Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማትና የጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩቶች እንደ አዲስ ተቋቋሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማትና የኢትዮጵያ የጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩቶችን፣ ለማዕድን ሚኒስቴር ተጠሪ በማድረግ እንደ አዲስ እንዲቋቋሙ ወሰነ፡፡

 

የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትን ለማቋቋም የወጣው አዲሱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ፣ ከዚህ ቀደም አገልግሎት ላይ የቆዩትን የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 182/2002 እና የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትን ለማቋቋም የወጣውን ደንብ ቁጥር 288/2005 ደንብ ሽሯል፡፡

በሌላ በኩል ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 194/1992 እንዲሁ፣ በአዲሱ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ማቋቋሚያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ እንደተሻረ ታውቋል፡፡

የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ተብሎ እንደገና የተቋቋመው ተቋም ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤት ሆኖ፣ ለማዕድን ሚኒስቴር ተጠሪ እንዲሆን በማሰብ በአዲሱ ደንብ ተቋቁሟል ተብሏል፡፡

 

ለማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ድጋፍ በመስጠት የቴክኖሎጂ ሽግግር ማፋጠን፣ እንዲሁም ኢንዱስትሪው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ማብቃት ኢንስቲትዩቱን ለማቋቋም ካስፈለጉበት ዋነኛ ዓላማዎች ተጠቃሽ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

እንደ አዲስ የተቋቋመው ኢንስቲትዩት የማዕድን እንዱስትሪ ልማት ለማስፋፋት የሚያስችሉ የፕሮጀክት ፕሮፋይሎችን ማዘጋጀትና ማሠራጨት፣ ወደ ዘርፉ ለሚገቡ ባለሀብቶች የአዋጭነት ጥናት ማድረግ፣ በፕሮጀክት አፈጻጸም ላይ ዕገዛ ማድረግ፣ እንዲሁም በአፈጻጸም ወቅት ለሚከሰቱ ችግሮች መፍትሔ መስጠት ከተሰጡት ሥልጣንና ተግባር ተጠቃሽ እንደሆነ ታውቋል፡፡

በማዕድን ልማት ዘርፍ ለሚሰማሩ ባለሀብቶች የቴክኖሎጂ መረጣ፣ ድርድር፣ የግንባታ፣ የተከላና ሙከራ ምርቶች ድጋፍ መስጠት የኢንስቲትዩቱ ሌላው የተግባር ምኅዳር መሆኑ በማቋቋሚያ ደንቡ ላይ ሠፍሯል፡፡ በምርት ሒደት፣ ዕቅድና ጥራት ቁጥጥር ላይ ድጋፍና ዕገዛዎችን ማድረግ እንዲሁ ይገኙበታል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ባለሀብቶች ለሚያመርቱዋቸው ምርቶች ዓለም አቀፍ የፍተሻ ላቦራቶሪ እንዲያቋቁሙ ከማበረታት ባሻገር፣ ተወዳደሪ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ሰርተፊኬሺን እንዲያገኙ የሚያስችል ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

ከጥሬ  ዕቃ አመራረት እስከ ዓለም አቀፍ ገበያ የምርቶች ዕሴት ሰንሰለት ውስጥ በሚገኙ አካላት መካከል ያለው ትስስር ውጤታማ  እንዲሆን፣ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል ማድረግ የማዕድን ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ኃላፊነት እንደሚሆን ተመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል የቀድሞውን ኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በመሻር የጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት በመባል ተጠሪነቱ ለማዕድን ሚኒስቴር የሆነው ተቋም፣ መሠረታዊ የጂኦሎጂ፣ የጂኦ ኬሚስትሪና የጂኦ ፊዚክስ ጥናት በማካሄድ የማዕድን፣ የኢንጂነሪንግ ጂኦሎጂ፣ የጂኦ ተርማል ሀብትና የሌሎች የሥነ ምድር መረጃ ሽፋን ተደራሽነትን እንዲያሳድግ በሚል እንደ አዲስ ተቋቁሟል፡፡

የግብርና ምርትን የሚያሳድጉ፣ ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉና ለመሠረተ ልማት የሚያገለግሉ የማዕድናትና ሌሎች የሥነ ምድር መረጃዎችን በመፈለግ፣ ለአገራዊ ኢንዱስትሪ ልማት ተደራሽ ማድረግ ኢንስቲትዩት የሚያከናውነው ጥናት አካል እንደሚሆን ታውቋል፡፡

የአገሪቱን የቆዳ ሽፋን የሚያካልል መሠረታዊ የጂኦሎጂ፣ የማዕድን፣ የጂኦ ተርማል፣ የጂኦ ፊዚክስ፣ጂኦ ኬሚስተሪና የኢንጂነሪንግ ጂኦሎጂ የማዕድናት ካርታ በኢንስቲትዩቱ በኩል የሚዘጋጅ ሲሆን፣ እንዲሁም የማዕድን ሀብት ክምችት ልየታ ቦታዎችን ጥናት ማዘጋጀትና ለኢንዱስትሪ ኢንስቲትዩት ማቅረብ የጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩት ሥልጣንና ተግባር እንዲሆን ተወስኗል፡፡

በሌላ በኩል የጂኦሎጂካል ኢንስቲትዩቱ የማዕድን፣ የነዳጅ ዘይትና የተፈጥሮ ጋዝ፣ የጂኦ ተርማልና የኢንጂነሪንግ ጂኦሎጂ መሠረታዊ መረጃዎችን በመሰብሰብ በየብስና በውኃ አካላት ላይ ጥናትና ምርምር ያካሂዳል፡፡ በተጨማሪም የክምችታቸውን መጠንመገመትና ክምችቱ የሚገኝባቸውን ሥፍራዎች ድንበር ለይቶ እንዲያካልልና በትንተና እንዲያመለክት መሥሪያ ቤቱ ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡

የሥነ ምድር ጥናትና ምርምርን አቅም ለማጎልበት የሚያስችሉትን የመረጃ፣ የቁፋሮ፣ የላብራቶሪና የፍለጋ ሥራዎችን ገበያን መሠረት በማድረግ ለመንግሥትና ለግል ዘርፉ በመስጠት የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ ማድረግ ሌላው የኢንስቲትዩቱ ኃላፊነት እንደሆነ በማቋቋሚያ ደንቡ ላይ የሠፈረ ሲሆን፣ በተጨማሪም የሥነ ምድር ጥናትከወቅቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር አብሮ ለማስኬድ ከአገር ውስጥ፣ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር የትብብር ግንኙነቶችንና ስምምነቶችን የሚተገብር ይሆናል ተብሏል፡፡

 

መጋቢት 17 ቀን 2014 ዓ.ም. በተካሄደው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስድስተኛ መደበኛ ስብሰባ  11 የአስፈጻሚ ተቋማትን አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በቀረቡ ረቂቅ ደንቦች አደረጃጀት፣ ሥልጣንና ተግባር ለመወሰን በቀረቡ ረቂቅ ደንቦች ላይ ተወያይቶ ደንቦቹ በነጋሪት ጋዜጣ ታትመው ከወጡበት ቀን ጀምሮ ሥራ ላይ እንዲውሉ መወሰኑ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ የስፔስ ሳይንስና ጂኦ ስፓሻል ኢንስቲትዩት፣  የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን፣ የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ ደን ልማትን ባለሥልጣን፣ የእንስሳት ልማት ኢንስቲትዩት፣ የእንስሳት ጤና ኢንስቲትዩት፣ የአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩትና የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ሌሎች በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 መሠረት እንደ አዲስ መቋቋማቸው ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች