በመንግሥትና በተለያዩ ኩባንያዎች አማካይነት ወደ አገር ውስጥ ገብተው፣ ለበርካታ ዓመታት ጥቅም ላይ ሳይውሉ ተከማችተው የሚገኙ ኬሚካሎችን ለማስወገድ ተጀምሮ የነበረው ሥራ፣ የተፈለገው ገንዘብ ባለመገኘቱ መስተጓጎሉ ተገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ የሆነ አደጋ ሊያስከትሉ ይችላሉ የተባለውና የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸው ኬሚካሎች ክምችት በተለያዩ መጋዘኖች እንደሚገኝ በመግለጽ፣ የማስወገድ ሥራው ከለጋሽ አገሮች በሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና የባዮ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በዘርፉ ዓለም አቀፍ ልምድ ካላቸው ባለሙያዎች ጋር በመተባበር፣ ኬሚካሎቹ ስለሚወገዱበት ሁኔታ ጥናት መጀመሩ የተገለጸው ሚያዚያ 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ነበር፡፡
በ2013 ዓ.ም. መረጃውን ለጋዜጠኞች የሰጡትን የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሐጂ ኢብሳ፣ ማክሰኞ መጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ.ም. ሪፖርተር የአወጋገዱ ሒደት ምን ላይ ደረሰ ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ኬሚካሎችን ለማስወገድ ከለጋሽ አካላት ይገኛል ተብሎ የታሰበው ገንዘብ፣ ከአገሮቹ ጋር በነበረው ሁኔታ እንደተጠበቀው ባለመሄዱ፣ ኬሚካሎችን የማስወገድ ሥራው በታሰበለት ጊዜ እየሄደ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ተጀምሮ የነበረውንና የተቋረጠውን የአወጋገድ ጥናት ለመቀጠል የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች መኖራቸውን አቶ ሐጂ ጠቁመዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ውጪ በተለያዩ አካባቢዎች፣ የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን ኬሚካሎች ለማስወገድ የሚያግዝ የኬሚካል አወጋገድ ሥርዓት አለመኖሩ በተደጋጋሚ ሲነሳ ይስተዋላል፡፡
በተለያዩ ሥፍራዎች የሚገኙ ተቀጣጣይ የኬሚካሎች ክምችቶች ከፈነዱ በሰዎችና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስከትሉ ይችላሉ ከተባሉት ውስጥ፣ በበርካታ ድርጅቶች መጋዘን ይገኛሉ የተባሉት የግብርናና የኢንዱስትሪ ኬሚካሎች ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ተከማችተው የሚገኙ ዲዲቲ፣ ኦርጋኖ ፎስፌትና ኦርጋኖ ክሎሪን ኬሚካሎችን ለማስወገድ ከ4.5 ሚሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ፣ አዲስ ማለዳ ጋዜጣ ከአንድ ዓመት በፊት የአካባቢ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽንን ዋቢ አድርጎ ዘግቦ ነበር፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ 383 ያህል ኬሚካሎች የተከማቹባቸው መጋዘኖች እንዳሉ፣ በእነዚህ መጋዘኖችም 1‚300 ቶን ዲዲቲና ኦርጋኖ ክሎሪን የተሰኙ ኬሚካሎች መኖራቸውን የኮሚሽኑ መረጃ ያመላክታል፡፡
በተመሳሳይ ዜና በ189 በመንግሥት ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች ተሸጠው እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ገቢ ሊያስገኙ ይችላሉ የተባሉና በተለያዩ ተቋማት ተከማችተው ከሚገኙ የመንግሥት ንብረቶች ውስጥ፣ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ 22 ሚሊዮን ብር መገኘቱን ከመንግሥት ግዥ አገልግሎት መሥሪያ ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የመንግሥት ግዥ አገልግሎት በ2014 በጀት ዓመት ስድስት ወራት በፌዴራል መሥሪያ ቤቶች እንዲወገዱ ውሳኔ ከተሰጠባቸው ንብረቶች፣ በበጀት ዓመቱ የመጀመርያ ግማሽ ዓመት ከ14 ፌዴራል ባለበጀት መሥሪያ ቤቶች 29 ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችን በሽያጭ በማስወገድ 14.4 ሚሊዮን ብር መገኘቱ ተገልጿል፡፡
በተጨማሪም ሁለት ተቋማት ውስጥ ተከማችተው የነበሩ 141 ሽሕ ኪሎ ግራም ቁርጥራጭ ብረቶችን፣ ቆርቆሮዎችንና አልሙኒየሞች በሽያጭ በማስወገድ 4.5 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም በ14 ተቋማት ያገለገሉ ንብረቶችን በመሸጥ 3.8 ሚሊዮነ ብር ገቢ ተገኝቷል ተብሏል፡፡
አቶ ሐጂ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በሁሉም ባለበጀት የመንግሥት ተቋማት በየመሥሪያ ቤቱ ያለ ሥራ የቆሙ ተሽከርካሪዎች ተጣርተው እስከ ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ እንዲወገዱ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡
ይሁን እንጂ በየተቋማቱ ተከማችተው የሚገኙት ተሽከርካሪዎች መቼ እንደገቡ፣ እንዴትና በማን እንደተገዙ፣ በምን ያህል ገንዘብ እንደተገዙና አሁን ያሉበትን ሁኔታ ለማጣራት ጊዜ ስለሚያስፈልግ ተቋማቱ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. የሚሄዱበት ርቀት ታይቶ በመጨረሻ ግምገማ ይደረግበታል ብለዋል፡፡