የወላይታ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ በደቡብ ክልል የሚገኝ ‹‹ብቸኛው የእርሻ ኮሌጅ›› ነው፡፡ ከደቡብ ክልል ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ ተማሪዎችን በመካከለኛ ግብርና ባለሙያዎችን ሲያፈራ ቆይቷል፡፡ በኮሌጁ የመማር ማስተማርን ጨምሮ፣ መሠረታዊ የግብርና ሥራዎችን በተግባር እንዲሁም የማኅበረሰብ አቀፍ ትምህርትን ይሰጣል፡፡ ከ1972 ዓ.ም. የተመሠረተው የወላይታ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ 18ኛ ዙር ተማሪዎችን በ2013 ዓ.ም. አስመርቋል፡፡ በአጠቃላይ ከምሥረታው ጀምሮ ከ22 ሺሕ በላይ ተማሪዎችን ማስመረቅ ችሏል፡፡ ዘንድሮ ከ2000 በላይ የሦስተኛና አራተኛ ዓመት ተማሪዎች እያስተማረ ይገኛል፡፡ ስለኮሌጁ አጠቃላይ እንቅስቃሴ በተመለከተ ዳዊት ቶሎሳ የወላይታ ሶዶ ግብርና ኮሌጅ ዲን መርክነ መሰኔን (ረዳት ፕሮፌሰር) አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የኮሌጁ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
መርክነ (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- ኮሌጁ 72 ሔክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን ከዚያ ውስጥ 32 ሔክታር መሬት ለሠርቶ ማሳያ አውሏል፡፡ በኮሌጁ ከ40 በላይ የከብት ዕርባታ፣ የዶሮ ዕርባታ፣ አትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም የወተት ማቀናበሪያዎች ይገኛሉ፡፡ ሌላው 300 ሺሕ የተዳቀለ አቮካዶ እየለየ ሲሆን በቅርቡም ለአርሶ አደሩ ያደርሳል፡፡ የወላይታ ሶዶ ቡና ዓለም አቀፍ ስም ኖሮት በገበያ ላይ እንዲውል በኮሌጁ እየተሠራ ይገኛል፡፡ ከዚህም ባሻገር የንብ፣ የሃር ሀብትና ለግብርና የሚያስፈልጉ ሙሉ ግብዓቶች በኮሌጁ ይገኛሉ፡፡ ኮሌጁንም ሙሉ በሙሉ እንደ አዲስ ለማደስ ጨረታ አውጥተናል፡፡
ሪፖርተር፡- ኮሌጁ ተማሪዎችን በምን መሥፈርት ይቀበላል?
መርክነ (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- ቀደም ብሎ በክልላችን ሥር ከሚገኙ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የሚላኩትን ተማሪዎች በሙሉ ተቀብለን እናስተምር ነበር፡፡ በሒደት ግን በደንብ ሳይለዩ የሚላኩት ተማሪዎች ቁጥር እየበዛ መምጣቱን ተከትሎ የትምህርት ጥራታችን ላይ እክል ይፈጥርብን ጀመር፡፡ ከዛም ከቦርዱ ጋር ከተወያየን በኋላ በተመሳሳይ አካሄድ መጓዝ እንደሌለብንና የመጣውን ተማሪ በፈተና ብቻ ተመዝኖ መግባት እንዳለበት ተወሰነ፡፡ ከቦርዱ ጋር ውይይት ካደረግን በኋላ ግን በኮሌጃችን የሚሰጠው ትምህርት 70 በመቶ የተግባር እንዲሆንና ቀሪው 30 በመቶ ደግሞ በክፍል ውስጥ በትምህርት እንዲሰጥ ተደረገ፡፡
ሪፖርተር፡- ከኮሌጁ የተመረቁ ተማሪዎች ወደ አርሶ አደሩ ወርደው የተማሩትን ተግባራዊ ማድረጋቸው እንዴት ይገመገማል?
መርክነ (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- ከዚህ ቀድም ከኮሌጁ ትምህርት የሚወስዱት ተማሪዎች፣ በክፍል ውስጥ ብቻ የሚጠናቀቅ የነበረ ሲሆን በተግባር ወደ አርሶ አደሩ ወርደው ለመሥራት ይቸገሩ ነበር፡፡ ከኮሌጁ ተመርቀው የወጡትም ተማሪዎች ምን ያክል አርሶ አደሩ ጋ ወርደው የተማሩትን ተግብረዋል የሚለውም ላይ ጥናት ተደርጓል፡፡ በጥናቱም መሠረት ተማሪዎቹ ራሳቸውን ከመግለጽ አንፃር፣ ከቋንቋ እንዲሁም ዘመናዊውን የግብርና አሠራርን ለአርሶ አደሩ የማስተላለፍ ክፍተቶች እንደነበሩ ተረድተናል፡፡ ለዚህም ዋንኛ መንስዔ የነበረው ሁለት ነገር ነው፡፡ አንደኛው ተማሪዎቹ የመጡበት የኋላ ዳራ ወይም መነሻ ሲሆን ሁለተኛው ኮሌጁ ቀድሞ የነበረው ስምና በመሀል ግን የነበሩት ክፍተቶች ዋንኛ መንስዔዎች ነበሩ፡፡ በሒደት ግን ችግሩን ከክልሉ ግብርና ቢሮና በኮሌጁ አቅራቢያ ላይ ከሚገኙ የእርሻ ተቋማት እንዲሁም፣ ከተለያዩ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር ተቀራርበን በመሥራት ተማሪዎቹ በቂ ዕውቀት እንዲሰንቁ አድርገናል፡፡ ከዚህም ባሻገር ተማሪዎች አጫጭር ሥልጠናዎችን እንዲወስዱ እንዲሁም ክረምት ወደ አርሶ አደሩ ወርደው የተግባር ሥራ እንዲሠሩ ተደርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- የኮሌጁ የትምህርት አሰጣጥና ጥራት ምን ይመስላል?
መርክነህ (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- በኮሌጁ የትምህርት ጥራት ችግር ይስተዋል ነበር፡፡ አንደኛው ችግር የሠራተኛው ቁርጠኝነት ችግር ነው፡፡ ይህንንም ለመፍታት በርካታ ዕርምጃዎች ወስደናል፡፡ ሌላኛው የፆታ ትንኮሳ የትምህርት ሒደቱ ላይ እንቅፋት ሆኖ ነበር፡፡ የመማር ማስተማሩ 70 በመቶ በተግባር ይሆን የሚለውን ተማሪዎችን ለማሳመን ተቸግረን ነበር፡፡ ሆኖም በሒደት የተለያዩ ሥልጠናዎችን እየሰጠን ችግሩን መቅረፍ ችለናል፡፡ በአንፃሩ ኮሌጁ አሁን ላይ የተሻለ የበጀት አቅምና ቆራጥ አስተዳደር ያለው እንዲሁም ጥራት ያላቸው መምህራንም ይዞ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ አንዳንድ ተማሪዎች ግብርናን አለመውደድና ወደ አርሶ አደሩ ወርዶ የመሥራት ፍላጎት የሌላቸው ነበሩ፡፡ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እያዘጋጀን ጥሩ የትምህርት ፍላጎት እንዲኖራቸውና በአግባቡ እንዲከታተሉ ግንዛቤ መፍጠር ችለናል፡፡ አሁን ላይ ግን እያንዳንዱን ችግር እየተከታተልንና እየፈታን ግብርናውን ሊያሻሽሉና ሊለውጡ የሚችሉ ተማሪዎችን እያፈራን እንገኛለን፡፡
ሪፖርተር፡- በአገር አቀፍ ደረጃ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ኮሌጁ በዚህ ረገድ የሠራው ሥራ ምን አለ?
መርክነህ (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- ከዚህ ቀደም በክልሉ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች የበጋ መስኖ ስንዴ ማልማት የተለመደ አይደለም፡፡ የበጋ መስኖ ልማት ለመጀመር በኮሌጁ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያለውም መሬት እንዲሁም የአካባቢው አየር ንብረት አመቺ እንዲሆን ማመቻቸት ነበረብን፡፡ ከዛም የሚዘራውን የእህል ዓይነት መምረጥ፣ ማሳውን ማዘጋጀትና ኬሚካሎችን ማዘጋጀት ነበረብን፡፡ ምንም እንኳ ቀላል የነበር ባይሆንም በአንድ ሔክታር መሬት የበጋ ስንዴ ማልማት ችለናል፡፡ ውጤቱም ጥሩ ነው፡፡ ተማሪዎቹም የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እንዴት ማልማት ይቻላል የሚለውን በዚህ አጋጣሚ ለአርሶ አደሩ የዕውቀት ሽግግር እንዲያደርጉ ዕድል ከፍቶላችዋል፡፡
ሪፖርተር፡- የኮሌጁ ቀጣይ ዕቅድ ምንድነው?
መርክነህ (ረዳት ፕሮፌሰር)፡- ኮሌጁ ዘንድሮ ከቴክኒክና ሙያ ወደ ኮሌጅ ደረጃ አድጓል፡፡ በኮሌጃችን የአሥር ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ ነድፈናል፡፡ ኮሌጁ በስትራቴጂክ ዕቅዱ መሠረት በርካታ ሥራዎች ሊከውን እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ ተማሪዎች የአርሶ አደሩን ባህላዊ የግብርና አሠራር ወደ ዘመናዊ እንዲቀይሩ የሚችሉበትን አቅም እንዲፈጥሩ ይደረጋል፡፡ ከዚህ ቀደም እንደነበረው ተማሪን ለብ ለብ አድርጎ መልቀቅ ሳይሆን፣ በቂ ዕውቀት አግኝቶ እንዲወጣ፣ ትምህርትና ክህሎትን አጣምሮም የመሥራት አቅም ያለውን ተማሪ ማብቃት ዋናው ግባችን ነው፡፡ ከዛም ባሻገር በአገሪቷ ካሉ 24 አቻ የትምህርት ተቋማት መካከል ሞዴል ሆኖ ለመውጣት እየሠራን ነው፡፡ የዚህ ኮሌጅ ተማሪዎች እንደ አገር ግብርናው ማሻሻል የሚችሉና ለሌሎች ምሳሌ ሆነው እንዲወጡ ማብቃት አለብን ብለን ግብ አስቀምጠናል፡፡