፈጥረን ከዓለም ማንኛውም ቱሪስት ቢመጣ ተስተናግዶና አድንቆ፣ ኢትዮጵያን ልቡ ውስጥ ከትቶ የሚሄድበትን ሥራ እንገነባለን›› በማለት ገልጸዋል፡፡

የአገሪቱን ቱሪዝም ለማሳደግ እንዲህ ያሉ ግንባታዎች ያስፈልገናል ያሉት ወ/ሮ ሌሊሴ፣ አሁን ባለው አገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ቱሪዝም አንደኛው የኢኮኖሚ ምሰሶ ነው፡፡ ሰፊ የሆነ የቱሪዝም ሀብት አለን፡፡ በጣም የረዥም ታሪክ ባለቤት ስለሆንን፣ ያሉንን የቱሪዝም መዳረሻዎች የኢኮኖሚ ፋይዳቸው ከፍ እንዲል ማድረግ ይኖርብናል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

‹‹አዋሽ ፓርክ በእጅጉ የሚታወቅ ፓርክ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ውብ የሆኑ የቱሪስት ማረፊዎች ሲገነቡ የቱሪስት የቆይታ ጊዜን ያራዝማል፡፡ ጎብኚም ናፍቆ እንዲመጣ ያደርጋል›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ እንዲህ ያሉ የተፈጥሮ ሀብቶቻችንን የበለጠ አጉልቶ የሚያወጣ የአገነባብ ሥልት ብዙ ነገሮችን እንደሚቀይርም ጠቁመዋል፡፡  

በየቦታው እንዲህ ያሉ መስህቦችን እየመረጡ የማልማቱን ሥራ መንግሥትም እንደጀመረ ገልጸው፣ ነገር ግን የግል ባለሀብቱ በስፋት እንዲገባ ይፈልጋል ብለዋል፡፡  

ወ/ሮ ሰዓዳ እንደገለጹትም፣ ኩሪፍቱ አዋሽን ልዩ የሚደርገው ግንባታውን ለማካሄድም ሆነ ለውስጣዊ ግልጋሎት የሚውሉ ዕቃዎች በአገር ውስጥ በሚገኙ ዕቃዎችን መሠረት ያደረጉ በመሆናቸው የቱሪስቶችን ዕይታ በመሳብ የራሱ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል፡፡

ኩሪፍቱ ሪዞርት የመጀመርያውን ሪዞርት የከፈተው በቢሾፍቱ ኩሪፍቱ ሐይቅ ላይ ነው፡፡ በራሱ ሪዞርቶችና በሌሎች በሚያስተዳደራቸው ሆቴሎች ከ3,000 በላይ ሠራተኞች አሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች