Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናሕወሓት በዋግህምራ ከያዛቸው ወረዳዎች ከ61 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ

ሕወሓት በዋግህምራ ከያዛቸው ወረዳዎች ከ61 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ

ቀን:

በአማራ ክልል ዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሁለት ወረዳዎች ሙሉ ለሙሉና ሁለት ወረዳዎች በከፊል አሁንም በሕወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ሥር በመሆናቸው፣ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ61 ሺሕ በላይ መድረሱ ተገለጸ፡፡ በሕወሓት ከተያዙት አከባቢዎች የሚፈናቀሉ ሰዎች ብዛትና የሚደርሰው የዕርዳታ መጠን የሚመጣጠን ካለመሆኑም በላይ፣ ከተፈናቃዮቹ ውስጥ መንግሥት ባዘጋጃቸው መጠለያ ውስጥ ያሉት 3.2 በመቶ ያህሉ ብቻ መሆናቸውን የብሔረሰብ አስተዳደሩ አስታውቋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ከትግራይ ክልል መውጣቱን ተከትሎ የሕወሓት ኃይሎች ወደ አማራና አፋር ክልሎች ሲስፋፉ፣ በዋግህምራ ብሔረሰብ ውስጥ ከሚገኙ ሰባት ወረዳዎችና ሁለት የከተማ መስተዳደሮች ውስጥ ከሳሃራ ወረዳ በስተቀር ሁሉም ወረዳና የከተማ አስተዳደሮች በሕወሓት ቁጥጥር ሥር ነበሩ፡፡

ከታኅሳስ 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ መንግሥት አብዛኛዎቹን ወረዳዎች መልሶ በቁጥጥሩ ሥር እንዳስገባ ለሪፖርተር የተናገሩት የአስተዳደሩ የኮሙዩኒኬሽን መምርያ ኃላፊ አቶ ከፍያለው ደባሽ፣ ነገር ግን ሁሉም ወረዳዎች በመንግሥት ሥር ሳይሆኑ ሠራዊቱ ባለበት እንዲቆም መታዘዙን አስታውሰዋል፡፡

በዚህም የተነሳ አበርገሌና ፃግብጂ የተባሉት ወረዳዎች ሙሉ ለሙሉ፣ እንዲሁም በዝቋላ ወረዳ ስድስት ቀበሌዎችና በሰቆጣ ወረዳ ሁለት ቀበሌዎች በሕወሓት ቁጥጥር ሥር መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ከዚህ ቀደም በትግራይ ክልል ሥር የነበረውና ከጦርነቱ ወዲህ በዋግህምራ ብሔረሰብ ውስጥ ተጠቃሎ ወፍላና ዛታ ተብሎ የተከፈለው ወፍላ ወረዳም፣ በሕወሓት ሥር እንደሆነና የዋግህምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ለሠራተኞች ደመወዝ ክፍያ እንደሚፈጽም አቶ ከፍያለው ተናግረዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ከእነዚህ ዞኖች እየተፈናቀሉ በመንግሥት ሥር የሚገኙ አከባቢዎች የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመሆኑ፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ የተፈናቃዮች ቁጥር ከ61‚800 በላይ ሆኗል፡፡ ከእነዚህ ተፈናቃዮች ውስጥ ከ2‚500 በላይ የሚሆኑት አጥቢ እናቶች፣ 882 ያህሉ ነፍሰ ጡር እናቶች፣ እንዲሁም ከ1‚200 የሚልቁት ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ናቸው ብለዋል፡፡ 

ኃላፊው እንደተናገሩት፣ ከተፈናቃዎቹ ውስጥ 20 ሺሕ ገደማ ሰዎች መጠለያ አግኝተዋል፡፡ ነገር ግን ከ18 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ተፈናቃዮች ደግሞ ባገኟቸው ክፍት መጋዘኖችና ሌሎች መደበኛ ያልሆኑ መጠለያዎች እንደተሰባሰቡ፣ መንግሥት ባዘጋጃቸው መደበኛ መጠለያዎች ውስጥ የሚገኙት ሰዎች ከሁለት ሺሕ እንደማይበልጡ አቶ ከፍያለው ተናግረዋል፡፡ ይህም የሆነው መንግሥት ያዘጋጃቸው ድንኳኖች ከዚህ በላይ የማስተናገድ አቅም የሌላቸው በመሆኑ እንደሆነ አስረድተው፣ የመንግሥት ድጋፍ አነስተኛ መሆኑን አክለዋል፡፡

ቀሪዎቹ ተፈናቃዎች በዘመድ ቤት ተጠግተው፣ በረንዳ ላይና የሚያስጠጋቸው ሰው እየፈለጉ መጠለላቸውን ገልጸው በአጠቃላይ ተፈናቃዮቹ ችግር ውስጥ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ “በምሽት እየሸሹ ይመጣሉ” ከተባሉት እነዚህ ተፈናቃዎች ውስጥ፣ ነፍሰ ጡር ሴቶች ጭምር በቀዝቃዛ የሲሚንቶ ወለሎች ላይ ለመተኛት መገደዳቸውንም አቶ ከፍያለው አክለዋል፡፡ ኃላፊው እንደሚናገሩት፣ ቅዝቃዜ ላይ በመተኛታቸው ምክንያት እግራቸው በሽተኛ የሆኑ ተፈናቃዎች አሉ፡፡ በረሃብ የተነሳ ከፍተኛ ጉዳት አጋጥሟቸው በሰቆጣ ከተማ ለሕክምና የተኙ ስምንት ሕፃናት እንዳሉ አስታውቀዋል፡፡ 

“ሌላው ሰው እንደፈለገ የሚበላና የሚታከም አይደለም፤” ያሉት አቶ ከፍያለው፣ ሌሎቹም የአስተዳደሩ አከባቢዎች በሕወሓት ኃይሎች ዝርፊያ የተፈጸመባቸው በመሆናቸው ያልተፈናቀሉ ሰዎችም ችግር ውስጥ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ይህም ተፈናቅለው ለመጡት ነዋሪዎች በተፈለገው ልክ መድረስ እንዳይቻል ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

ተፈናቃዮቹ ዕርዳታ እየተደረገላቸው ያለው መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች፣ ከግለሰቦች፣ እንዲሁም ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች በሚገኙ ዕርዳታዎች መሆኑ ታውቋል፡፡ የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ከዚህ ቀደም 1‚500 ኩንታል እህል መላኩን የገለጹት ኃላፊው፣ ከተፈናቃዮች ቁጥር አንፃር ይህ ዕርዳታ እዚህ ግባ የማይባል መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለተፈናቃዮቹ ዕርዳታ የሚውሉ ግብዓቶች ለማግኘት ጥያቄ እየቀረበ መሆኑን አክለዋል፡፡

“የተፈናቃይ ቁጥር እየበዛ በመሆኑ በዕርዳታ የሚዘለቅ አይሆንም፤” የሚል ሐሳብ ያላቸው አቶ ከፍያለው፣ መፍትሔው አካባቢዎቹን በመንግሥት ቁጥጥር ሥር አድርጎ ነዋሪዎቹን ወደ አካባቢያቸው መመለስ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ኃላፊው ይህ ሐሳብ የነዋሪዎችም እንደሆነ በመግለጽ፣ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአካባቢው የሚገኘው የመከላከያ ሠራዊትና ነዋሪዎች ውይይት ባደረጉበት መድረክ ላይ መነሳቱን አስረድተዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት አባላቱም፣ ይህ የመንግሥት ውሳኔ ቢሆንም ከጎናችሁ ነን የሚል ምላሽ መስጠታቸውን አቶ ከፍያለው ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል መንግሥት በክልሉ በአጠቃላይ 11.6 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ ዕርዳታ እንደሚፈልግ፣ 263 ሺሕ ተፈናቃዮች እንደሚገኙም በባለፈው ሳምንት ማሳወቁ አይዘነጋም፡፡ ከእነዚህ ተፈናቃዎች ውስጥ ከዋግህምራ አዋሳኝ አካባቢዎች፣ ከአላማጣና ከኮረም ተፈናቅለው ወደ ቆቦ የመጡ፣ እንዲሁም በሰሜን በኩል ተፈናቅለው ወደ ደባርቅ የመጡ እንዳሉ አስታውቋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...