Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልነፍስ የዘራው በገና

ነፍስ የዘራው በገና

ቀን:

ናሆም ኤፍሬም ባለ አሥር አውታሩን (ክር) የበገናን ድምፅ በልጅነቱ የሰማው በቀድሞው ሬዲዮ ኢትዮጵያ ሁዳዴን ተንተርሶ በሚደመጥበት ወቅት ነበር፡፡ ይበልጥ የተዋወቀው ደግሞ በ1970ዎቹ አጋማሽ በመርካቶ በጎ አድራጎት ሕንፃ በሥራ አጋጣሚ በተመላለሰበት በዚያው በሁዳዴ ወቅት ሙዚቃ ቤቶች በሚያሰሙበት ጊዜ ነው፡፡ በመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬ ከተደረሱት የበገና መንፈሳዊ መዝሙሮች ባሻገር ከታሪክና ትውፊት የተያያዙ ድርደራዎች እነ ዓለሙ አጋ ይደረድሩ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

‹‹አባ ግራኝ ሞተ የሆዴ ወዳጅ

የሚያበላኝ ጮማ የሚያጠጣኝ ጠጅ

- Advertisement -

 እኔ መዩ ቱርክ ባይ የምሸሽ ነኝ ወይ!

ታጠቅ ብሎ ፈረስ ካሳ ብሎ ስም

ዓርብ ዓርብ ይሸበራል ኢየሩሳሌም

እኔ መዩ ቱርክ ባይ የምሸሽ ነኝ ወይ!››

ናሆም ከሚያስታውሳቸው ሌሎች ድርደራዎች መካከልም፡-

‹‹መለስ ቀለስ ብላ አየችው ቀሚሷን

ረሳችውና ካፈር መለወሷን››

‹‹ሆዴ ልመድ ልመድ

የለህምና ዘመድ፤

ሆዴ ሁን ዋሻ

የለህምና መሸሻ፤››

ይህ የሺሕ ዓመታት ታሪክ ያለውና በጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለዝማሬ አገልግሎት እየሰጠ የኖረው የበገና የዜማ መሣርያ ለቀራቢዎቹ አያሌ ዓመታት ህልውናው ለአደጋ ተጋልጦ ነበር፡፡ የሚደረድሩ ሰዎች ማነስ ብቻ ሳይሆን መሣርያውም እንደልብ አይገኝም ነበር፡፡ ከሁለት አሠርታት በፊት የአዲሱ የበገና ትውልድ መምህራኑ እነ ‹‹ሲሳይ በገና›› (የራሳቸው የበገና ማሠልጠኛ ማዕከል ያቋቋሙት የመምህር ሲሳይ ደምሴ ገብረጻድቅ ቅጽል ስም) በተነሱ ጊዜ በገና በልዩ ልዩ መንገድ ህልውናውን እየታየ መጥቷል፡፡

ነፍስ የዘራው በገና

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና በገና

የጥንቱን አቆይተን ከቅርቡ 19ኛው ምዕት ብንነሳ እንኳ በገና በነገሥታቱና በመኳንንቱ ቤት አገልግሎት ይሰጥ ነበር። የበገናው መምህር ሲሳይ ደምሴ ገብረጻድቅየበገና መማሪያበተሰኘው መጽሐፋቸው እንደጻፉት አፄዎቹ ቴዎድሮስ፣ [ተክለ ጊዮርጊስ] ዮሐንስ፣ ምኒልክ፣ ንግሥታቱ እቴጌ ጣይቱ፣ ዘውዲቱ፣ እነ ራስ መኰንን በገና ይደረድሩ ነበር። ሌሎች ነገሥታትና መሳፍንት፣ መኳንንትም መደርደር ባይችሉ እንኳ በገና ደርዳሪዎች እንደነበራቸው ይነገራል።

ንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ በ1950ዎቹ በአክሱም የኅዳር ጽዮን ዓመታዊ ክብረ በዓል ላይ በተገኙ ጊዜ ታቦተ ሕጉን ካጀቡት መካከል አንዱ የሆኑትን አለቃ ተሰማ ወልደ አማኑኤልን በገና ሲደረድሩ በትኩረት ይመለከታሉ፡፡ ይህ የበገና ሙያ አገርንና ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅም ሙያ ስለሆነ መስፋፋት ይገባዋል በማለትም አለቃ ተሰማ ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ያደርጋሉ፡፡ በወቅቱ የሙዚቃና ስፖርት ሥልጠና ይሰጥ በነበረው በቀድሞ ስሙ አምሃ ደስታ ትምህርት ቤት (የአሁኑ እንጦጦ አምባ) የበገና ድርደራን እንዲያስተምሩ ይመድባቸዋል፡፡

‹‹መጽሐፈ በገና›› በሚል ርዕስ መጽሐፍ  ያሳተሙት ዲያቆን  ዳዊት ዮሐንስ እንደገለጹት፣ በወቅቱ ከመሳፍንቱና ከመኳንንቱ፣ ከካህናምመ ወገን የሆኑና ሌሎች ወንዶችና ሴቶች በገና ድርደራን ለመማር ወደ አለቃ ተሰማ ዘንድ ይዘልቁ ነበር፡፡ ነገር ግን ትምህርቱ የሚሰጥበት መንገድ ሥርዓተ ትምህርት ተቀርፆለት፣ መማሪያ ቦታ ተዘጋጅቶለት፣ ቋሚ መምህር ተመድቦለት አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ዘመን ከአለቃ ተሰማ ትምህርት የቀሰሙት ተማሪዎች መጋቤ ስብሐት ዓለሙ አጋ፣ አቶ ገብረ ኢየሱስ፣ አቶ አድማሱ ፍቅሬ፣ አቶ ታፈሰ ተስፋዬ፣ አቶ ደምሴ ደስታ፣ አቶ ሥዩም መንግሥቱና አቶ ተድላ ተበጀ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ከነዚህ ተማሪዎች መካከል በተለይ ዓለሙ አጋ በ1965 ዓ.ም. ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በባዮሎጂ (ሥነ ሕይወት) በባችለር ዲግሪ ከተመረቁ በኋላ በሠለጠኑበት ሙያ በተጨማሪ በገናን በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ማስተማር የጀመሩበት ጊዜ ነው፡፡

በ1966 ዓ.ም. ‹‹ለመጀመርያ ጊዜ›› መጋቤ ስብሐት ዓለሙ አጋ፣ ጸጋዬ ደባልቄና ሲንትያን (ዶ/ር) የበገና ሥርዓተ ትምህርት በእንግሊዝኛ ቋንቅ ማዘጋጀታቸውን፣ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ለ3ኛና 4ኛ ዓመት ተማሪዎች በሳምንት ሁለት ቀን ትምሀርቱ ይሰጥ እንደነበረ መጽሐፈ በገና ዘክሮታል፡፡

የ1966ቱን አብዮት ተከትሎ በያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ይሰጥ የነበረው የበገና ሥልጠና እየተዳከመ በመምጣት በ1972 ዓ.ም. መቋረጡም ተመልክቷል፡፡ በኋላ ላይ በተለያዩ አጋጣሚዎች በታዋቂው የበገና ደርዳሪና የማሲንቆ ተጫዋች መምህር ጭምር የሆኑት ዓለማየሁ ፋንታ ትምህርቱ በውስን መልኩ መሰጡት አልቀረም፡፡

በቀጣይ ሁለት አሠርታት የበገና ሙያ የተመናመነበት የደርዳሪዎች ቁጥርም ያነሰበት ቢሆንም፣ ውስን መምህራን ልጆቻቸውንና ፍላጎቱ ያላቸውን ሁሉ ያስተምሩ ነበር፡፡ ከእነዚህም መካከል የበገና ደርዳሪው ገብረ ኢየሱስ ልጅ የሆነችው ሶስና ገብረ ኢየሱስና የትምወርቅ ሙላት ይገኙበታል፡፡

ፒያሳ በሚገኘው የታዋቂው በገና ደርዳሪ መጋቤ ስብሐት ዓለሙ አጋ መሥሪያ ቤት በመሄድ ሙያቸውን የሚያሳድጉም ነበሩ፡፡ በገናን ከመጥፋት ካዳኑት መካከል እሳቸውን በቀዳሚነት የሚጠቅሱ አሉ፡፡

በአሁኑ ዘመን ከተነሱ የበገና ባለሙያዎች አንዲ የሆኑት መምህር ሲሳይ ደምሴ ገብረ ጻድቅ በ1989 ዓ.ም. የበገና ትምህርታቸውን አጠናክረው በመያዝ ከድርደራ ባለፈ ራሱን የሙዚቃ መሣሪያውን በማምረት የነበረውን ዕጥረት ማቃለላቸው ይነገርላቸዋል፡፡

‹‹በገና ለምን ይጥፋ?››

በገና ለመስፋፋት ዕድል ያገኘበት 1996 ዓ.ም. ለበገና ታሪካዊት ዓመት ነች፡፡ ከዚህች ዘመን በኋላ የበገና ሙያ እንዲስፋፋ የሚያደርጉ ብዙ ለውጦች ታይቶበታል፡፡ በአዲስ አበባ በሰኔ 1996 ዓ.ም. የተዘጋጀው ጉባዔ ‹‹በገና ለምን ይጥፋ?›› በሚል መሪ ቃል ነው፡፡ በዲያቆን ዳዊት ዮሐንስ ‹‹መጽሓፈ በገና›› ላይ እንደተጠቀሰው፣ ከጉባዔው በኋላ በገናን የማስተማር አስፈላጊነት በመጥቀስ ትምህርቱ እንዲሰጥ ምክረ ሐሳባቸውን ለማኅበረ ቅዱሳን ያቀረቡት መምህር ሲሳይ ደምሴ ናቸው፡፡ በዚያው ዓመት በሐምሌ ወር  ‹›የአቡነ ጎርጎርዮስ የዜማ መሣርያዎች ማሠልጠኛ ማዕከል›› ተቋቁሞ በይፋ በገናን ማስተማር ሲጀመር ቀዳሚዎቹ መምህራን ሲሳይ ደምሴ፣ ሶስና ገብረኢየሱስና ዘውዱ ጌታቸው ነበሩ፡፡

ከሦስት ዓመት ቆይታ በኋላ ከአዲስ አበባ ውጭ በጉራጌ ዞን በሚገኘው የምሑር ኢየሱስ ገዳም ‹‹ቤተ እንዚራ›› የሚባል የበገና ትምህርት ቤት በመምህር ሲሳይ አስተባባሪነት በሀገረ ስብከቱ አማካይነት ሲቋቋም የመጀመርያዎቹን ሠልጣኞች ያስተማሩት አስተባባሪው ናቸው፡፡ ትምህርት ቤቱ እስካሁን ሥልጠና እየሰጠ ሲሆን በርካቶችን አፍርቷል፡፡ በየዓመቱም የበገና ጉባዔ በእኩሌታ ጾም (ደብረ ዘይት) እያከናወነ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል የበገናን ዕጥረት ለመቅረፍም በ2005 ዓ.ም የተቋቋመው ‹‹ሲሳይና ፍጹም የዕደ ጥበባትና የዜማ መሣርያዎች ማምረቻ›› ዓይነተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ መምህር ሲሳይ በቀጣይ ዓመትም የራሳቸውን ‹‹ሲሳይ በገና የዜማ መሣሪያዎች ማሠልጠኛ ተቋም››ን በአዲስ አበባ በማቋቋማቸው በስምንት ዓመታት ውስጥ በርካቶችን ከበገና ሙያ ጋር አስተዋውቀዋል፡፡ በአሁን ጊዜ አራት ኪሎ በሚገኘው የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ ባሉት ክፍሎች ከበገና በተጨማሪ የመሰንቆና የክራር ትምህርት ይሰጡበታል፡፡

በሌላ በኩል በየክልሉ ከተሞችም የሚገኙት የማኅበረ ቅዱሳን ማዕከላትም የበገና ሙያን በማሠልጠን ሙያው እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ እያደረጉ ናቸው፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት በዲያቆን ዳዊት ዮሐንስ አማካይነት በመቐለ ከተማ የተመሠረተው ‹‹ዳዊት በገና የዜማ መሣርያዎች ማሠልጠኛ ማዕከል፣ ከበገና በተጨማሪ በመሰንቆ (ጭራ)፣ ክራር፣ ዋሽንትና ከበሮ ሥልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ መሥራቹ  ባሳተሙት መጽሐፋቸው ጠቅሰውታል፡፡

ናሆም ከትዝታው ጓዳ የቀዳውንም እንዲህ አካፋለን፡-
‹‹ሆዴ ልመድ ልመድ
የለህምና ዘመድ፤
ሆዴ ሁን ዋሻ
የለህምና መሸሻ፡፡››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...