ከአንድ ወር በፊት ተዘጋጅቶ ለአሜሪካ ምክር ቤት የውጭ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የቀረበው ኤችአር 6600 የተሰኘው ረቂቅ ሕግ፣ ዛሬ ረቡዕ መጋቢት 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ለአገሪቱ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ይሰጥበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከኢትዮጵያ የሰሜን ክፍል ጦርነት ጋር በተገናኘ በሰብዓዊ መብት ጥሰት በተሳተፉ አካላትና በጦርነቱ ተጠያቂ ናቸው ባላቸው ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ ለመጣል ያለመው ኤችአር 6600፣ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምታደርገውን የደኅንነትና የንግድ ድጋፍ እንድታቆምና ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ዕርዳታና ብድር እንዳታገኝ ክልከላ እንዲደረግ ማስቻል የሚሉ ሐሳቦችን የያዘ ረቂቅ ሕግ ነው።
በተጨማሪም በጦርነቱ ተሳትፈዋል በተባሉ የኢትዮጵያና የኤርትራ የፀጥታ ተቋማት፣ ባለሥልጣናትና የመንግሥት አካላት ላይ ጠንከር ያሉ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ ያስችላል ተብሎ የተዘጋጀው ረቀቅ የማዕቀብ ሕግ፣ በአሜሪካ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ከፀደቀ፣ በቀጣይ ለሕግ አውጭው ምክር ቤት ቀርቦ መጨረሻም በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ተፈርሞ ተፈጻሚ ሊሆን እንደሚችል ታውቋል፡፡
በኒውጀርሲ ሴናተር ቶም ማሊኖውስኪ መሪነት ተረቆ የቀረበው ‹‹ኢትዮጵያ ስታብላይዜሽን ፒስ ኤንድ ዴሞክራሲ›› የተሰኘው ረቂቅ ሕጉ፣ በኢትዮጵያ በተለይ በትግራይ ክልል ጦርነት በተፈጸሙ ሰብዓዊ ወንጀሎች ላይ የተሳተፉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግና በኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን ያለመ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በ25 ገጾችና በ12 ክፍሎች የቀረቡ ጠንካራ አንቀጾችን ይዟል፡፡
ኤችአር 6600 የተሰኘው ረቂቅ ሕግ ወደ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ሲላክ፣ ኤስ 3199 ተብሎ የተመዘገበ ሲሆን፣ ረቂቁ ይፋ ከመደረጉ ጀምሮ ሐሳቡን የሚቃወሙ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራ አባላት በሰላማዊ ሠልፍ እየተቃወሙት ነው፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን መጋቢት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች፣ በአሜሪካ ምክር ቤቶች በኢትዮጵያ ላይ ለማሳለፍ የታቀደው ረቂቅ ሕግ እንዳይፀድቅ ዘመቻ እንዲያደርጉ በበይነ መረብ ባደረጉት ውይይት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይ ኢትዮጵያ የራሷን ሉዓላዊ መብት እንዳታስጠብቅ፣ በፀጥታው ዘርፍ እንዳታደራጅ፣ እንዲሁም በንግድና በኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዳትጠናከር የሚያደርግ፣ በጦርነቱና የተዳከሙ አካባቢዎችን መልሰው እንዲያገግሙ የሚያግዝ ዕርዳታና ድጋፍ እንዳታገኝ የሚያደርግ እንደሆነ፣ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ፍጹም አረጋ ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በጦርነቱ ቤተሰቡን፣ ቤት ንብረቱን ያጣው ሕዝብ ፈጥኖ እንዳይቋቋም የሚያደርጉና የወደሙ የትምህርት፣ የጤናና ሌሎች የመሠረተ ልማቶች ፈጥነው እንዳይሠሩ የውጭ ብድርና ዕርዳታ የሚያስከለክሉ መሆናቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩም ሆኑ ፍጹም (አምባሳደር) ይህን ይበሉ እንጂ፣ ረቂቅ ሕጉ በአንዳንድ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባላት የተገፋና በአሜሪካ መንግሥት በኩል የተወሰነ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) ተናግረዋል፡፡
ቃል አቀባዩ እንደሚሉት ረቂቁ የአሜሪካ መንግሥት አቋም አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ አገራዊ ምክክር ሊካሄድ እየተሠራ ባለበትና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተነስቶ የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸውን በማስታወስ፣ በሕዝብ በተመረጠ መንግሥት ላይ ይህንን ዓይነት ዕርምጃ መውሰድ አስፈላጊ አለመሆኑን፣ ለአሜሪካ መንግሥት የማስረዳትና ለኮንግረንስ አባላት መልዕክት የማድረስ ሥራ ይከናወናል ብለዋል፡፡
ከመጋቢት 12 እስከ 13 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ ላሉት አዲሱ የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ዴቪድ ሳተርፊልድ፣ በጉዳዩ ላይ ግልጽ ማብራሪያ እንደሚሰጣቸው ቃል አቀባዩ አስረድተዋል፡፡