Monday, March 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ከመርጦ አልቃሽነትና ከአጨብጫቢነት ይሰውረን!

ሰላም! ሰላም! ዘመነ ወከባና ሩጫው እንዴት ይዟችኋል? አንዳንዴ ሐሞት ያፈሳል አይደል? ይህች ዓለም ያለ ድካም አትሞከርም፡፡ ማለቴ ካልደከመው የሚበረታ፣ ካልታከተው የሚጠነክር ያለ አይመስልም። እንኳን ሩጠን ቁጭ ብለን የሚደክመን እኮ እየበዛን ነን፡፡ ታዲያ ይኼን ጊዜ ሰው ማለት ስስ ጎኑ የበዛ ፍጡር መሆኑ ይገባናል። በተለይ እኛ አዳሞች በስስ ጎንና በጎን አጥንት በኩል ጉድለታችን ብዙ ነው። ምን ለማለት እንደፈለግኩ ገብቷችኋል። በዚህ ጥድፊያና ሁካታ በበዛበት ዓለም በመወሰን የራስን ሔዋን ሳይዙ ጉዞ አደጋው ከፍ ያለ ነው። እውነቴን እኮ ነው፡፡ ‹‹መልካም ሴት ለባልዋ ዘውድ ናት›› የተባለውን አላነበባችሁም? ቆይ እስኪ የማንበብ ባህል ያላዳበረ ኅብረተሰብ ሲሠለጥን የታየው የት ነው? ማንበብ የሚሉት ወሳኝ ጉዳይ ብዙውን ሰው ለምን ያንገሸግሸዋል? ማንበብና ማገናዘብ እያቃተን መሰለኝ በረባ ባልረባው የምንናጨው፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ የምንገዳደለው፡፡ ይህም አልበቃ ብሎ ሰውን የመሰለ ሰብዓዊ ፍጡር ከእነ ሕይወቱ እሳት ውስጥ የምንከተው፡፡ ዘንድሮ ሰይጥነናል!

እንደ አዛውንቱ ባሻዬ አስተያየት ያለ ሴቶች የሚደረግ የሕይወት ጉዞ እንኳን ለሥጋ ለነፍስም አይረባም። ታዲያ ሁሌም የሚገርመኝ ሴቶች እንዲህ ዓይነቱ ማሰሪያ አንቀጽ ላይ ሚናቸው መጉላቱ ብቻ አይደለም። ከእነሱ ውጪ የሚመራ ሕይወት የሚባለው ነገር አሰልቺ ከመሆን አልፎ በጭካኔ የተሞላ መሆኑን ማን ይክዳል? እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ዕድሜ ለውዷ ባለቤቴ ለማንጠግቦሽ ሁሌም ድርጊቴ ከግፍና ከጭካኔ የፀዳ ነው። አንዳንዱ ግን ትዳርን በሚያህል ትልቅ ቁምነገር ላይ ኮንትሮባንድ› ከመሥራት አልፎ የኃጢያት ባሪያ ነው ይባላል። ይወሰልታል ብቻ ሳይሆን ግፈኛ ነው ለማለት ነው። ትዳር ጣፋጭ ነው እንደ ማርባለበት አፉ ሌላ ከመሳም አልፎ አስገድዶ መድፈርና ግድያ ውስጥ ይዘፈቃል። ‹‹የሰይጣ ዘመን›› አሉ አዛውንቱ ባሻዬ፡፡ እውነታቸውን እኮ ነው፡፡ አይደለም እንዴ!

ውዷ ማንጠግቦሽና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ የፍቅርን ነገር ካነሱ ሳይተራረቡ አይላቀቁም። ‹‹አይ የሴቶች ነገር?›› ይላታል። ‹‹አይ የወንዶች ነገር?›› ትለዋለች። ‹‹ደግሞ ወንዶች ምን አደረጉ?›› ሲላት፣ ‹‹ሴቶችስ ምን ኃጢያት ተገኘባቸው?›› ትለዋለች። ጎራ ለይተው አንዳቸው የአንዳቸውን ፆታ ገመና ሲዘከዝኩ ይኼ ሁሉ ድርጊት ድራማ ነው? ወይስ በዕውኑ ዓለም የተፈጸመ ነው? እላለሁ፡፡ እናም መሀል እሆንና የሁለቱንም ‹‹ጠቅልለህ ውቃ›› ወግ በትዝብት አዳምጣለሁ። ምነው የዘንድሮ ወግ ሁሉ የጅምላ ብቻ ሆነ? ፈረንጆቹ ‹‹ጄኔራላይዜሽን›› የሚሉት የጅምላ ፍረጃ ትክት ሲለኝ ብቸኝነት ያምረኛል፡፡ ይኼ የጅምላ ፍረጃ ከላይ እስከ ታች ይወርድና አዳሜን በፆታ፣ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በቋንቋና በአስተሳሰብ ሲያባላ የዴሞክራሲ ዳር ድንበሩ ይጠፋብኛል፡፡ በፆታ የተጀመረው ውጥንቅጥ ወደ አጠቃላዩ ማኅበረሰብ ሲሸጋገር ግራ ግብት ይላል እኮ? እንዲህ አይደል እንዴ ነገር የምንጀምረው!

ማንጠግቦሽና የባሻዬ ልጅ ቀልዱን ትተው ከልባቸው ሲጫወቱ ማንጠግቦሽ፣ ‹‹የሴቶች ጥቅምና አስተዋጽኦ ብዙ ሆኖ ሳለ ለእኩልነታቸው ተጋሁ የሚለው መንግሥት ግን፣ አስተማማኝ የሕግ ከለላ አላረጋግጥልን ብሎ በጠራራ ፀሐይ በማንም ወረበላ እንገደላለን…›› ብላ ትኮሳተራለች። ‹‹እኔ ምለው ግን ማንጠግቦሽ? ራሳችሁ የሴቶች ማኅበር አላችሁ አይደል እንዴ? ምነው ለራሳችሁ እናንተው ብትታገሉ?›› ሲላት ዓይን ዓይኗን እያየ፣ ‹‹እኛ ብቻ እናውቅላችኋለን የሚሉ አገር ምድሩን ሞልተውት እንጂ መቼ መተባበሩን ጠላን?›› ትለዋለች። ታዲያ ምን እንደሚነካኝ አላውቅም እንዲህ ዓይን ዓይኗን ሲያይብኝ ቅናት ነገር ይጀማምረኛል። መቼም ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ባይሆን ኖሮ ልቤ ሌላ ይጠረጥር ነበር። ምን ነካችሁ? ‹ሰውን ማመን ቀብሮ ነውአይደለም እንዴ የተባለው? ለነገሩ ዛሬ የበፊቱ ተረት እየተናቀና እየተለዋወጠ ስለሆነ ቢረሳችሁ አልፈርድባችሁም። ‹‹የዘንድሮን ሰው ማመን ደውለው ከተገናኙ በኋላ ነውሲባል ሰማሁ በጆሮዬ። መቼም ደላላና ጆሮ በየሄዱበት የማይሰሙት የለም። ዘንድሮ እኮ ጆሮ ባልተረጋገጠ ወሬ ከመደንቆር አልፎ ሊበጠስ ምንም አልቀረውም፡፡ አሸር ባሸር ወሬ በዝቶ እኮ ነው!

ታዲያ ጨዋታ ነውና የሰሙትን ማሰማት መልካም ነገር ይመስለኛል። ባለፈው ሳምንት አንድ ልጅ እግር ደላላ በእግር በፈረስ አስፈልጎ አገኘኝ። ‹‹ምነው በሰላም ነው?›› አልኩት። ‹‹ኧረ ጋሽ አንበርብር ሰው ሊበላኝ ነው…›› አለኝ ሰላምታውን በቅጡ ሳይጨርስ። ‹‹ለምን ተብሎ?›› አልኩት ደንገጥ ብዬ። ለሥራው አዲስ ስለሆነ ምን ችግር ገጠመው እያልኩ አብሰለስላለሁ። የእኛን አገር ነገር ታውቁታላችሁ። አዲስ የሥራ ቅጥር ማስታወቂያ ይወጣና በአምስትና በአሥር ዓመት የሥራ ልምድ ጥያቄ ይጨናነቃል፡፡ ‹‹የእዚህ አገር ነገር እንደ ገብስ ቆሎ መታሸት ነው…›› ያለኝን አንድ ሥራ ፈላጊ ወጣት አስታውሳለሁ። ‹‹እንዴት?›› ስለው፣ ‹‹የትምህርቱ መመዘኛ ተሟልቶ የልምዱ ጥያቄ ሲነሳ ለዓመታት ያሻል። ያ በልምድ የታሸው በተራው ቀጣሪ ሲሆን፣ ማን ታሽቶ ማን ይቀራል ዓይነት የእልህ የሚያስመስል መመዘኛ ያወጣል…›› ብሎኛል። አሁንስ ይታክታል!

ሁሉም ተማሪ ሁሉም ለማጅ ሆኖ ባያልፍ ግን ምን ይውጠን ነበር ወገኖቼ? አንዳንዱ ከእናቱ ሆድ ይዞት የወጣ ይመስል ያለ እኔ ማን አለ እያለ አገር ይበጠብጣል። ይኼ ወጣት ደላላ ምን አለኝ መሰላችሁ? ‹‹ወንዱ ሚስት፣ ሴቱ ባል ፈልግልኝ እያለ አስቸገረኝ…›› አይለኝ መሰላችሁ? እናማ ጨዋታ የያዘ ስለመሰለኝ ከት ብዬ ሳቅኩበት። ፍቅር በድለላ፣ ትዳር በፎርሙላ ከቶ የት አገር ታይቶ ይሆን? መቼም እኛ ከውጭ አገር ልምድ በመቅሰም፣ ቀስመንም የሚረባውን ከማይረባው ባለመለየት በአፍሪካ የመጀመርያዎቹ ሳንሆን አንቀርም። ይህች ‹‹አንደኛና የመጀመርያ›› ሳትሆን ትቀራለች መጨረሻ ላይ የወረወረችን? መጠርጠር ደግ ነው፡፡ ያልጠረጠረ ተመነጠረ›› ነዋ፡፡ ግን ማን ነቅቶ!

ለማንኛውም በዚህ ወከባው ፋታ አልሰጥ ባለበት ሰዓት አንዳንዴ ቆም እያሉ እርስ በርስ መገማገምና ራስንም መገምገም ቢለምድብን ጥሩ ነበር። በተለይ የራስን አካሄድ ከማወቅና ከመገምገም በፊት የሌላው ባይቀድም እንዴት ሸጋ ነበር መሰላችሁ? ባሻዬን፣ ‹‹ዘንድሮ እኮ ሰው መጠቋቆሙን አበዛው…›› አልኳቸው። ፊታቸው በሐሳብ ጉም መስሎ ቆይተው፣ ‹‹እንደ መፍረድ ምን ቀላል ነገር አለ ብለህ ነው ልጅ አንበርብር? እንግዲያማ መጽሐፉ ይል የነበረው የራስህን ጉድፍ ሳታጠራ የጓደኛህን ማጥራት አይቻልህም ነው። አይ እኛ? አሁንም ራሳችን ግራ እየገባን ሌላውን ግራ ማጋባት መደበኛ ሙያ አደረግነው መሰለኝ?›› አሉኝ በከፍተኛ ሐዘን ተውጠው። እውነታቸውን ነው!

የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹የዴሞክራሲ አንዱ ጥቅም የተለያዩ አመለካከቶችን ወይም አስተያየቶችን ሰምቶ የሚጠቅመውን መውሰድ ነው፡፡ ሌሎችም መደመጥ ስላለባቸው ይህንን ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ የዴሞክራሲ ፀጋ ነው…›› ብሎኝ ነበር። ታዲያ ይኼ ራስን ሳይገመግሙና ሳይመዝኑ እንዴት ይሆናል? የእኛ ትልቁና ዋናው በሽታ እኮ ስለራሳችን መስማት የማንፈልጋቸው እውነታዎች ብዙ መሆናቸው ነው። እውነቴን እኮ ነው ለምን ብዬ እዋሻለሁ? እናም በዚህ በደረስንበት ዘመን ዕድሉን ተጠቅመን ቁጭ ብለን የነበረውን ተረት፣ አባባል፣ ወግና ልምድ ስንከልስ ከምንውል አኗኗራችንና ስለራሳችን ያለንን አመለካከት ብንቀይር ምን ይለናል? ‹‹የተለየ አስተያየትና ሐሳብ መስማት የማይወዱ ወገኖቻችን በአንድ ማርሽ ብቻ የትም እንደማይደረስ ብንጠቁማቸው፣ ለአገር ትልቅ ነገር እንዳበረከትን ይቆጠራል…›› የሚል ምክር የለገሰኝ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ መማር እንዲህ ነው!

በነገራችን ላይ ባለፈው ሳምንት የገዥው ብልፅግና ፓርቲ ሰዎች ጉባዔ ተቀምጠው ነበር። እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ እንዳነሳው ልብ በሉ። በአገራችን ቀበኛ ሌቦችን በጉያው ሸጉጦ ተንከባክቦ በመኖር የሚታወቅ መንግሥት የሚመራው ብልፅግና ፓርቲ መሆኑን ብዙ የተባለበት ነው፡፡ አሁን ደግሞ በዙሪያ መለስ ችግሮቻችን ላይ ውይይት አደረገ መባሉና ትኩረት መሳቡ አያስገርመኝም። ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ስለአገሩ ድህነትና ኋላቀርነት በቁጭት፣ በንዴት፣ አንዳንዴ ደግሞ በስሜት ይናገር የነበረው መቼም አይረሳኝም፡፡ ‹‹በእኛ በኩል ለኋላቀርነታችን መንስዔው ያልተለወጠው አስተሳሰባችን ሲሆን፣ በመንግሥት በኩል ደግሞ የድህነታችን ዋናው ምክንያት ሥራን በአግባቡ ከሚሠሩ ይልቅ የሕዝቡን ሀብት የሚዘርፉትን በመሰብሰቡ ነው…›› ከዓመታት በፊት ማለቱ አይረሳኝም። አይደለም እንዴ!

አንድ ደንበኛዬ ባለፈው ሰሞን ለአንዲት ተራ ጉዳይ እየተበሳጨ መቶ ሺሕ ብር በጥሬው መሸጎጥ ግድ ሆነበትና ጉዳዩን አስጨረሰ። ከመስጠቱ በፊት ግን የተጨቃጨቀውን ሲነግረኝ ውሸቱን መስሎኝ ነበር። ደንበኛዬ ጉዳይ የሚፈጽምለትን፣ ‹‹እባክህ ጉዳዬን ቶሎ ፈጽምልኝ…›› ይለዋል። ‹‹ነገርኩህ እኮ በዚህ የኑሮ ውድነት እንዴት እንዲህ እንጨካከናለን?›› ካለው በኋላ ጉዳይ ፈጻሚው፣ ‹‹እንዲህ ስትጨቃጨቅ ግሽበቱ ኪስህ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ያተንልህና ታርፈዋለህ…›› እንዳለው አጫወተኝ። ‹‹አንዳንዶቹ እኮ ጉቦ ሲጠይቁ የቫት ደረሰኝ አምጡ ቢባሉ ከመስጠት አይመለሱም…›› ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ ነገሩ ሌብነትን የሚያጋልጡ ከለላ ባጡበት በዚህ ዘመን መስጠት እንዴት ወንጀል ይሆናል? ወይ አገርና ጉቦ? ወይ ታሪክና እውነታ? በእኔ ሞት ዕውን ኢትዮጵያ የቅኖች መናኸሪያ ናት? ወይስ የሌቦች ዋሻ ናት? ኧረ ግራ ገባን!

ከባሻዬ ልጅ ጋር የማይቀርበት ለቅሶ ለመድረስ አንድ ወዳጄ ዘንድ ሄድን፡፡ የአያቱን ሞት ተረድቶ አንድ ሳምንት ሐዘን የተቀመጠው ወዳጄ እንዳያኮርፈኝ በማለት ነው ሳልወድ የሄድኩት እንጂ፣ መተከል ውስጥ የተፈጸመው ግፍ ልቤን ስብር አድርጎት መቶ ዓመት ያለፋቸው አዛውንት ከድካም በማረፋቸው ንክች አላደርገውም ነበር፡፡ ‹‹ሰልስት አትድረሱ›› በሚባልበት በዚህ ዘመን ወዳጄ ማስኩን አፉ ላይ ግጥም አድርጎ ከቢጤዎቹ ጋር ካርታ እየተጫወተ ነበር፡፡ በዚህ ቅልጥ በሚያደርግ ወበቅ አንዳች የሚያህል ጋቢ ተከናንቦ ኩይሳ መስሎ የአያቱን ሐዘን በካርታ ቁማር የሚያረሳሳው ወዳጄ ኮስተር ቢልብኝም፣ ‹‹እግዜር ያጥናህ›› ማለቴ ግን አልቀረም፡፡ ይኼው ወዳጄ ዘግቶኝ ካርታው ላይ ቢያተኩርም፣ እንደ እኔ በመገረም ከሚመለከተው የባሻዬ ልጅ ጋር በሹክሹክታ ወግ ያዝን፡፡ እንደ እኔ የዚህን ሰው ኩርፊያ ፈርቶ የመጣ ሌላ ሰው፣ ‹‹ለቅሶ ከተቀመጠ ይኼው ሰባት ቀኑ አለፈ፡፡ ከዚህ ሁሉ ቀን በኋላም ተቀምጦ ይቆምራል፡፡ ሰው ለምን ለቅሶ አልደረሰኝም ብሎ ያኮርፋል ሲሉ መጣሁ እንጂ ድርሽ አልልም ነበር…›› አለን ተንገፍግፎ፡፡ እኔም የእሱን ሐሳብ እንደምጋራ ስነግረው ሰውየው ደስ ብሎት ወግ ጀመረ፡፡ እንዲህ ነው እንግዲህ!

‹‹ይኼን እንኳ ተወው የልማድ እስረኛ ስለሆነ ነው፡፡ አሉ እንጂ ተምረዋል፣ ብዙ ልምድ አካብተዋል፣ ሌሎችን ማስተማር ይችላሉ የሚባሉት ታጥቦ ጭቃ የሚሆኑት…›› አለን፡፡ ወሬውን ፈልጌያለሁና፣ ‹‹ለምሳሌ?›› አልኩት፡፡ ‹‹ምን ሩቅ አስኬደህ ዙሪያህን አትመለከትም? ከጎረቤትህ ጀምር፣ መሥሪያ ቤትህ ድረስ፣ ትልልቅ የመንግሥት ተቋማትን አስስ፣ አንቱ የተባሉ ፖለቲከኞች ጭምር ተመልከት፡፡ አንድ ዓይነት አመለካከት፣ ፍላጎትና ስሜት ታነባለህ፡፡ ኧረ ጎበዝ ለየት ያለ ነገር አስተዋውቁን ይኼ ሰለቸን እኮ ስትል አንድ ታርጋ ይለጠፍብህና ትፈረጃለህ፡፡ ልማዳዊ ድርጊት ሠልጥኖ የተሻለ አመለካከት ወይም ለውጥ ሲመጣ ጉዳዩ ሳይገባው ሊገነድስ የሚነሳው ይበዛል፡፡ ነገራችን ሁሉ አድሮ ቃሪያ ሆኗል፡፡ አሁን ደግሞ እንደምናየውና እንደምንሰማው ሰይጣናዊ ድርጊቶቻችን እየገዘፉ ሰውን የመሰለ ሰብዓዊ ፍጡር ከእነ ሕይወቱ እሳት ውስጥ እየከተትን ነው…›› እያለ ሲንገፈገፍ ትካዜ ውስጥ ገባሁ፡፡ ያስተክዛል!

ከሐዘኑ ቤት ተሰናብተን ስንወጣ ይኼ የተባረከ ሰው ጎጂ ልምዶች ምን ያህል እየተጫወቱብን እንዳለ በሚገባ የነገረንን እያሰላሰልኩ ነበር፡፡ አዲሱን ትውልድ ከእንዲህ ዓይነቶቹ ጎጂ ድርጊቶች የመጠበቅ ሞራላዊ ኃላፊነት እንዳለብን አስገነዘበን፡፡ መንታ መንገድ ላይ ደርሰን ስንሰነባበት፣ ‹‹ወንድሜ እዚህ አገር ከመጠን በላይ ያስቸገረው ከአንጀት ሳይሆን ከአንገት መንሰቅሰቅ ነው፡፡ አገር ሰላም ነው ብለህ የልብህን ስትናገር በጅምላ ተፈርጀህ  ትጠላለህ፣ በጅምላ ተፈርጀህ ትወነጀላለህ፣ በጅምላ ተፈርጀህ መብትህን ትቀማለህ፣ በጅምላ ተፈርጀህ ትሳደዳለህ፣ በማንነት ተለይተህ ትገደላለህ…›› እያለ ተብሰለሰለ፡፡ ለአስተያየቱ አመሥግኘው ስንሰነባበተው፣ ‹‹ወንድሜ ከአንገት በላይ ፈገግ እያሉ አንጀትህን ከሚቆርጡ ይጠብቅህ፡፡ ከመርጦ አልቃሾችና ከአጨብጫቢዎች ይሰውርህ፡፡ አንተም መርጦ አልቃሽና አጨብጫቢ አትሁን…›› ሲለኝ ድምፄ ከአድማስ ማዶ እስከሚያስተጋባ ድረስ ‹‹አሜን!›› አልኩት፡፡ ከአንገት ሳይሆን ከአንጀቴ ነው፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት