Wednesday, July 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኪሳራ እንደሚያስመዘግብ ዕቅድ የተያዘለት የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን 91.5 ሚሊዮን ብር አተረፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸሙ የ10.7 ሚሊዮን ብር ኪሳራ ያስመዘግባል ተብሎ ዕቅድ ተይዞለት የነበረው የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ ከታክስ በፊት የ91.5 ሚሊዮን ብር ትርፍ አገኘ፡፡

ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ መጀመሪያ ዕቅዱን ሲይዝ፣ በመጀመሪያው መንፈቅ 1.23 ቢሊዮን ብር አገኛለሁ ብሎ የነበረ ሲሆን፣ የዚሁ መንፈቅ ወጪ ደግሞ 1.24 ቢሊዮን ብር እንደሚደርስ ተጠብቆ ነበር፡፡ ይኼ ቁጥር የኮርፖሬሽኑ ወጪ ከገቢው እንደሚበልጥ በማሳየቱ በስድስት ወር ውስጥ 10.7 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንደሚመዘገብ ታስቦ ነበር፡፡

የኮርፖሬሽኑ የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ የበጀት ዓመቱ ስድስት ወር የዝግጅት ምዕራፍ ተደርጎ የሚቆጠር በመሆኑ ብዙውን ጊዜ ገቢ የሚሰበሰብበት ወቅት አይደለም፡፡ ኮርፖሬሽኑ የሚያቀርባቸው የግብርና ግብዓትና አገልግሎቶች ተፈላጊነታቸው የሚጨምረው በበልግና መኸር ወቅቶች በመሆኑ፣ እንዲሁም የመጀመሪያው ስድስት ወር ኮርፖሬሽኑ እንደ ምርጥ ዘር ያሉ ግበዓቶቹን የሚሰበስብበትና ከውጪ የሚያስገባበት በመሆኑ እንደሆነ አቶ ጋሻው ገልጸዋል፡፡

ይሁንና ኮርፖሬሽኑ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አጋማሽ 1.46 ቢሊዮን ብር በማግኘት የዕቅዱን 118 በመቶ አሳክቷል፡፡ በስድስት ወሩ ለወጪ የታቀደው ገንዘብ በአሥር በመቶ ጨምሮ ወደ 1.37 ቢሊዮን ብር ያደገ ቢሆንም፣ ገቢውም በመጨመሩ ኮርፖሬሽኑ 91.5 ሚሊዮን ብር ሊያተርፍ ችሏል፡፡

እንደ አቶ ጋሻው ገለጻ፣ ይኼ ትርፍ የተገኘበት ዋንኛው ምክንያት በዓለም ገበያ ላይ የዋጋ ለውጥ በመኖሩና የውጭ ምንዛሪ ላይም ልዩነት በመታየቱ የመጣ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ትራክተርና መለዋመጫ ያሉ የእርሻ መሣሪያዎችን አስቀድሞ ያገባ በመሆኑ፣ የውጭ ምንዛሪ ዋጋው ሲለወጥ ትርፍ አስገኝቶለታል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በዚህ ወቅት ሽያጩ ብዙ ያልነበረው የፈሳሽና ጠጣር ማዳበሪያ አቅርቦት፣ በመንግሥት አቅጣጫ ለበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በብዛት እንዲቀርብ መደረጉ፣ የኮርፖሬሽኑን የኪሣራ ዕቅድ ወደ ትርፍ ቀይሮታል፡፡ እንደ ፀረ ዓረምና ፀረ ነፍሳት ያሉ የአግሮ ኮሚካል ውጤቶችም ከተለመደው በተለየ በብዛት መሸጣቸውን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከዚህ ቀደም ከስኳር ኮርፖሬሽን ጋር ገብቶ የነበረው የቆየው የኦሞ ኩራዝ የማሳ ዝግጅት ስምምነት ለዓመታት ሲራዘም በመቆየቱ፣ ስምምነት በተገባበት ዋጋ ሥራውን መሥራት የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽንን ኪሣራ ውስጥ ጥሎት ነበር፡፡ አሁን ግን በሁለቱ ኮርፖሬሽኖች ስምምነት ይኼ ውል በመቋረጡ የኮርፖሬሽኑ ኪሣራ እንዲቀንስ አድርጎታል፡፡

አቶ ጋሻው እንደሚገልጹት ኮርፖሬሽኑ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ትርፋማ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመትም ከታክስ በፊት 174.5 ሚሊዮን ብር አትርፏል፡፡ በዚህ ዓመት 200 የሚሊዮን ብር ትርፍ ለማግኘት ያቀደው የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከመጀመሪያው ቢሆንም ይኼንን ትርፍ ለማግኘት አስቦ የነበረው በሁለተኛው የበጀት ዓመት አጋማሽ መሆኑ ተገልጿል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች