Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ስንዴን በቆላ አካባቢዎች የማልማቱ ሥራ በሌሎች ሰብሎች ይቀጥል!

ሰሞኑን በተለይ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ ከሰማኋቸው ዜናዎች ውስጥ እንደ አገር የቆላ ስንዴን ለማምረት እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችና እየተገኙ ያሉ ውጤቶች ቀልቤን ስበውታል፡፡

ከሁለት ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የሚመረተውን የስንዴ መጠን ለመጨመር፣ ከውጭ የሚገባውን ለማስቀረት ታስቦ እየተሠራ ያለው ሥራ በእርግጥም ተስፋ የሚሰጥ ሆኖ ተሰምቶኛል፡፡ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሱ በራሱ ትልቅ ክንውን ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

እንደተባለው በሚሊዮኖች ኩንታል የስንዴ ምርት ተመርቶ ተጨማሪ ምርት ማግኘት መቻሉም ከተሠራ ከዚህም በላይ ውጤት ሊገኝ እንደሚችል ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድም ነው፡፡

ኢትዮጵያ ታቅዶ ከተሠራባት የምትነፍገው እንደሌላት ያየንበት ነው፡፡ በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ይህንኑ ተግባር በማስፋፋት ከስንዴ ተመፅዋችነት የሚያላቅቀን ምርት ማምረት እንደምንችል አስገንዝቦናል፡፡

ከተሰጠው መረጃ መረዳት የቻልኩትም ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ የምታመርተው ምርት በቂ ያለመሆኑንና ፍላጎቷን ለመሸፈን በዓመት አንድ ቢሊዮን ዶላር ለስንዴ ግዥ እያዋለች እንደምትገኝ ነው፡፡ አሁን እያየን ያለው ጅማሮ ከዚህም በላይ ተጠናክሮ የሚሠራበት ከሆነ ግን ኢትዮጵያ ከራሷ ፍጆታ አልፋ ከስንዴ የወጪ ንግድ አንድ ቢሊዮን ዶላር አገኘች የሚል ዜና የምንሰማበት ወቅት ይመጣል፡፡

ነገር ግን በኢትዮጵያ በምርትና በአቅርቦት መካከል ያለው ልዩነት ሁሌም በገበያ ውስጥ የሚፈጥረው ክፍተት እያደገ በመሆኑ ስንዴን ወደ ውጭ ለመላክ የታሰበው ረዥም ሐሳብ በመልካም የመወሰዱን ያህል ይህ እሳቤ በጥንቃቄ መታየት አለበት፡፡ ዋናው ትኩረታችንም ራስን በምግብ መቻል ላይ ቢሆን ይመረጣል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር ዕድገት በየዓመቱ ፍጆታችንን እየጨመረው በመሆኑም ከወጪ ንግድ ዘላቂ የሆነ ጥቅም ለማግኘትና ያለምንም ክፍተት ራሳችንን ለመቻል በርትቶ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ይህንን ካደረግን ጥረታችን ስንዴን ወደ መላክ ይወስደናል፡፡ ጅምሩንም ለፓስታና ለመኮሮኒ የሚሆኑ የስንዴ ዝርያዎችን በማምረት ከፍ ልናደርገው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ለእነዚህ ምርቶች ግብዓት የሚሆን ስንዴ ከውጭ የሚገባ በመሆኑና ይህንን ማስቀረት ስለሚገባ ጅምሩን በተለያዩ መንገዶች ማዳበር ተመራጭ ነው፡፡

የስንዴ ምርት ጉዳይ በተለይ በዚህ ወቅት የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው የሚፈለግበት ዋናው ቁም ነገር ራሳችንን መመገብ ግድ ስለሚለን ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ዕቅዶችን ለጠጥ በማድረግ በሌሎች በቀላሉ ልንተገብራቸው በሚችሉ ምርቶች ላይም ማሳየቱ ተገቢ ነው፡፡

በሌላ በኩል ዛሬ ከውስጥም ሆነ ከውጭ ጠላቶች የበዙባትን አገራችንን ከችግር ለማውጣት የምንችለው እንደቆላ ስንዴ ዓይነት ሥራዎችን በሌላው አስፈላጊ የሚባሉ ምርቶች ላይ መተግበር ስንችል ነው፡፡

ዛሬ አገራችንን እንደፈለጉ ሊያደርጉ የሚሹ ወገኖች እጅ ለመጠምዘዝ ከሚጠቀሙባቸው ምክንያቶች አንዱ የምንሰጣችሁን ዕርዳታ እናቋርጣለን የሚል ጭምር በመሆኑ በምግብ ራሳችንን መቻላችን የህልውና ጉዳይ ነው፡፡ እንዲያውም ይህንን ተስፋ ሰጪ ዕርምጃ በማጠናከር ፍራንካ ያለው የግሉ ዘርፍ ሳይቀር ዓይኑን ወደ ግብርና ጣል የማድረጉ ልምምድ ከወዲሁ መጀመር አለበት፡፡

የፋይናንስ ተቋማት በግብርና ምርቶች በተለይ ከውጭ ሊገቡ የሚችሉ ምርቶችን የሚተኩ ምርቶችን ለሚያመርቱ ባለሀብቶች እጃቸውን ፈታ ማድረግ አለባቸው፡፡ ይህንን ደግሞ መንግሥት አስገዳጅ እስኪያደርግ ከመጠበቅ በመለስ አዋጭነቱን እያረጋገጡ ፋይናንስ ቢያደርጉ እነሱም ተጠቃሚ ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል አለ፡፡

የምግብ ሰብሎች ፍላጎት በየዓመቱ እያደገ የሚሄድ በየትኛውም ጊዜ ገበያ ያለው በመሆኑ አዋጪነቱ ጥያቄ ውስጥ ሊገባ አይችልም፡፡ ችግሩ ያለምንም ጥናት አያዋጣም የሚለው የተንሻፈፈ ዕሳቤ ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ሐሳብ ዳር ለማድረስ ግን መንግሥት በተለይ ለምርቱ ይሆናሉ ተብለው የሚታመንባቸውን ቦታዎች በጥናት ለይቶ በማዘጋጀት ቦታው በቀላሉ እንዲገኝ ማድረግ አለበት፡፡  

ግብርና የምናውቀው ሥራችን የመሆኑን ያህል ደረጃውን ከፍ አለማድረጋችን ብዙ ዋጋ እያስከፈለን መሆኑን በመገንዘብ፣ ከሌላው ዘርፍ በተለየ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ችግሮቻችን ሊያስተምሩን ይገባል፡፡ ግብርና የአገር መሠረት ነው፡፡ ከራሳችን ሆድ ባለፈ ተጨማሪ የገቢ ምንጫችን ማድረግ ሲገባን፣ ያለማድረጋችን ሊቆጨን ይገባል፡፡

የሰሞኑ የቆላ ስንዴ ምርትን ምሳሌ ማድረግ የወደድኩት ከተሠራ ዕድገት እንደሚኖር አመላካች የሆኑ እውነቶች በመታየታቸው ነው፡፡ ስለዚህ ከዚህ ቀደም እንደተለመደው የአንድ ሰሞን ሆይ ሆይታ እንዳይሆን በጣም መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

ሥራው ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል ያሻል፡፡ ዕገዛም ይሻል፣ ቅን መሆንንም ይጠይቃል፡፡ ግብርና የኢትዮጵያውያን መሠረት መሆኑንም የበለጠ ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡ የቱንም ያህል ብንሠለጥን ከዚህ ዘርፍ ውጪ ልንቆም የማንችል በመሆኑ ይህንን ማስተማር ያስፈልጋል፡፡

ሌላው ቀርቶ ግብርና የሥልጣኔ ምልክት መሆኑን ለልጆቻችን በትምህርት መጻሕፍት በስፋት ተካተው ከሥር ጀምሮ ማስተማር ጭምር የሚያስፈልግ ነው፡፡

በዚህ ዘርፍ ተምሮ አገር መለወጥ ትልቅ ጀግንነት እንደሆነ ሁሉ እያሳወቅን ወጣቱ በዚህ ዘርፍ እንዲሰማራ ማንቃት ግድ ይለናል፡፡

ዛሬ ያለውን የፍላጎት ክፍተት በቆላ ስንዴ መሙላት ብንችልም ነገ ተጨማሪ በላተኛ የሚፈልቅ በመሆኑ የሕዝብ ቁጥር ዕድገታችንን የመጠነ ሥራ አቅዶ መከወን ያስፈልጋል፡፡ ዛሬም እኛን ለማንበርከክ እንቅልፍ የሌላቸው ወገኖች፣ ማዕቀብ እንጥላለን ብለው ያሰቡትን ከተገበሩት ብትሩ የሚፈጥርብንን ሕመም ለማቋቋም በአገር ደረጃ በቀላሉ ልንሠራው የምንችለውን ግብርና ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሰጥተን በመሥራት ተፅዕኖዎችን ለመቋቋም ይረዳናል፡፡

በረዥም ጊዜም አገራዊ ኢኮኖሚው ላይ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ይህንን ሥራ የምንሠራው እንዲህ ያሉ ችግሮችን ለመቋቋም ኢኮኖሚውንም ለማሳደግ ቀዳሚ ዕድል በመሆኑ ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደጠቀስኩት ከውጭ የምናስገባው ስንዴ ለዳቦና ለዱቄት የሚሆነው ብቻ አይደለም፡፡ በዋጋ ወደድ የሚለውና ለመኮሮኒና ፓስታ ምርት የሚሆን የስንዴ ምርትም ነውና እነዚህን እሴት የተጨመረባቸው ምርቶች የሚያመርቱ ፋብሪካዎች ስንዴ ከማስመጣት እንዲላቀቁ ማድረግና የራሳቸው እርሻ እንዲኖራቸው ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡

ከዚህ ባለፈ ስንዴን ግብዓት አድርገው የሚያመርቱ ኩባንያዎች ሲቋቋሙ የሚጠቀሙትን ስንዴ የሚያመርቱበት አሠራር ቢኖር ይመረጣል፡፡ ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቆላ ስንዴን ለማስፋት ያደረጉት ጥረት የበለጠ እንዲመሠገን ከዚህ ጋር የተያያዙ ቀጣይ ተያያዥ ሥራዎችን ታሳቢ እያደረጉ ጠቀሜታውን በማስፋት ሁሉም የበኩልን ያድርግ፡፡ ዘላለም በስንዴ እጃችንን አንጠምዘዝ፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት