- የሚገነባው ማዕከል በ4,040 ካሬ ሜትር ላይ ያርፋል
በአዲስ አበባ ከተማ ከልማት መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎችን ለመከላከል የሚያግዝ ማዕከልን እንደሚገነባ የከተማው አስተዳደር እሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ አትክልት ተራ አካባቢ በ4,040 ካሬ ሜትር ላይ የሚያርፈውን የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከያ ማዕከል ግንባታ ለማስጀመር የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ እሑድ መጋቢት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ላይ የመሠረት ድንጋይ አስቀምጠዋል፡፡
የእሳትና አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ሰለሞን ፍሰሐ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በከተማዋ ዘመናዊነት የተላበሱ የእሳትና አደጋዎች መከላከያ ማዕከሎችን ቁጥር በመጨመር አደጋዎችን መከላከል ይገባል፡፡
የሚገነባው ሕንፃ ባለስድስት ወለልና ዘመናዊነት የተላበሰ መሆኑን፣ ለግንባታው ማስጀመርያ አራት ሚሊዮን ብር መመደቡን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡
ግንባታው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ ምን ያህል ብር ይፈጃል የሚለውን ለጊዜው አለማወቃቸውን የተናገሩት አቶ ሰለሞን፣ ለግንባታው የሚውለውን ቀሪ ብር በ2015 በጀት ዓመት የሚለቀቅላቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ግንባታውንም በሁለት ዓመት ከስድስት ወራት በሆነ ጊዜ ውስጥ አጠናቅቆ ለመጨረስ ስምምነት መደረጉን ለግንባታው ከሚውሉ ጥሬ ዕቃዎች ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ችግር ስለሚኖር ጊዜውን ማስረዘሙ እንደ አማራጭነት ታይቷል ብለዋል፡፡
አብዛኛው ጊዜ አደጋ እየደረሰ ያለው የገበያ ማዕከሎች ላይ መሆኑን፣ ባለፉት ስምንት ወራት ውስጥ በገበያም ሆነ በኢንዱስትሪ ቦታዎች ላይ ከፍተኛ አደጋ መታየቱን ኃላፊው ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የሚገነባው ማዕከል የገበያ ቦታን ያማከለ በመሆኑ፣ በጊዜው የሚደርሱ አደጋዎችን በአፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንደሚረዳ ገልጸው፣ ይህንን ታሳቢ በማድረግ አቃቂና አያት አካባቢ በተመሳሳይ መልኩ ግንባታ ለማከናወን የቦታ ይዞታ መረከባቸውን አክለዋል፡፡
በከተማዋ በአሁኑ ወቅት ዘጠኝ ማዕከሎች እንዳሉ ያስታወሱት ኃላፊው፣ እነዚህም ማዕከሎች እሳትና ድንገተኛ አደጋዎች በሚከሰትበት ጊዜ አፋጣኝ የሆነ ምላሽ እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በገበያ፣ በኢንዱስትሪና በሌሎች ቦታዎች ላይ የእሳትና ድንገተኛ የቅድመ መከላከያ ሥርዓት እንደሌለ፣ ቢኖሩም እንኳን በተቋሞች ላይ የሚገኙ ሠራተኞች ስለመከላከያው መሣሪያ በቂ የሆነ ግንዛቤ እንደሌላቸው አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡ ለእሳትና ለተለያዩ ነገሮች ተጋላጭ የሆኑ ቦታዎችን ኮሚሽኑ የመለየት ሥራ እየሠራ እንደሆነ፣ በተለይም ደግሞ ለእሳት አደጋ ተጋላጭ የሆኑ ግብዓቶችን ተቋሞች እንዲያርቁ የሚያስችል ሕግ መውጣቱን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በእያንዳንዱ ተቋም ላይ የሴፍቲ መከላከያ ሲሊንደርና ሌሎች ግብዓቶችን ተቋሞች እንዲያሟሉ የሚል ትዕዛዝ መውጣቱን፣ ይህም በከተማዋ የሚታየውን አደጋ በተወሰነ መልኩ ሊቀርፍ እንደሚችል ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
ከልማት መስፋፋት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ የእሳትና አደጋ ችግሮችን ለመቅረፍ ተቋሙ እየሠራ መሆኑን፣ በተለይም ከከተማዋ መውጫ ቦታዎች ላይ ሆነ፣ ከተማ ውስጥ ያሉ ውስን ቦታዎችን ላይ ፈጥኖ ለመድረስ ትልቅ ችግር እንደሆነባቸው የሚገልጹት አቶ ሰለሞን፣ ይህንን ችግር ለመታደግ እንደ እነዚህ ዓይነት ማዕከሎችን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
ከኢኮኖሚ ዕድገት፣ ከማኅበረሰቡ እንቅስቃሴና ከልማት መስፋፋት ጋር በተያያዘ የሚያጋጥሙ የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎችን ለመቆጣጠር የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች ተናግረዋል፡፡
ገበያና ሕዝብ የሚበዛባቸው ቦታዎችን በመለየት የእሳት አደጋ ሥጋቶችን መቆጣጠር እንደሚያስፈልግ ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሚያስፈልጋቸውን አካባቢዎች በመለየትና በማቋቋም ለማኅበረሰቡ አኗኗር መሻሻል ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሠራና አሁንም የተጀመረው ፕሮጀክት በታቀደለት ጊዜ ተጠናቆ እንዲያልቅ ክትትል የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል፡፡