የግል አየር መንገዶች ኤርፖርቶች ኢንተርፕራይዝ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥር እንዲተዳደር በመደረጉ፣ እኩል አገልግሎት እንዳናገኝ አድርጎናል አሉ።
የኤርፖርቶች ኢንተርፕራይዝ ከአራት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥር እንዲተዳደር መደረጉ የሚታወስ ሲሆን፣ የግል አየር መንገዶችም የሚፈልጓቸውን አገልግሎቶች በዚሁ መሠረት እንዲያገኙ ተወስኗል። ነገር ግን የግል አየር መንገዶች አገልግሎቶችን ተፎካካሪያቸው ከሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲጠይቁ መደረጋቸውን ትክክል አይደለም ሲሉ ተቃውመዋል።
የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎትና አቪዬሽን አካዳሚ ባለቤትና ማኔጂንግ ዳይሬክተር ካፒቴን ሰለሞን ግዛው፣ ከኤርፖርቶች ኢንተርፕራይዝ ሲያገኟቸው የነበሩ አገልግሎቶችን በአሁኑ ወቅት በተገቢው መንገድ እያገኙ እንዳልሆነ ተናግረዋል። በተለይም ለግል አየር መንገዶች ትልቅ ፈተና የሆነው የማረፊያ ቦታ ጥያቄ እስካሁን ድረስ አለመመለሱን ገልጸዋል።
በዚህም ምክንያት ያሏቸውን 14 ያህል አውሮፕላኖች በሙሉ አቅም ለማሠራት መቸገራቸውን ተናግረው ነፃና ገለልተኛ በሆነ መንገድ ጥያቄዎቻችን ሊመለሱ ይገባል ብለዋል። ኢንተርፕራይዙን የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ፉክክሩን በመፍራት የሚቀርቡለትን ጥያቄዎች እያስተናገደ አይደለም ብለዋል።
ሌላው ችግር የጥገና ቦታ እጥረት ሲሆን ይህም ለተጨማሪ ወጪ እየዳረጋቸው እንደሚገኝ ካፒቴን ሰለሞን አስረድተው፣ የጥገናና ዕድሳት አገልግሎት የሚያገኙት ኬንያ፣ ናይሮቢ በመሄድ እንደሆነ ይገልጻሉ። ‹‹ለጥገናና ለዕድሳት አውሮፕላኖችን ወደ ኬንያ መላካችን በአንድ አውሮፕላን ከ10,000 ዶላር በላይ ተጨማሪ ገንዘብ ወጪ እንድናደርግ አስገድዶናል፤›› ብለዋል። ‹‹ይህም በተለይ በኮቪድና በሌሎች አገራዊ ችግሮች የተጎዳውን የግል አየር መንገዶች ቢዝነስ እንዳያገግም እያደረገው ነው፤›› በማለት ትክክለኛ አገልግሎት እንዲገኝ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ኢንተርፕራይዝ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
በአቪዬሽን ዘርፍ በተለይም ለግል አየር መንገዶች ላይ በቂ ትኩረት እንዳልተሰጠ የሚገልጹት ካፒቴን ሰለሞን፣ ለዘርፉ በቂ ድጋፍ ለማድረግ በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ደረጃ የሲቪል አቪዬሽን አማካሪ እንዲቋቋም ጠይቀዋል።
የአኳሪየስ አቪዬሽን ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬሕይወት ተሰማ በበኩላቸው፣ የማረፊያ ቦታ ከፍተኛ ችግር በመሆኑ በውጭ ምንዛሪ ለሚከፈል ተጨማሪ ወጪ መዳረጋቸውን ተናግረዋል። በዚህም መሠረት በመንግሥት የማይቻል ከሆነ የግል ባለሀብቶች የማረፊያ ቦታዎችን እንዲገነቡ ምክረ ሐሳብ መቅረቡን ይገልጻሉ። ‹‹የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተመሳሳይ ሥራ ውስጥ ሆኖ ኤርፖርትን ማስተዳደር የለበትም፣ መመራት ያለበት በመንግሥት ነው፤›› ብለዋል።
የግል አየር መንገዶቹ ባነሷቸው ጥያቄዎች ላይ ለሪፖርተር ምላሽ የሰጡት የሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢኮኖሚክ ሬጉሌሽንና ስትራቴጂክ አመራር ዳይሬክተር አቶ እንደሻው ይገዙ፣ በአገልግሎቶቹ ላይ የሚነሱት ጥያቄዎች ኢንተርፕራይዙ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥር በመካተቱ የመጡ አይደሉም ይላሉ። ኤርፖርቶች ኢንተርፕራይዝ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሥር የተካተተው ሁለት ዓመታት ከፈጀ ጥናት በኋላ መሆኑን ገልጸው፣ ኤርፖርቱ በሚፈለገው ደረጃ ባለማደጉና ማሻሻያ ለማምጣት በማሰብ የተላለፈ ውሳኔ መሆኑን አስረድተዋል።
የማረፊያም ይሁን የጥገና አገልግሎት ማግኘት ያልተቻለው በቂ መሠረተ ልማት ባለመኖሩ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ቦታ ለመጠቀም በቂ ቦታ ማግኘት አለመቻሉን ተናግረዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማረፊያ፣ ለሥልጠናና ለሌሎች ጉዳዮች ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ ለመደበኛ በረራዎች ከአየር መንገዱ አውሮፕላኖች በተጨማሪ ለ13 የውጭ አየር መንገዶች አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አብራርተዋል።
‹‹በዚህም ምክንያት ለግል አየር መንገዶች የማረፊያና የጥገና ቦታ ለመገንባት የሚቻልበት መንገድ ጥናት እየተደረገበት ነው፤›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ‹‹በግል ባለሀብቶች ለማልማት የሚቻል በመሆኑ ከአዲስ አበባ ውጪ ባሉ ቦታዎች መገንባት እንደሚቻል ለመለየት እየሠራን ነው፤›› ብለዋል።
በተጨማሪም ሰባት ዓመታት የፈጀውና እስካሁን ያልፀደቀው የአቪዬሽን ፖሊሲ በተያዘው ዓመት እንደሚፀድቅ ይጠበቃል ያሉት አቶ እንደሻው፣ በተለይ በግል አየር መንገዶች የሚነሱ ጥያቄዎችን ይፈታል ሲሉ አስረድተዋል።