Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት የሚቻለው ሴረኝነት ሲመክን ነው!

  በሁሉም ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ባይቻልም፣ መሠረታዊ በሚባሉት ላይ ግን መግባባት አያቅትም፡፡ ሊያግባቡ ከሚችሉ በጣም መሠረታዊ ከሚባሉ ጉዳዮች መሀል በዋነኝነት የሚጠቀሱት ሰብዓዊነት፣ ፍትሐዊነት፣ እኩልነትና ነፃነት ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ምድር የማንነት፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የፆታ፣ የፖለቲካ አቋምና የመሳሰሉት ፀጋዎች ተከብረው በሰላም መኖር ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚያስፈልገው የሁሉም ወገኖች ፈቃደኝነት ነው፡፡ አንዱ በሌላው ላይ የበላይ ሳይሆን በእኩልነት የሚኖርበት ሥርዓት ለመመሥረት፣ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ቅርርብ የሚረዱ የተለያዩ ሐሳቦች መሰማት ይኖርባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያውያን አንዳቸው ለሌላቸው አስፈላጊ መሆናቸውን በመገንዘብ፣ ከሚለያዩዋቸው ጥቃቅን ቅራኔዎች ይልቅ አንድ የሚያደርጓቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይኖርባቸዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከታሪክ ጀምሮ በበርካታ ጉዳዮቻቸው ላይ ለመነጋገርና ተቀራራቢ አቋም ለመያዝ ዝግጅት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ይሆን ዘንድ ግን ከመጠን ካለፈ ራስ ወዳድነት፣ ስግብግብነት፣ ጭካኔ፣ ፍርደ ገምድልነትና ሞራል አልባነት መላቀቅ የግድ ይላል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሴረኝነት መወገድ አለበት፡፡

  በዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን እንኳን እርስ በርስ ሊጋጩና ሊጠፋፉ ቀርቶ ከመቼውም ጊዜ በላይ መቀራረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ዓለም በሩሲያና በዩክሬን ጦርነት ምክንያት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ገብቶ የምግብ ምርቶችና የነዳጅ ዋጋ ከመጠን በላይ ሲጨምር፣ ኢትዮጵያውያን አንዳቸው ያላቸውን ወደ ሌላው እያሻገሩና የጎደላቸውን ደግሞ እየተቀበሉ ይህን ክፉ ጊዜ ማለፍ ይኖርባቸዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ ከጎረቤት አገሮች ጀምሮ ከመላው የአፍሪካ አገሮች ጋር የንግድ ግንኙነትን በማቀላጠፍ፣ ለዘለቄታዊ ትስስር አገርን ማዘጋጀት ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ ራዕይ አልባ ሆኖ መሬትና መሰል ቁሳዊ ነገሮችን በማሳደድ እርስ በርስ ከመጠላለፍ፣ ኢትዮጵያ የታደለቻቸውን ተፈጥሯዊ በረከቶች አውጥቶ ለመጠቀም መረዳዳት ያስፈልጋል፡፡ በአራቱም ማዕዘናት የሚገኙ አጓጊ ሃይማኖታዊ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ የቱሪስት መስህቦችን ለአገር ውስጥና ለውስጥ ጎብኚዎች ማመቻቸት ተገቢ ነው፡፡ ወጣቱን በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በቴክኖሎጂ፣ በጤና፣ በትምህርት፣ በትራንስፖርትና በመሳሰሉ መስኮች ውጤታማ እንዲሆን ማገዝና ማበረታት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት መሆን ይኖርበታል፡፡ ሠርቶ ማደግና መለወጥ በሚቻልባት ኢትዮጵያ ውስጥ በሴራ ፖለቲካ ተጠልፎ መውደቅ ኪሳራው ከባድ ነው፡፡

  በአሁኑ ጊዜ የአዕምሮን ዕምቅ ሀብት በመጠቀም ከዘመናት ችግሮች ለመገላገል የሚያስችሉ ብልኃቶች በዕውቀት መልክ እየቀረቡ ነው፡፡ ከመደበኛው ትምህርት በተጓዳኝ በተለያዩ ሴሚናሮች፣ ኮንፈረንሶች፣ በትርፍ ጊዜ በሚሰጡ የዕውቀት ማጋሪያ መድረኮች ሰዎች በተለያዩ ዘዴዎች መለወጥና ማደግ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ የሰው ልጅ በተፈጥሮ የተሰጠውን የማገናዘብ ችሎታ በመጠቀም ራሱን በመለወጥ ለማኅበረሰቡ መትረፍ የሚችልበት ዕውቀት እያገኘ ነው፡፡ ለበርካታ ዓመታት የተዘጉ አዕምሮዎች እየተከፈቱ በርካታ የሥራ መስኮችን መፍጠር እየቻሉ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ታይተውም ሆነ ተሰምተው በማይታወቁ ምልከታዎች ሰዎች ዓለምን መለወጥ የሚያስችል ዕምቅ አቅም እንዳላቸው እየታወቀ ነው፡፡ በዚህ መሠረት በመደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆነ የዕውቀት አማራጭ ራስንና አገርን ማሳደግ እየተቻለ፣ ውስን የሆኑ ሀብቶች ላይ በመራኮት ለልማትና ለዕድገት መዋል ያለበት የሰው ኃይልና ጊዜ እየባከነ ነው፡፡ ከዚህም አልፎ ተርፎ ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት እየተቀጠፈ ነው፡፡ አሁን የሚስተዋሉትን ዙሪያ መለስ ችግሮች በመፍታት ትልቅ ደረጃ መድረስ ሲገባ፣ በሴራ ፖለቲካ ተተብትቦ አገርና ሕዝብ መርሳት ያስተዛዝባል፡፡

  የዘመኑ ትውልድ ዕውቀት ለመቅሰም ከፈለገ በርካታ አማራጮች ስላሉት በጣም ዕድለኛ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ከበፊት በተሻለ ብዙ የአንደኛ፣ የሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተከፍተውለታል፡፡ ጎን ለጎንም የተለያዩ ዕውቀቶችን የሚቀስምባቸው አማራጭ የዕውቀት ማዕዶች አሉት፡፡ እንዲህ ዓይነት መታደል ሲኖር ደግሞ በከፍተኛ ደረጃ ለትምህርት ጥራት መጨነቅ ይኖርበታል፡፡ የትምህርት ጥራት በሌለበት ስለዕውቀት መነጋገር አይቻልም፡፡ በተጨማሪም ተማሪዎች ለፈተና ሲዘጋጁ ኩረጃ የሚባለው አሳፋሪ ነገር ወደ አዕምሮዋቸው እንዳይመጣ መገታት አለበት፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ግን ኩረጃን መከላከል የሚገባቸው ወላጆች፣ የትምህርት ተቋማት፣ የመንግሥት አካላትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ አይደለም፡፡ ፈተና ሲደርስ የስርቆትና የኩረጃ ወሬ በሰፊው መድራቱ ይህንን ድክመት ነው የሚያስገነዝበው፡፡ ኩረጃ ተቋማዊ መሆኑ በሚመለከተው የትምህርት አካል በፓርላማ ጭምር ሲነገር፣ ይዞት ሊመጣ የሚችለው መዘዝ አለመጤኑ አሁን ያለንበትን የውድቀት ጉዞ አመልካች ነው፡፡ የእነ እከሌ ክልል ከሌሎች ክልሎች የበለጠ ተማሪዎችን ያሳለፈው ፈተናው ተሰርቆ ነው ተብሎ ጉዳዩ ፖለቲካዊ ገጽታ ሲላበስ፣ ኢትዮጵያ እየገባችበት ያለውን አደገኛ ሴረኝነት ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡

  ኢትዮጵያ ውስጥ በየቀኑ በሚፈበረኩ አጀንዳዎች ምክንያት አንድ ከመሆን ይልቅ፣ ወደ መለያየት ማምራት ልምምድ እየተደረገበት ነው፡፡ ለዘመናት ክፉና ደጉን አብሮ ያሳለፈን ሕዝብ ባህሪ የማይወክሉ ክፋት፣ ተንኮል፣ መሰሪነት፣ ስግብግብነት፣ አልጠግብ ባይነት፣ ምቀኝነትና ጨለምተኝነት እየበረከቱ ነው፡፡ በሚያጋጥሙ የልዩነት ጉዳዮች ላይ በግልጽ ለመነጋገር ድፍረት ጠፍቶ መተማማት፣ ገመናን መዘካዘክና የጥላቻ መንገዶችን መስበክ ተለምዷል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አስተዋይነት የጎደለው ድርጊት በተቃራኒ ኃይሎች መካከል ብቻ ሳይሆን፣ በአንድ ፓርቲ ወይም ስብስብ ውስጥ ያሉ የትግል ጓዶችን ጭምር እየበከለ ነው፡፡ በደህና ጊዜ የተለዋወጡትን ሚስጥር ለሦስተኛ ወገን አሳልፎ በመስጠት መከዳዳት የጊዜው ፋሽን ሆኗል፡፡ ጨዋነት አስከባሪ እንደሆነ ለዘመናት በሚታወቅባት አገር ውስጥ ሌባና ምግባረ ቢስ መሆን ያን ያህል ስለማያሸማቅቅ፣ ዘርፎ ለመክበር የሚደረገው ሩጫ የኦሊምፒክ ሻምፒዮኖችን የሚያስንቅ እየሆነ ነው፡፡ አገርን የምታህል ታላቅ ምድር በሚያኮሩ ተግባራት ለማስጠራት የማይችሉ ብኩኖች፣ በሴራ ፖለቲካቸው ቁልቁል ሲያንደረድሯት መከራው የሚተርፈው ለምስኪኑ ሕዝብና ለአገር ነው፡፡

  ኢትዮጵያን የሚያስከብራት፣ የሚያሳድጋትና በዓለም አደባባይ አንገቷን ቀና አድርጋ በኩራት እንድትራመድ የሚያደርጋት ፈተና ሰርቆ በማለፍ አይደለም፡፡ የአገርና የሕዝብ ሀብት ዘርፎ በመክበር አይደለም፡፡ በሐሜትና በአሉባልታ በመዘላለፍ አይደለም፡፡ ዘመኑን በማይመጥን አስተሳሰብ በመዳከር አይደለም፡፡ ለፍተውና ጥረው ባላገኙት ማንነትና እምነት በመኮፈስ አይደለም፡፡ በኢሰብዓዊነት መንፈስ ተሞልቶ ጨካኝ በመሆን አይደለም፡፡ በሰብዓዊ ፍጡራን ላይ ወንጀል በመፈጸም አይደለም፡፡ የአገርን ሚስጥር ለባዕዳን አሳልፎ በመሸጥ አይደለም፡፡ በአጠቃላይ ሴረኝነት ውስጥ በመሰማራት ሕዝብን በማስለቀስ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ በኩራት የዓለም ሰገነት ላይ ቆማ ማንፀባረቅ የምትችለው ሕጋዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት የሚያስችል ቁመና ላይ መገኘት ስትችል ነው፡፡ ለዚህ ዓይነቱ ታላቅ ኃላፊነት ራሳቸውን የሚያዘጋጁ ኢትዮጵያውያን ለዘመኑ የሚመጥን ዕውቀት የታጠቁ፣ የሞራልና የሥነ ምግባር ከፍታቸውን ማሳየት የሚችሉ፣ ለማኅበራዊ ፍትሕ መስፈን መስዋዕትነት የሚከፍሉ፣ በንፁኃን ደም እጃቸውን የማይታጠቡ፣ ሌብነትና ዝርፊያን ከመፀየፍ አልፈው የሚያስወግዱና ለሕዝብ ልዩ ፍቅርና ክብር ያላቸው ናቸው፡፡ እኛ እዚህኛው መደብ ውስጥ ነን የምትሉ ለአገራችሁና ለሕዝባችሁ ልዩ ፍቅርና ክብር አሳዩ፡፡ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት የሚቻለው ሴረኝነት ሲመክን ብቻ ነው!

    

   

   

   

   

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  በዕድሳት ምክንያት የተዘጋው የአዲስ አበባ ስታዲየም በቅርቡ ለአገልግሎት ክፍት ይሆናል

  የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታ በሚፈለገው ልክ እየተከናወነ እንዳልሆነ ተገልጿል ከስፖርታዊ...

  የንብረት ታክስ ጉዳይ በሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ጉባዔ ቀዳሚ አጀንዳ ይሆናል ተባለ

  መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም. በሚጀምረው የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን...

  መንግሥት ለሶማሊያ የፀጥታ ኃይሎችና የመንግሥት ሠራተኞች ሥልጠና ለመስጠት ቃል ገባ

  የኢትዮጵያ መንግሥት ለጎረቤት አገር ሶማሊያ የመንግሥት ሠራተኞችና የፀጥታ አካላት...

  የኢትዮጵያ ባንኮችን የማዋሃድ አስፈላጊነት ፍንትው ያደረገው ዓመታዊው የአፍሪካ ባንኮች የደረጃ ምዘና ሪፖርት

  የአፍሪካ ባንኮችን በየዓመቱ በመመዘንና ደረጃ በመስጠት የሚታወቀው አፍሪካ ቢዝነስ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች