በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ 18ቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በ2014 ዓ.ም. የመጀመርያው ግማሽ ዓመት ያገኙት ገቢ አሥር ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህ አፈጻጸማቸው ከቀደሙት ዓመታት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸርም የተሻለ ገቢ ያገኙበት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡
እነዚህ ኩባንያዎች በግማሽ ዓመቱ ካሰባሰቡት ጠቅላላ ዓረቦን ውስጥ 9.43 ቢሊዮን ብር የሚሆነው ሕይወት ነክ ካልሆነ የኢንሹራንስ ዘርፉ የተገኘ ነው፡፡ ቀሪው 563.2 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፉ የተገኘ መሆኑን የኩባንያዎቹ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ያመለክታል፡፡
በሁለቱም የኢንሹራንስ ዘርፎች በኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ የተሰበሰበው የዓረቦን መጠን ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀርም የ15 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡ በ2013 የሒሳብ ዓመት በመጀመርያው ግማሽ ዓመት ኩባንያዎቹ አሰባስበው የነበረው የዓረቦን መጠን 8.7 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ በዘንድሮ የግማሽ ዓመት አፈጻጸማቸው ከ1.2 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው የዓረቦን ገቢ አግኝተዋል፡፡
ከተሰበሰበው ጠቅላላ ዓረቦን ውስጥ 50.2 በመቶ የሚሆነውን ዓረቦን ማሰባሰብ የቻለው መንግሥታዊው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ነው፡፡ ይህም ከኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ገበያ ግማሽ ያህሉ በዚህ ኩባንያ የተያዘ መሆኑን ያመለክታል፡፡
ቀሪዎቹ 17ቱ የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከጠቅላላው የዓረቦን ገቢ ውስጥ 49.8 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የያዙ መሆናቸውን የሚያሳየው ይኼው መረጃ፣ ከ17ቱ የግል የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በግማሽ ዓመቱ ከፍተኛውን ዓረቦን ያሰባሰበው አዋሽ ኢንሹራንስ ሲሆን፣ ይህም ከኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ገበያ 7.1 በመቶ ያህሉን ድርሻ መያዙን ይጠቁማል፡፡
ከአዋሽ ቀጥሎ ከፍተኛውን ዓረቦን ያሰባሰበው ኒያላ ኢንሹራንስ ሲሆን፣ ከአጠቃላይ የኢንሹራንስ ገበያ 5.2 በመቶ የገበያ ድርሻ እንደያዘ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በዘንድሮው የግማሽ ዓመት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሥራ ክዋኔ ለየት ብሎ ሊጠቀስ የሚችለው አፈጻጸም ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ የተሰበሰበው የዓረቦን መጠን ከሌላው ጊዜ በተለየ ከፍተኛ የሚባል ዕድገት የታየበት መሆኑ ነው፡፡
ከ18ቱ የኢንሹራስ ኩባንዎች የሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን የሚሰጡት አሥራ አንዱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በግማሽ ዓመቱ ከሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ያሰባሰቡት የዓረቦን መጠን በ53.2 በመቶ ብልጫ አሳይቷል፡፡
አምና በተመሳሳይ ወቅት ከሕይወት ኢንሹራንስ ሽፋን ኩባንያዎች አሰባስበው የነበረው የዓረቦን መጠን 367.8 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ ዘንድሮ ግን የዓረቦን መጠኑ የ195 ሚሊዮን ብር ብልጫ በማሳየት 563.2 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡
በግማሽ ዓመት ከ53 በመቶ በላይ ብልጫ የታየበት ገቢ ማስገኘት የቻለው የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ ምናልባትም በኢንዱስትሪው እስከዛሬ ያልታየ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ እጅግ ወደኋላ የቀረችና አሁንም ከጠቅላላው የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ገበያ አንፃር ሲታይ የሕይወት ኢንሹራንስ ድርሻ ከአምስት በመቶ ያነሰ ሆኖ መቀጠሉን ያመለክታል፡፡
በዘንድሮ ግማሽ ዓመት ከሕይወት ኢንሹራንስ ዓረቦን አሰባሰብ ጋር በተያያዘ ለየት ብሎ የታየው ሌላው ክዋኔ ደግሞ፣ ኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጄኔራል ኢንሹራንስ ኩባንያ በዘርፉ ከፍተኛ ዓረቦን ማሰባሰብ መቻሉ ነው፡፡
በስድስት ወራት ውስጥ ከአሥራ አንዱ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከተሰበሰበው የሕይወት ኢንሹራንስ ዓረቦን ውስጥ ኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጄኔራል ኢንሹራንስ ኩባንያ 128 ሚሊዮን ብር አሰባስቧል፡፡ ይህም ከጠቅላላ የሕይወት ኢንሹራንስ ገበያ 22 በመቶውን እንዲይዝና ቀዳሚ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
በቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት በሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ በዓረቦን አሰባሰብ ይዞት የነበረው ደረጃ አራተኛ እንደነበር መረጃው ያመለክታል፡፡
ኢትዮ ላይፍ በግማሽ ዓመቱ ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 245.9 በመቶ ወይም የ91 ሚሊዮን ብር ዕድገት ያለው ነው፡፡
ከኢትዮ ላይፍ ቀጥሎ ከሕይወት ኢንሹራንስ ከፍተኛ ዓረቦን ያሰባሰበው ኒያላ ኢንሹራንስ ሲሆን፣ በግማሽ ዓመቱ ያገኘው ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ64.5 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
ከጠቅላላ የኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ገበያ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን የያዘው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ከሕይወት ኢንሹራንስ ያገኘው ገቢ በኢንዱስትሪው በሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በዘንድሮ ግማሽ ዓመት ከሕይወት ኢንሹራንስ የዓረቦን አሰባሰብ ከፍተኛ ዕድገት አስመዝግበዋል ተብለው ከሚጠቀሱት ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ገቢውን በ121.4 በመቶ ማሳደግ መቻሉ ታውቋል፡፡
የዘንድሮ የግማሽ ዓመት አፈጻጸም በሁለቱም የኢንሹራንስ ዘርፎች በድምር ዓረቦን ገቢያቸውን በማሳደግ ተጠቃሽ ከሆኑ ኩባንያዎች መካከል ኢትዮ ላሌፍ ኤንድ ጄኔራል ኢንሹራንስ፣ ቡና ኢንሹራንስና ኒያላ ኢንሹራንስ ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ሦስት ኩባንያዎች በግማሽ ዓመት ውስጥ ያገኙት ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከ40 በመቶ በላይ ዕድገት አሳይቷል፡፡
በተለይ ኢትዮ ላይፍ ኤንድ ጄኔራል ኢንሹራንስ አ.ማ. በ2014 ግማሽ የሒሳብ ዓመት ከሁለቱም የመድን ዘርፎች ያገኘው ጠቅላላ የዓረቦን ገቢ በ92.6 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ 267 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ ችሏል፡፡
ቡና ኢንሹራንስ ደግሞ የግማሽ ዓመት ገቢውን በ55.6 በመቶ በማሳደግ 242.8 ሚሊዮን ብር ማሰባሰብ መቻሉን ይኼው መረጃ ያስረዳል፡፡
ከአንጋፋዎቹ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ ደግሞ የዘንድሮውን የግማሽ የሒሳብ ዓመት በ45.4 በመቶ ማሳደግ የቻለው ኒያላ ኢንሹራንስ ነው፡፡ ኒያላ ኢንሹራንስ በግማሽ ዓመቱ ከሁለቱም ዘርፎች ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን 516.4 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ በቀዳሚው ዓመት በተመሳሳይ ወቅት አግኝቶት የነበረው የዓረቦን ገቢ 355.1 ሚሊዮን ብር በመሆኑ የ161.3 ሚሊዮን ብር ብልጫ አሳይቷል፡፡
ከግማሽ ዓመቱ ሪፖርት መረዳት እንደተቻለው፣ ከሁለት ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሌላ ሁሉም የዓረቦን ገቢያቸውን ከ3.5 በመቶ እስከ 92.6 በመቶ ማሳደግ ችለዋል፡፡
የግማሽ ዓመቱ የዓረቦን ገቢው ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ ቅናሽ ያሳየው አፍሪካ ኢንሹራንስ ነው፡፡ ኩባንያው አምና በመጀመርያው የግማሽ ዓመት 350.3 ሚሊዮን ብር ዓረቦን የሰበሰበ ቢሆንም፣ በዘንድሮ ግማሽ ዓመት የሰባሰበው 299 በመቶ በ50.4 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህም በ14.4 በመቶ የዓረቦን ገቢ መቀነሱን ያመለክታል፡፡