Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበሶማሌ ክልል የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ለማምረት ፈቃድ የወሰደው ፖሊ ጂሲኤል ማስጠንቀቂያ ተሰጠው

በሶማሌ ክልል የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ለማምረት ፈቃድ የወሰደው ፖሊ ጂሲኤል ማስጠንቀቂያ ተሰጠው

ቀን:

የቻይናው ኩባንያ ፖሊ ጂሲኤል በሶማሌ ክልል ለሚያካሂደው የነዳጅና ጋዝ ልማት ፕሮጀክቶቹ በቂ ኢንቨስትመንት ካፒታል እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ካላቀረበ፣ ፈቃዱን ያለ ተጨማሪ ማስታወቂያ እንደሚሰርዝ የማዕድን ሚኒስቴር አስጠነቀቀ።

የማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ከፖሊ ጂሲኤል ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች ጋር ባለፈው ሳምንት በጽፈት ቤታቸው ውይይት ማድረጋቸውን፣ ይህንንም ተከትሎ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ ያዘለ ይፋዊ ደብዳቤ ለኩባንያው መላካቸውን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል።

የሪፖርተር ምንጮች እንደሚሉት፣ የቻይናው ኩባንያ በሶማሌ ክልል ኦጋዴን ውስጥ የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት አምርቶ ኤክስፖርት ለማድረግና የነዳጅ ዘይት ለመፈለግ እ.ኤ.አ. በ2013 ፈቃድ ያገኘ ቢሆንም፣ የተወሰኑ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ያለፈ የተጨበጠ የፕሮጀክት ልማት አላካሄደም። 

- Advertisement -

የማዕድን ሚኒስትሩ ከሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን ከፖሊ ጂሲኤል የሥራ ኃላፊዎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት፣ ኩባንያው ልማቱን ለማካሄድ የሚያስችል በቂ የፋይናንስ አቅም እንደሌለው መታወቁን ምንጮች ገልጸዋል።

ኩባንያው ለአጠቃላይ የፕሮጀክት ልማቱ የሚያስፈልገው ኢንቨስትመንት ካፒታል 4.2 ቢሊዮን ዶላር መሆኑን ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል።

በማዕድን ሚኒስትሩ ተፈርሞ የወጣውን የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ሪፖርተር መመልከት የቻለ ሲሆን፣ ሚኒስትሩ ታከለ (ኢንጂነር) በዚህ ደብዳቤያቸው ኩባንያው በሶማሌ ክልል የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ለማምረት ከሚያስፈልገው አጠቃላይ የኢንቨስትመንት ካፒታል ውስጥ 30 በመቶውን ከሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በፊት በብሔራዊ ባንክ እንዲያስመዘግብ፣ ቀሪውን የኢንቨስትመንት ካፒታል ኩባንያው በገለጸው መጠን በብድር ስለማግኘቱ ማስተማመኛ እንዲያቀርብ አሳስበዋል።

ይህ ካልሆነ ግን የማዕድን ሚኒስቴር ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ መስጠት ሳያስፈልገው የኩባንያውን ፈቃድ እንደሚሰርዝ፣ ለኩባንያው በላኩት ደብዳቤ አስታውቀዋል።

በመሆኑም ኩባንያው በተሰጠው ማስጠንቀቂያ መሠረት ፕሮጀክቱ ከሚጠይቀው አጠቃላይ ወጪ ውስጥ 30 በመቶውን፣ ማለትም 1.26 ቢሊዮን ዶላር የሚሆነውን እስከ ሰኔ 23 ድረስ ወደ ኢትዮጵያ በማስገባት በብሔራዊ ባንክ ማስመዝገብ ይጠበቅበታል። 

ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ ግን ኩባንያው ይህንን ለማድረግ የሚያስችል የፋይናንስ አቅም ቢኖረው ኖሮ፣ ያለፉትን ዘጠኝ ዓመታት መጠበቅ አያስፈልገውም ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ ኩባንያው በገባው ውል መሠረት እንደ ማንኛውም በኢትዮጵያ ፈቃድ ያገኘ የማዕድን ኩባንያ የሚጠበቅበትን ለማኅበረሰባዊ ኃላፊነት የሚውል የድርሻ ክፍያ እንኳን መወጣት እንዳልቻለ ምንጮች ገልጸዋል።

ኩባንያው ለማኅበረሰባዊ ኃላፊነት 50,000 ዶላር በየዓመቱ ማዋጣት ያለበት ቢሆንም፣ ይህንን ክፍያ ላለፉት አምስት ዓመታት እንዳልከፈለ አስረድተዋል።

ሪፖርተር በተመለከተው የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ላይም ኩባንያው ላልከፈለው የማኅበረሰባዊ ኃላፊነት መዋጮ 1.7 ሚሊዮን ዶላር እስከ ግንቦት 16 ቀን 2014 ድረስ በሙሉ እንዲከፍል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶታል።

የቻይናው ኩባንያ በሶማሌ ክልል የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ወደ ፈሳሽ በመቀየር ከኦጋዴን ወደ ጂቡቲ በሚዘረጋ የቧንቧ መስመር ለውጭ ገበያ፣ በተለይም ወደ ቻይና ለመላክ ፍላጎት እንዳለው ይታወቃል።

ከዚህም በተጨማሪ በኦጋዴን ክልል የተገኘውን የነዳጅ ክምችት ፈልጎ ለማልማት ፈቃድ የወሰደ ሲሆን፣ ከሦስት ዓመት በፊት የነዳጅ ክምችት ማግኘቱንና ነዳጁን ለማውጣት እንቅስቃሴ መጀመሩን ይፋ ካደረገ በኋላ በተጨባጭ ወደ ምርት መግባት አልቻለም። 

ሪፖርተር የኩባንያውን ኃላፊዎች ምላሽ ለማካተት ጥረት ቢያደርግም አልተሳካም።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...