የግል አየር መንገዶች መጋቢት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. በሸራተን ሆቴል ባዘጋጁት የምስጋና ሥነ ሥርዓት፣ ኮሎኔል ወሰንየለህ በኃላፊነት ላይ በነበሩበት ወቅት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሽልማት አበርክተውላቸዋል።
የግል አየር መንገዶችን በመወከል ንግግር ያደረጉት የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎት፣ የአቪዬሽን አካዳሚ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ካፒቴን ሰለሞን ግዛው፣ ኮለኔል ወሰንየለህ የአቪዬሽን ዘርፉ ሕጉን አክብሮ እንዲንቀሳቀስና የሚገጥሙት ፈተናዎች እንዳያቆሙት ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጾ ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
‹‹እንደ ኃላፊ ሳይሆን እንደ ራሳቸው ጉዳይ በመመልከት ሲያገለግሉ ቆይተዋል፤›› ብለዋል። ባለፉት 12 ዓመታት ባበረከቱት አስተዋጽኦም የአቪዬሽን ዘርፉ የተሻለ ዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲያገኝ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፣ ይህም በተለይ የግል አየር መንገዶችን ተፈላጊነት አሳድጎታል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በኃላፊነት ላይ በነበሩበት ወቅት ላበረከቱት አስተዋጽኦም ምሥጋና ይሆን ዘንድ፣ ሁለት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ መኪና በስጦታ ማበርከታቸውን ገልጸዋል።
በምሥጋና ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የትራንስፖርት ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው፣ ‹‹በኃላፊነት የቆየኸው ረዥም ጊዜ ነው፡፡ በዚህም ሁሉንም አግባብቶ ማገልገል ከባድ ኃላፊነት ቢሆንም፣ በጥንካሬ ስለተወጣኸው ምሥጋና ይገባሃል፤›› ሲሉ ኮሎኔል ወሰንየለህን አመሥግነዋል፡፡ ‹‹እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትም በቀጣይም በማማከርና ሐሳቦችን በመለዋወጥ አብረን እንደምንዘልቅ ሙሉ እምነት አለኝ፤›› ብለዋል፡፡
ከግል አየር መንገዶች ጋር በተያያዘ ብዙ ችግሮች ቢኖሩም ያሉትን ዕድሎች አሟጦ መጠቀም እንደሚገባ የገለጹት ሚኒስትሯ፣ በተለይ ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በቅንጅት የሚሠራበትን መንገድ ለመጠቀም ዝግጁ መሆን እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡
ሽልማቱ የተበረከተላቸው ኮሎኔል ወሰንየለህ ለተደረገላቸው የምሥጋናና የሽልማት ሥነ ሥርዓት ምሥጋናቸውን አቅርበው፣ ባለፉት 12 ዓመታት በኃላፊነት በቆዩበት ጊዜ በርካታ ለውጦች ሲገኙ ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጀምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ባለፉት ዓመታት በአቪዬሽን ዘርፉ በተለይ በአፍሪካ ደረጃ ለሚሰጠው የተቆጣጣሪነት መለኪያ ከነበረበት 67 ነጥብ ወደ 89 ማደጉን ገልጸው፣ ይህም ለኢትዮጵያ አየር መንገድም ሆነ ለግል አየር መንገዶች ከፍተኛ ጥቅም ያስገኘ ነው ብለዋል። በተጨማሪም የአየር ክልል ቁጥጥርን በተመለከተ ሙሉ ለሙሉ በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን አማካይነት መከናወን መቻሉንም አክለዋል።
የአቪዬሽን ዘርፍ ከፍተኛ ዕድገት ያለበትና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች በየጊዜው የሚለዋወጡ ከመሆናቸው በተጨማሪ፣ ባለፉት ጊዜያትም ይሁን በአሁኑ ወቅት የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት የዘርፉ ትልቁ ፈተና መሆኑን ጠቅሰው፣ አሁን ያሉትን ሙያተኞች ለማቆየትም ሆነ አዳዲሶቹ ወደ ዘርፉ እንዲሳቡ ለማድረግ ትኩረት መሰጠት አለበት ብለዋል።
ኮሎኔል ወሰንየለህ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣንን ላለፉት 12 ዓመታት በዋና ዳይሬክተርነት ሲመሩ መቆየታቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በቅርቡ እሳቸውን በመተካት አቶ ጌታቸው መንግሥቴ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መሾማቸው አይዘነጋም፡፡