በመሬት አጠቃቀም ላይ የሚነሱ አለመግባባቶችን ይፈታል የተባለ የጥናት ፕሮጀክት መጀመሩን፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ፕሮጀክቱ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የሚቆይ ሲሆን ለተለያዩ ዓላማዎች የሚፈለጉ መሬቶች ከሚፈለጉበት ዓላማ ውጪ እንዳይውሉ፣ የአለመግባባት ምንጭ እንዳይሆኑና እንዳይባክኑ ለማድረግ ያለመ መሆኑን፣ በፕላንና ልማት ሚኒስቴር የፖሊሲ ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ነመራ ገበየሁ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ገልጸዋል።
ለተለያዩ ዓላማዎች የሚፈለጉ መሬቶች ጥናት ሳይደረግባቸውና ተገቢነታቸው ሳይታወቅ ፕሮጀክቶች ይገነባሉ ያሉት ሚኒስትር ደኤታው፣ ይህም የመሬት ሀብቱ ለትክክለኛ ዓላማ እንዳይውል እያደረገው መሆኑን ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ግንባታ ለአብነት ያነሱት ነመራ (ዶ/ር)፣ የፓርኮቹ ግንባታ ከተከናወነ በኋላ ለከተማ ማስፋፊያና ለሰብል ማምረቻነት የሚውሉ ናቸው የሚል ጥያቄ እንደሚቀርብላቸው ገልጸዋል።
አሁን የተጀመረው ፕሮጀክት ለግብርና፣ ለከተማ ማስፋፋት፣ ለቱሪዝም፣ ለፋብሪካና ለሌሎች ዓላማዎች የሚውሉ መሬቶችን በመለየት ለተገቢው ዓላማ እንዲውሉ ለማድረግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲ በአሁኑ ወቅት አለመኖሩን የገለጹት ነመራ (ዶ/ር)፣ የተጀመረው ፕሮጀክት ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር በመሆን የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀም ሥርዓትንና መረጃ እንዲኖር የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃና በክልሎች የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲዎች፣ ሕጎችና ተቋማዊ አደረጃጀቶችን ለማሻሻል በተመረጡ አካባቢዎች የማሳያ ሥራዎች እንደሚሠሩ አክለዋል።
እንደ ሚኒስትር ደኤታው ገለጻ በአማራ፣ በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች የሚተገበረው ፕሮጀክቱ፣ በመሬት አጠቃቀም የሚያጋጥሙ ችግሮች የተከሰቱባቸውን ምክንያቶች በመለየት፣ በሌሎችም አካባቢዎች በመተግበር ፍትሐዊ የመሬት አጠቃቀም እንዲኖር ያስችላል። ሦስቱ ክልሎች ለፕሮጀክቱ የተመረጡት እስካሁን እያጋጠሙ ያሉ የመሬት አጠቃቀም አለመግባባቶች በአብዛኛው በእነዚህ ክልሎች መሆናቸውን መነሻ በማድረግ ነው ብለዋል።
ፕሮጀክቱ በጀርመን የልማት ተቋም (GIZ) የገንዘብና የቴክኒክ ድጋፎች የሚደረጉለት እንደሆነ፣ አምስት ሚሊዮን ዩሮ ወጪ እንደተመደበለትም ለማወቅ ተችሏል፡፡