- በጦርነት ለተጎዱ አካባቢዎች የፋይናንስ ድጋፍ ጥያቄ ላይ ለመወሰን ቀጠሮ ተይዟል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ከዓለም ባንክ የአፍሪካ ቡድን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከሆኑት ታኡፊላ ናያማዛቦ ጋር ተወያዩ።
በዓለም ባንክ በአፍሪካ ለሚገኙ 21 አገሮች ቡድን ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት ቦትስዋናዊው ታኡፊላ ናያማዛቦ ካለፈው ሰኞ መጋቢት 12 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ የሥራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፣ በቆይታቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን ጨምሮ ከተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።
የባንኩ የአፍሪካ ቡድን ኃላፊ ጋር ተገናኝተው ከመከሩ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች መካከልም የፋይናንስ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) እና የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) ይገኙበታል።
ባንኩ የኢትዮጵያ መንግሥት ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘውን “አገር በቀል የኢኮኖሚ ልማት ፕሮግራም” ለመደገፍ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የገንዘብ ስምምነት የፈጸመ ቢሆንም፣ የፋይናንስ ድጋፉ በተገቢው ጊዜ አለመለቀቁ በመንግሥት ላይ ያስከተለውን ጫና በተመለከተ ከባንኩ የአፍሪካ ቡድን ኃላፊ ጋር ውይይት መደረጉን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል።
በውይይቱም ለአገር በቀል የኢኮኖሚ ልማት ዕቅዱ ማስፈጸሚያ የተፈቀደው የፋይናንስ ድጋፍ በፍጥነትና በተሟላ መልኩ መለቀቅ በሚችልበት ሁኔታ ላይ መግባባት እንደተደረሰ ምንጮቹ ገለጸዋል።
ከዚህ ጉዳይ ባሻገር በኢትዮጵያ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ነዋሪዎችን መልሶ ለማቋቋም፣ መንግሥት ባቀረበው የፋይናንስ ድጋፍ ጥያቄ እንዲሁም፣ በድርቅና በኮቪድ-19 ወረርሽኝ የኢኮኖሚ ተዕዕኖዎች ዙሪያ ባንኩ የሚያደርገውን ድጋፍ በተመለከተ ውይይት መደረጉን ምንጮቹ ገልጸዋል።
በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤት የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ የሆኑት ገሊላ ውድነህ፣ የባንኩ የአፍሪካ ቡድን ዋና ሥራ አስፈጻሚ በአዲስ አበባ ያደረጉትን ጉብኝት አስመልክቶ ለሪፖርተር በሰጡት ምላሽ፣ በአሁኑ ወቅት ዋና ሥራ አስፈጻሚው በሚመሩት የአፍሪካ ቡድን ውስጥ የሚገኙ አገሮችን በመጎብኘት ላይ መሆናቸውን በዋናነት ገልጸዋል።
ኢትዮጵያም የዚሁ ቡድን አንዷ አባል አገር በመሆኗ የተደረገ ጉብኝት ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ መንግሥትም ጉብኝቱ በዚህ ወቅት እንዲፈጸም ለዋና ሥራ አስፈጻሚው ግብዣ ማድረጉን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሠፈሩት መልዕክት፣ ከባንኩ የአፍሪካ ቡድን ዋና ሥራ አስፈጻሚና በኢትዮጵያ የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ጋር በኦሮሚያ ክልል የተጀመሩ የስንዴ ማሳዎችን እንደጎበኙና በዚህም መንግሥት ከውጭ እያስገባ ያለውን የስንዴ ምርት ለመተካት እያደረገ ያለውን ጥረት በአካል መመልከት መቻላቸውን ገልጸዋል።
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፣ ከባንኩ የአፍሪካ ቡድን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋር በነበራቸው ውይይት፣ መንግሥት ተግባራዊ እያደረገ የሚገኘውን የአሥር ዓመት የኢኮኖሚ ልማት ዕቅድ በተመለከተ ገለጻ ማድረጋቸውን ሚኒስቴሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።
ባንኩ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ልማት ከሚያደርገው ትብብርና ከሰብዓዊ ዕርዳታ ድጋፎቹ ዓይኑን ሊያነሳ እንደማይገባ ሚኒስትሯ በውይይቱ ወቅት በአጽንኦት መናገራቸውን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
የጤና ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር)፣ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሠፈሩት መልዕክት፣ ከባንኩ የአፍሪካ ቡድን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋር በአደጋ ጊዜ ምላሽ፣ በመልሶ ግንባታና ማገገሚያ ፕሮጀክቶች፣ በሥነ ምግብ፣ በእናቶችና ሕፃናት ጤናና ሌሎች ቅድሚያ የሚሰጣቸው ተግዳሮቶችን ለመፍታት የዓለም ባንክ ትብብርን ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደመከሩ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ትግራይን ጨምሮ በጦርነትና ግጭት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባትና ነዋሪዎችን ለማቋቋም ከ19 ቢሊዮን ብር በላይ የሚጠይቅ ፕሮጀክት ይፋ ማድረጉን ሪፖርተር በእሑድ ዕትሙ መዘገቡ የሚታወስ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ ከሚጠይቀው ወጪ ከ15 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወይም 300 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው ወጪ በዓለም ባንክ እንዲሸፍን መንግሥት የፋይናንስ ድጋፍ ጥያቄውን ለባንኩ አቅርቧል።
ለዚህ የመልሶ ግንባታና መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት የፋይናንስ ድጋፍ ጥያቄ ላይ ለመወሰን የዓለም ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ለመጪው ዓርብ መጋቢት 16 ቀን 2014 ዓዓም. ጊዜያዊ ቀጠሮ መያዙን የባንኩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በጉዳዩ ላይ የጠየቅናቸው የባንኩ የኢትዮጵያ ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ ገሊላ ውድነህ፣ የባንኩ ቦርድ በኢትዮጵያ መንግሥት የድጋፍ ጥያቄ ላይ ለመወያየት ለመጪው ዓርብ የያዘው ቀጠሮ ጊዜዊ መሆኑንና እንደ ሁኔታው ሊለወጥ አሊያም ሊካሄድ እንደሚችል ገልጸዋል።
በቀረበው የመልሶ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ ባንኩ የወከላቸው ባለሙያዎች ባደረጉት የፕሮጀክቱ የአካባቢና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ግምገማ ላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸምን በተመለከተ በተለይም ፕሮጀክቱ በሚካሄድባቸው አካባቢዎች ካለው የፀጥታ ሥጋት ጋር የተገናኘ ሥጋት ማንሳታቸውን የባንኩ የግምገማ ሰነድ ያስረዳል።