Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአገርን ከረሃብ የማያስጥል የዘውግ መራኮት የት ያደርሰን ይሆን?

አገርን ከረሃብ የማያስጥል የዘውግ መራኮት የት ያደርሰን ይሆን?

ቀን:

በገለታ ገብረ ወልድ

አገራችን ሰፊና ብዝኃነት የሞላባት ምድር ነች፡፡ ታሪካዊና የነፃነት ቀንዲልነቷ እንደ ምሰሶ የቆመ ምልክት ከመሆኑም በላይ፣ የሰብዓዊነትና የመረዳዳት ፀጋ ያላት አኩሪ አገር ናት፡፡ የእርስ በርስ ጦርነት፣ የጭቆናና የፀረ ዴሞክራሲ ሥርዓቶች መጥፎ የታሪኳ ጠባሳ መሆናቸው ባይካድም፣ ኢትዮጵያ የእርግማን ምድር እንዳልሆነች አፍ ሞልቶ መናገር ዋሾነት አይደለም፡፡

የሚያስቆጨው ሀቅ ግን አሁን በምንገኝበት ጊዜና በዚህ ትውልድ እንኳን፣ አገራችንን በተሻለ መጠበቅ አለመቻላችንና ለሁላችንም የምትበቃ አለማድረጋችን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬም ሀብት እያላት ሚሊዮኖች በድህነት የሚማቅቁባት፣ ቀላል ግምት የማይሰጣቸው ወጣቶች ሥራ የማያገኙባትና ዜጎች (በዋናነት በፅንፈኛ ብሔርተኞች ተንኳሽነት) ከእርስ በርስ ግጭት ያልወጡባት ነች፡፡ ድርቅና ረሃብም በተፈጥሮ ብቻ ሳይሆን በሰው ሠራሽ ፈተና እየታገዘ መወገድ አልቻለም፡፡ ይህንን ድቅድቅ ጨለማ መግፈፍ አለመቻል ነው የሚያበሳጨው፡፡

ለእነዚህ መከራዎችና የዕድገት ጉዞ እንቅፋቶች በቅድሚያ ማንሳትና መውቀስ ያለብን የፖለቲካ አቅጣጫውን መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ከሦስት አሠርት ዓመታት በፊት ምንም እንኳን በአሀዳዊነት የሚወቀሱና የብሔረሰቦችን መብት ባለማስከበር የሚተቹ ሥርዓቶች ለድህነቱ ትውልድ መሻገር የራሳቸው ድርሻ ቢኖራቸውም፣ ከሦስት አሠርት ዓመታት ወዲህ በአገራችን የተተከለው የዘውግ ፌዴራሊዝም ላይ የተመሠረተው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ጉዞም የቀውሱን አዙሪት አባብሶታል፡፡

በምንገኝበት ደረጃ የሥርዓት ለውጥ ባይባል እንኳን የአስተሳሳብ ከፍታና የለውጥ ኃይሎች ጉጉት ያጀበው አዲስ ጉዞ ቢጀመርም፣ እንደ ሕዝብ ከሥጋት የሚያወጣ ነገር አልታየም፡፡ እንዲያውም ከእነ ችግሩ በቀደሙት ዓመታት የነበረው የልማት ጉዞ ተዳክሞ፣ የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስና የደኅንነት ሁኔታ ፈተና ተጋርጦበት፣ ዘውግ ተኮሩ ፌዴራሊዝም አብሮ ለመኖር ፈታኛ የሆነበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው፡፡ እንደ ሕዝብ በመሀል የለ በዳር ችግርና መከራው ሳይለያይ እየለበለበው፣ መለያያትን የሙጥኝ ያለ ትውልድም እየበረከተ ነው፡፡

በዛሬው ትዝብቴ በጥቅሉ ከመነጋገር በደቡብ ምሥራቅና በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚገኙትን ሰፊ የአርብቶ አደር ማኅበረሰቦች በማሳያነት እነሳለሁ፡፡ ይህም ምናልባት ገዥው ፓርቲ ለቀጣይ ተጨማሪ አገራዊ ማሻሻያ የሚረዳ ጉባዔ ካጠናቀቀ በኋላ ወደላቀ ምዕራፍ ልሸጋገር ነው በማለቱ፣ አንዳች ማስተዋልን ለአንባቢያን እንደሚሰጥ በማመን የሆነ ነው፡፡

ዛሬ በሁለት የብሔረሰብ ክልሎች የሚተዳደሩት የቦረና ኦሮሞና የሶማሌ አርብቶ አደሮች ዋነኛ መተዳደሪያቸው የእንስሳት ዕርባታ ሲሆን፣ በአብዛኛው ለውኃ ፍለጋ ከቦታ ቦታ በመዘዋወር ለዘመናት የኖሩ ናቸው፡፡ የእነዚህ በሰፊ መልክዓ ምድር የሚኖሩ ሕዝቦች መግባቢያ ቋንቋ ቢለያይም ባህል፣ እምነት፣ አኗኗርና የሥራ ዘይቤ ተመሳሳይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

እነዚህ ወገኖች ዛሬ የገጠማቸው የድርቅ ፈተና ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈላቸው ነው፡፡ ዘንድሮው ብቻ ከሶማሌና ከቦረና ዞን እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ የቁም እንስሳት (በከብትና በሥጋ አገራዊ ዋጋ ላይም ሌላ ጫና የሚፈጥር ፈተና መሆኑን ልብ ይሏል) በድርቅ ምክንያት ያለቁበት፣ በመቶ ሺዎች የሚገመቱ ዜጎች ለቋሚ ተረጅነት የተጋለጡበት አሳዛኝ ክስተት ተፈጥሯል፡፡

እነዚህ የቆላማ አካባቢ ሕዝቦች የተፈጥሮ አደጋው ወቅት እየጠበቀ በየጊዜው ሲፈትናቸው የኖረ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ የመንግሥትንና የመላው የአገራችንን ሕዝብ አልፎ ተርፎም የውጭ የረድዔት ድርጅቶችን ዕገዛ የሚፈልጉበት ሁኔታም ተከስቷል፡፡ አሁን ባለው አካሄድ ግን ስንቱ የኅብረተሰብ ክፍል ነው የአካባቢውን ፈተና የተረዳው ብሎ መጠየቅ፣ ያለንበትን መፋዘዝ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡

የአሁኑ ችግር ዋነኛ ማባባሻ ግን መንግሥት በአንድ በኩል በየአካባቢው፣ በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ለማስተካከል የሚባዝንበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡ በሌላ በኩል ችግሩና ፈተናው ዘርና ማንነትን ሳይለይ የሚያደኸይ ቢሆንም፣ የአገራችን ሕዝብ ተሳስቦና ተረዳድቶ እንዳይኖር የሚያደርግ መከፋፋልና የእርስ በርስ ግጭት ውስጥ ደጋግሞ የሚገባበት የተንጋደደው የፖለቲካ መንገድ ባለመስተካካሉም ጉዳቱ የበረታ ፈተና መሆኑ ነው፡፡

ለአብነት ያህል በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የተወሰኑ አካባቢዎች ከወሰን አከላለል ጋር በተያያዘ የግጭት ባህሪ ያለው ችግር የተቀሰቀሰው ከዓመታት በፊት ነበር። በእርግጥ የኦሮሚያና የሶማሌ ክልሎች ከአንድ ሺሕ ኪሎ ሜትር በላይ የጋራ ድንበር ቢኖራቸውም፣ የግጭት ባህሪ ያለው አለመግባባት ተፈጥሮ የነበረው በጥቂት አካባቢዎች እንደነበር አይዘነጋም።

ችግሩ የነበረው በኦሮሚያ ቦረና ዞንና በአዋሳኝ የሶማሌ አካባቢ በሚገኙ 26 ቀበሌዎች ነበር። በዚያ ወቅት የተፈናቀለውና የኑሮ መሠረቱ የተናጋው ሕዝብ ቁጥር ግን፣ ከአሁኑ የድርቅ ተጎጂ ቁጥር የሚተናነስ አልነበረም፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን ግጭቶችና ያለ መግባባቶች ከድርቅ ባልተናነሰ ፀረ ድህንት ትግሉን የሚጎዱ የዘላቂ ልማት እንቅፋቶችም ናቸው፡፡

እንዲያው ፍርጃ ሆኖብን እንጂ የቦረና (የኦሮሞ) እና የሶማሌ ብሔሮች ከ500 ለማያንሱ ዓመታት በድንበር ተጋሪነት አብረው መኖራቸውን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት። በዚህ የድንበር ተጋሪነት ኑሯቸው ወሰን አስምረው፣ እንደ ባላንጣ ሩቅ ለሩቅ ከመተያየት ይልቅ በእጅጉ ተቀራርበውም ነው የኖሩት። ኦሮሞዎችና ሶማሌዎች ተጋብተዋል፣ ተዋልደዋል፣ ለጋራ ችግራቸው ሸንጎ ተቀምጠው መክረው መፍትሔ አበጅተዋል፡፡

እንዳሁኑ ያለ የተፈጥሮ አደጋም ሆነ ሰው ሠራሽ ችግርና የጋራ ጠላታቸውን ለመመከትም ጎን ለጎን ተሠልፈው መክተዋል፣ ተዋግተው ደማቸውን አፍስሰዋል። ይህ በሁለቱ ብሔሮች ብዙ ትውልዶች የተካሄደ መቀራረብ በድንበራቸው አካባቢ የሁለቱም ብሔራዊ ማንነቶች ክልስ የሆኑ ማኅበረሰቦች እንዲፈጠሩ አድርጓል። ይህ ክልስ ማንነት በዋዣቂ ማንነት (Flood Identity) የሚገለጽበት ሁኔታዎች አጋጥመዋል። ታዲያ ዛሬ እንዴት እነዚያን እሴቶች ዘነጋናቸው ነው መባል ያለበት፡፡

የጠቀስናቸው ሕዝቦች ዋዣቂ ማንነት የገነቡት ማኅበረሰቦች የሁለቱንም ብሔሮች ማንነት በእኩል የሚጋሩ መገለጫዎች ናቸው ያሏቸው። ለምሳሌ ኦሮሚኛ ቋንቋ የሚናገሩ ሆነው የመኖሪያ ቤት አሠራራቸው፣ የጋብቻ ሥርዓታቸው፣ ወዘተ የሶማሌ ማኅበረሰብ ባህል የሚሆንበት ሁኔታ እንኳን ትናንት ዛሬም አለ። ነገም ሊቀየር እንዳማይችል ዕሙን ነው፡፡

ለምሳሌ ገሪ፣ ገርባ፣ ጃርሶ፣ ወዘተ ጎሳዎች ውስጥ የዚህ ዓይነት ነገር ይታያል። ቋንቋቸው ኦሮሚኛ ቢሆንም፣ ከከብት ይልቅ የግመል ዕርባታ ላይ መመሥረታቸውና የቤት አሠራራቸው ከሶማሌ ጋር ያመሳስላቸዋል። አብዛኛው የቦረና ኦሮሞ ጎሳ አባላት ሃይማኖት ዋቄፈታ ሲሆን፣ እነዚህ ሦስት ጎሳዎች ከሶማሌዎች ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ የእስልምና ሃይማኖት ተከታዮች ናቸው። ታዲያ ይህን ሕዝብ በአስተዳደርና በፍትሕ መቅረብ ጠቃሚ ሆኖ በወሰን፣ በማንነትና በፖለቲካ ማለያየት ፋይዳው ምንድነው? ድርቅና ችግሩ እንኳን ያለያያቸውን ወገኖች ማፈላቀሉስ ምን ይበጃል?

ይህ እውነት በብዙ የአገራችን ሕዝቦች መሀል የነበረና ያለ ቢሆንም፣ በዚህ ጽሑፍ የምንቃኛቸው የሁለቱን የጋራ ማንነት ያላቸው ማኅበረሰቦች አብሮነት ደጋግሞ ማየት ግን ኢትዮጵያዊያን ምን ያህል ጥብቅ ትስስር እንዳለን ያሳያል። እነዚህ ወገኖች የዛሬውን አያድርገውና ሁሉም በድህነትና በጭሰኝነት ውስጥም ቢሆን በጠላትነትና በጥርጣሬ ከመተያየት ይልቅ፣ አንዱ ሌላውን ወገኑ አድርጎ እየተሳሰቡ አብረው ነበር የኖሩት። ይህ የጋራ እሴት በአግባቡ ከተያዘ ጠንካራ የጋራ ልማትና የፀረ ድህነት ትግል መሠረት የማይሆንበት ምን ነገር አለ?

ከላይ እንደተጠቀሰው በኦሮሚያ ቦረና ዞንና በአዋሳኙ የሶማሌ ክልል ድንበር አካባቢ የሚኖሩ ማኅበረሰቦች በአርብቶ አደርነት የሚተዳደሩ ናቸው ብለናል። የአርብቶ አደር ማኅበረሰቦች ዋነኛ መለያ ኑሯቸው በአንድ ቦታ የረጋ ሳይሆን፣ በተወሰነ አካባቢ ለከብቶች መኖ የሚሆን ሳርና ውኃ ፍለጋ ተንቀሳቃሽ መሆኑንም ጠቅሰናል።

እርግጥ ነው በየትኛውም አገር ቢሆን አርብቶ አደር ማኅበረሰቦች አንድ ቦታ ረግተው አይኖሩም። ወቅት ተከትለው ለከብቶቻቸው ሳርና ውኃ ፍለጋ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሳሉ። ይህ የአርብቶ አደር ማኅበረሰቦች የኑሮ ዘይቤ ደግሞ ለእርስ በርስ ግጭት ተጋላጭ እንደሚዳርጋቸው ይታወቃል። በግጦሽ ሳር መስክና በውኃ መገኛ ሥፍራ ላይ ሽሚያ የሚገቡበት ሁኔታ የተለመደ ነውና። ይህ ሽሚያ ወደ ግጭት የማምራት ዕድሉ ሰፊ ቢሆንም ግን የእኛ አገር አርብቶ አደሮች፣ በተለይም የሶማሌና የኦሮሞ ተጎራባቾች ችግራቸውን የሚፈቱባቸው በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች ያሏቸው ናቸው።

እንደ አሁኑ ያለ ድርቅ ሲመጣ በሚከሰተው የእንስሳት ምግብ እጥረት ወደ ግጭት ቢገቡ እንኳን፣ ችግሩን ፈትተው የክልል ወሰን ሳይገድባቸው ድርቁን ለመመከት የሚሰባሰቡም ናቸው። የግጭቶቹ መንስዔ ግን የአንዱ ኦሮሞ መሆን፣ የሌላው ሶማሌ መሆን ሆኖ አያውቅም ነበር፡፡ ግጭቶቹ የብሔር ግጭት ተብለው የተገለጹበት የታሪክ ምዕራፍም አልነበረም፡፡ እንዲህ ያለ የንትርክና የቀውስ አዙሪት ተጠምጥሞብን የቀረው ግን አሁን ኢትዮጵያ ከምትከተለው የብሔር ፌዴራሊዝም ሥርዓት በኋላ ነው ቢባል ስህተት አይደለም። በተይም ጥገኛ የፖለቲካ ሥርዓት እያቆጠቆጠ ከመጣ ወዲህ፡፡

ይህን ፖለቲካዊ አካሄድ ወደ ግጭት የሚወስደው ደግሞ በየአካባቢው በጥገኝነት እየፋፋ ያለው የፖለቲካ ልሂቅ መሆኑ ተደጋግሞ ታይቷል፡፡ በተጠቀሰው አካባቢ ብቻ ሳይሆን፣ በመላው የአገራችን ጫፍም ሆነ መሀል ለሚቀሰቀሰው ሰው ሠራሽ ቀውስ መንስዔው የተማረው ኃይልና በተዛባ ትርክት ላይ የተጠመደው ወገን መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ይህ ባይሆንማ አርብቶ አደሩ እንኳን ከድህነት ሳይፋታ በማንነት ሊጣላ፣ በእኔ እበልጥ እኔ የጀብደኝነት መገለጫም የሚወቀስበት ታሪክ የለም፣ አልነበረም።

የተፈጥሮ ሀብት መራቆቱም ሆነ ግጭቶቹ እንደ ዘመነ መሣፍንት፣ በተስፋፊነት ግንኙነታቸውን ወደ አስገባሪና ገባሪ የመቀየር ዓላማም የላቸውም። ከዚህ ይልቅ ሰፊ ሀብትና የጋራ አገር እያለ በፅንፈኛው ፖለቲከኛ ሆደ ሰፊ አለመሆንና ስግብግብነት ነው ግጭቶች ሲባባሱ የቆዩት፣ ድህነትና ድርቅንም ከመሠረቱ መግታት ያልተቻለው፡፡

የአካባቢ ሰላምና ደኅንነት በጋራ እንዳይጠበቅ፣ በሙሉ አቅምና በተቀናጀ መንገድ ልማቱ እንዳይፋጠንም አዋኪ መሰናክሎች የሚደቀኑት በእነዚሁ መዘዝ ነው፡፡ እንዲህ ባይሆን ኖሮ ሦስቱ ጎሳዎች ቦረና፣ ገሪና ገርባ ግጭት ሲያጋጥማቸው እንኳን የሚፈቱበት ናጋ ቦረና (የቦረና ሰላም) የሚባል ተቋም እንዳላቸው የተወቀ ነው። ይህ ናጋ ቦረና የተባለ ተቋም ሰላማዊና የተረጋጋ የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲኖርም እንደሚሠራ የእኛዎቹ ብቻ ሳይሆኑ፣ የውጭ ምሁራንም በጥናታቸው ያረጋገጡት እውነት ነው፡፡

 እንዲህ ያሉ የአብሮነት ጠንካራ እሴቶችን በማጠናከር ድህነት፣ ኋላቀርነትና ትርምስን ማስቀረት ይሻላል? ወይስ በተሳከረ የብሔር ፖለቲካ መከራን ሲጋቱ መኖር? የሚሉትን ምርጫዎች በወጉ አጢኖ ለውጥ መሻት ግድ የሚል ይሆናል፡፡ ይህም ራስን በራስ እየመሩ በመቻቻል፣ በመከባበርና በእኩልነት ከመኖር፣ ችግሮች ሲፈጠሩም በሰላማዊ መንገድ ከመፍታት ባህል ጋር ሳይጋጭ፣ ብሔሮች ራሳቸውን በራሳቸው እያስተዳደሩ ከሚኖሩበት ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ ሥርዓት ጋርም ሳይጣላ ሊታረም እንደሚችል መዘንጋት አይገባም፡፡

በአገራችን ለትርምስና አለመተማመን በር እየከፈተ ስላለው ዘውግ መራሹ ፌዴራሊዝም፣ የሕዝቦችን አብሮነት ማዳከም ትልቁን ሚና እየተጫወተ ያለው ሕዝቡ ሳይሆን ጥገኛው ፖለቲከኛ እንደሆነ በዚሁ በጠቃቀስነው አካባቢ አንድ አብነት ልጥቀስ (የመጪው ጊዜ የብልፅግና ቀዳሚ ትኩረትም እንዲህ ያለውን የለየለት መራኮት ማስቀረት ሊሆን እንደሚገባ በማስታወስ ጭምር)፡፡

ጊዜው 1987 ዓ.ም. ነበር፡፡ በወቅቱ በተካሄደው አንደኛው ዙር አገራዊ ምርጫ አንድ ስማቸውን ለመጥቀስ የማልፈልግ ባለሥልጣን የገርባ ጎሳ አባል በኦሮሞ ማንነት፣ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) አባል በመሆን በድርጅቱ አቅራቢነት የኦሮሚያ ሞያሌ ወረዳን በመወከል፣ የፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ይመረጣሉ። አቶ ሸኑ ከ1988 እስከ 1997 ዓ.ም. ለሁለት ዙር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካገለገሉ በኋላ ጊዜያቸውን ጨርሰው ወደ መጡበት አካባቢም ይመለሳሉ።

ከዚህ በኋላ የክልሉ መንግሥት ግለሰቡን የቦረና ዞን የሕዝብ አደረጃጀትና ማስፈር መምርያ ኃላፊ አድርጎ ይሾማቸዋል። በዚህ የኃላፊነት ቦታ ለተወሰነ ዓመት ካገለገሉ በኋላ ክልሉ ከኃላፊነታቸው ያነሳቸዋል። ይኼኔ ማንነታቸውን ወደ ሶማሌነት በመቀየር የሶማሌ ክልልን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ ሶማሌ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) አባል ሆነው የሶማሌ ክልል ሞያሌ ወረዳ አስተዳደር ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት ቦታ ይሾማሉ።

ይኼኔ ገርባ የተባለው የእሳቸው ጎሳ ሁሉም አባላት ሶማሌዎች መሆን አለባቸው የሚል አቋም ማራመድ ይጀምራሉ። እዚህ ላይ ግለሰቡ በሁለቱ ክልሎች ሕዝቦች መካከል የእርስ በርስ ግጭት ቀስቅሰዋል ብዬ እየወነጀልኳቸው አለመሆኑ እንዲታወቅልኝ እፈልጋለሁ። ግለሰቡን የጠቀስኳቸው በአጠቃላይ በአካባቢው በግለሰቦችና በሥልጣን ፈላጊዎች ፍላጎት ወደ ግጭት ሊያመራ የሚችል ሁኔታ እንዴት እንደሚፈጠር ለማሳየት ስለሚያስችል ነው ያስታወስኩት።

እርግጥ ነው እሳቸው ማንነታቸውን ከኦሮሞነት ወደ ሶማሌነት የመለወጥ መብት አላቸው። በራሱ ምርጫ ኦሮሞ ነኝ ብሎ በሰላም የሚኖረው የገርባ ማኅበረሰብ አባላት በሙሉ ሶማሌ መሆን አለባቸው ብለው ሕዝቡን መቀስቀሳቸውን ግን ጤናማ ውጤት ይኖረዋል ብሎ መገመት ስህተትነቱ ያይላል። ግለሰቡን በምሳሌነት አነሳሁ እንጂ፣ በሁለቱ ክልሎች ብቻ ሳይሆን በርከት ባሉ አካባቢዎች የዚህ ዓይነት ሥልጣንና ጥቅም እያሸተቱ የሚዋልሉ በርካታ ፖለቲከኞች አሉ።

በእንዲህ ዓይነት ጥቅምና ሥልጣን አሳዳጅ የበታች አመራሮችና ፖለቲከኞች አካሄድ የአካባቢው ማኅበረሰቦች፣ በሕዝበ ወሳኔ ባፀደቁት ወሰን ውስጥ ረግተው እንዳይኖሩ የሚያደርጉ ግጭቶች ሲቀሰቀሱ ቆይተዋል። ድርቅ፣ ረሃብና ድህነትም ቢሆን በሕዝቡ ላይ እንደተጫነበት ይኖራል፡፡ እናም እንደ አዲስ ሥርዓትና በአገር ላይ ለውጥ እንዲመጣ እንደሚፈልግ ትውልድ መሻገር የሚያስፈልገው እንቅፋት ይህ ነው፡፡

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ በመከባበርና በእኩልነት ላይ በተመሠረተ የሕዝብ አንድነት የሚኖርበት ፌዴራላዊ ሥርዓት ከመገንባት ውጪ አማራጭ የለውም፡፡ በኢሕአዴግ ኮቴ ላይ ቆሞ ለውጥ እየተመኘ ያለው ብልፅግና ግን ካለፈው የውደቀት ታሪክ ተምሮ በተመጣበት የዘውግ ፌዴራሊዝም ላይ የተደቀኑ ሳንካዎችን ማስወገድ ካልቻለ፣ ሕዝቡ በተለይም በዳር አካባቢ ያለው የታዳጊ ክልል ሕዝብ ከሰው ሠራሽ ግጭትም ሆነ ከተፈጥሮ ችግር ለመውጣት መቸገሩ አይቀርም፡፡ ድህነቱም እንዲህ በቀላሉ ይወገዳል ማለት ዘበት ነው፡፡ ስለዚህ የቆምንበትን መሠረት መፈተሽ ከቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል እላለሁ፡፡

ከአዘጋጁጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ