Friday, June 9, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢሠማኮ የደመወዝ መነሻ ወለል ምጣኔን ለመንግሥት ሊያቀርብ ነው

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) አገር አቀፍ የደመወዝ መነሻ ወለል እንዲኖር ለማስቻል ያስጠናው ጥናት ላይ እየመከረ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ወቅቱን የጠበቀ የደመወዝ መነሻ ወለል ምጣኔን ለመንግሥት የሚያቀርብ መሆኑም አስታውቋል፡፡

መጋቢት 13 ቀን 2014 ዓ.ም. የኮንፌዴሬሽንና የፌዴሬሽን አመራሮች በጥናቱ ላይ ውይይት የጀመሩ ሲሆን፣ ከውይይቱ በኋላ አመራሩ የሚደርስበትን ሐሳብ ተንተርሶ ኢሠማኮ ዝቅተኛ የደመወዝ መነሻ ወለል ብሎ የሚስማማበትን ለመንግሥት ያቀርባል፡፡

ኢትዮጵያ እስካሁን ድረስ በአገር አቀፍ ደረጃ ገዥ የሆነ የደመወዝ መነሻ ወለል የሌላት መሆኑ፣ በተለይ ሠራተኞች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ እንደሆነ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ አሁን ግን ጉዳቱ እያየለ በመምጣቱ ይህ ዝቅተኛ የደመወዝ መነሻ ወለል እንዲኖር ኢሠማኮ ጉዳዩን ትኩረት ሰጥቶ እየሠራበት ይገኛል ተብሏል፡፡  

የደመወዝ መነሻ ወለል አለመኖር በርካታ ጉዳቶች እንዳሉት የሚያመለክተው ኢሠማኮ፣ በተለይ በአሁኑ ወቅት የዋጋ ንረት ሲያይል የኑሮ ውድነቱን ለማቃለል የደመወዝ መነሻ ወለል ላይ በውይይት በማድረግ ለማስተካከል ያስችል ነበር ብሏል፡፡

ሠራተኞች በኑሮ ውድነት በሚቸገሩበት ወቅት የደመወዝ መነሻ ወለሉ በኮሚቴ ወይም በቦርድ ተከልሶ የኑሮ ውድነቱን የሚመጥን የደመወዝ ጭማሪ ለማድረግ የሚያስችል ሲሆን፣ በሌሎች አገሮች እንዲህ ያለው አሠራር የተለመደ ሆኖ እየተሠራበት መሆኑን ይጠቅሳል፡፡ በተለይ የዋጋ ንረት በሚኖርበት ሰዓት ሠራተኞች ንረቱን ለመቋቋም የሚያስችላቸውን ጭማሪ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ግን እንዲህ ያለው አሠራር ባለመኖሩ በተደጋጋሚ በሚከሰት የኑሮ ውድነት ሠራተኞች ሲጎዱ ቆይተዋል፡፡ አሁንም ይህ ችግር እየተስተዋለ በመሆኑ ኮንፌዴሬሽኑ በዚሁ ታሳቢነት ከዚሁ ቀደም ያስጠናውን ጥናት በመፈተሽ ኢትዮጵያ  የደመወዝ መነሻ ወለል እንዲኖራት የሚያስችል ሰነድ አዘጋጅቶ ለመንግሥት ያቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ይህ ከመሆኑ በፊት ግን በጥናት ላይ የተመሠረተውን  የደመወዝ መነሻ ወለልን በሚመለከት በቀጥታ ባለድርሻ አካላት ከሚባሉት አሠሪዎችና መንግሥት ጋር የሚመክርበት እንደሆነም ይኼው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ሠራተኛው በዋጋ ንረት በሚጎዳበት ወቅት ንረቱን ለመቋቋም የሚያስችል የደመወዝ ጭማሪ ያግኝ ብሎ ለመጠየቅ እንኳን ይህ  የደመወዝ መነሻ ወለል እንዲኖር በሕግ መቀመጥ ስላለበት፣ ይህንን ለማድረግ ኢሠማኮ የሚሠራ መሆኑም ታውቋል፡፡

እንዲህ ያለው አሠራር ለአሠሪውም የሚጠቅም እንደሆነ የሚያመለክተው መረጃ ሠራተኛውም ተረጋግቶ ሥራውን መሥራት እንዲችል፣ ምርትና ምርታማነትም እንዲጨምር  የደመወዝ መነሻ ወለል መቀመጥና መተግበር አለበት ብሏል፡፡

አሁን ኢሠማኮ እየመከረበት ያለው ሰነድ ገበያውን በመመልከት ዝቅተኛው ደመወዝ ወለል ይህ መሆን አለበት የሚል ሐሳብ ይዞ እንዲቀርብ የሚያደርግ ሲሆን፣ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ መሠረት መቋቋም የነበረበት የደመወዝ ቦርድ እንዲቋቋም ይጠይቃል፡፡

ይኼ የደመወዝ ቦርድ ደግሞ በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሚመራው ነው፡፡ ይኼ የደመወዝ ቦርድ ግን ገና በደንብ ያልተቋቋመ ሲሆን፣ ይህንን ለማቋቋም የሚያስችል ደንብ እየተጠበቀ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሆኖም ይህ ቦርድ እስኪቋቋም ድረስ ኢሠማኮ አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ የሚጠብቅ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በእነዚህ ጉዳይ ላይ ኢሠማኮ በሳይንሳዊ ጥናት ላይ ተመሥርቶ ‹‹በኢትዮጵያ  የደመወዝ መነሻ ወለል ይህ መሆን አለበት›› ብሎ የሚያቀርብ ሲሆን፣ በጥናቱ ላይም ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚመክርበት አስታውቋል፡፡  

    

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች