- ተጨማሪ 82 ድርጅቶች ተመዝግበው ከመንግሥት ጋር በንግግር ላይ ናቸው ተብሏል
በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ 28 የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በግንባታ ላይ መሆናቸውን፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።
በምግብ ማቀነባበር ዘርፍ ለመሰማራት የሚፈልጉ ኩባንያዎች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ለመሥራት ፍላጎት እያደገ መሆኑንና ከ110 በላይ ድርጅቶች ዘርፉን ለመቀላቀል በሒደት ላይ መሆናቸውን፣ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ልማት ዳይሬክተር አቶ አያልነህ አባዋ ለሪፖርተር ገልጸዋል።
ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ ገብተው በምግብ ማቀነባበር ዘርፍ ለመሰማራት ፍላጎት ካሳዩ ድርጅቶች መካከል፣ 28 ያህሉ የፋብሪካ ግንባታ መጀመራቸውን አስረድተዋል፡፡ ፋብሪካዎቹ በ2014 በጀት ዓመት ውስጥ ፈቃድ ያገኙ መሆናቸውን፣ ግሉኮስና የተለያዩ ምግቦች በማቀነባበር ሥራ ላይ እንደሚሰማሩ ገልጸዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ በምግብ ማቀነባበሪያ ዘርፍ ሰባት ፋብሪካዎች ብቻ መኖራቸውን ገልጸው፣ በተለይም በአቮካዶ ዘይት ምርት ላይ እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
በ2014 በጀት ዓመት ስምንት ወራት ውስጥም ድርጅቶቹ ከ300 ሺሕ ሊትር በላይ የአቮካዶ ዘይት ለሆላንድ ገበያ በማቅረብ፣ ከሦስት ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን አቶ አያልነህ ጠቁመዋል፡፡ የሚገነቡት የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች በተለይም በሐዋሳ፣ በይርጋለምና በቡሬ አግሮ ኢንዱስትሪዎች ውስጥ እንደሚገኙ፣ በማምረት ላይ የሚገኙት ደግሞ በይርጋለም አግሮ ኢንዱስትሪ ውስጥ መሆናቸው ተገልጿል።
አግሮ ኢንዱስትሪዎችን ከአርሶ አደሮች ጋር በማስተሳሰር የግብዓት አቅርቦት ችግር እንዳይኖር በማድረግ፣ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል። እስካሁንም ከ135 ሺሕ በላይ አርሶ አደሮች ከፓርኮቹ ጋር ተሳስረው አቮካዶን ጨምሮ ሌሎችም ምርቶችም ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
በመቋቋም ላይ ከሚገኙት ፋብሪካዎች በተጨማሪ 82 ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር ንግግር በማድረግ ላይ መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ አያልነህ፣ አስፈላጊውን መሥፈርት የሚያሟሉት ድርጅቶች ወደ ፋብሪካ ግንባታ እንደሚገቡ ገልጸዋል። በመገንባት ላይ ካሉትና በንግግር ላይ ከሚገኙት ፋብሪካዎች ውስጥ 80 በመቶ የሚሆኑት የአገር ውስጥ መሆናቸውን ተናግረዋል።