Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአማራ ክልል የመልሶ ማልማት ግንባታ ለክልሉ ተቋራጮች ቅድሚያ እንዲሰጥ ጥያቄ ቀረበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሰሜኑ የኢትዮጵያ ጦርነት ጋር ተያይዞ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ውድመት በደረሰበት፣ በአማራ ክልል የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ዝግጅት፣ በኢኮኖሚ መቀዛቀዝና በጦርነቱ ሳቢያ ከሥራ ተገልለው የቆዩት የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ቅድሚያ ዕድል እንዲሰጣቸው ጥያቄ ቀረበ።

 

ጥያቄውን ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጨምሮ በተለያየ ደረጃ ለሚገኙ ቢሮዎች ያቀረበው የአማራ ክልል የኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር መሆኑን የማኅበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ሙሉቀን ቢተው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንዳብራሩት፣ በክልሉ የሚገኙ በርካታ የሥራ ተቋራጮች በኢኮኖሚ መቀዛቀዝና በተካሄደው ጦርነት ምክንያት ለረዥም ጊዜ ከሥራ ተገልለው ቆይተዋል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ ከከፍተኛ የማሽኖች ውድመት አንስቶ፣ በዝርፊያና በሌሎች ጉዳቶች ሳቢያ ችግር ላይ የወደቁ  በርካታ ተቋራጮች እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

ተቋራጮቹ ያከናውኗቸው በነበሩ ግንባታዎች ላይ በጦርነቱ ጉዳት መድረሱ ተገልጾ፣ በዚህ ወቅት ክልሉ ከሚገኝበት ሁኔታ አኳያ ለግንባታዎች የዋጋ ማስተካከያ እንደማይጠይቁ ማኅበሩ አስታውቋል፡፡ ነገር ግን በክልሉ ዝግጅት እየተደረገበት በሚገኘው የመልሶ ማልማት ግንባታ ማለትም በትምህርት ቤቶች፣ በሆስፒታሎች፣ በጤና ጣቢዎች፣ በጤና ኬላዎችና በሌሎች ግንባታዎች ተጎጂ የሆኑት የክልሉ ተቋራጮች በቀጥታ ተሳታፊ እንዲሆኑ ማኅበሩ ጥያቄ አቅርቧል፡፡

በመልሶ ማልማት ሥራው የክልሉን ተቋራጮች ማሳተፍ በርካታ ጥቅሞች እንደሚኖረው የተናገሩት አቶ ሙሉቀን፣ አንደኛው ተቋራጮቹ የጉዳቱን አስከፊነት ስለሚረዱ በቁርጠኝነት መሥራታቸው ሲሆን፣ በሌላ በኩል በጦርነቱና ቀደም ብሎ ለገጠማቸው ጉዳትና ውድመት ማገገሚያ እንደሚሆናቸው አስረድተዋል፡፡

ጥያቄውን በተደጋጋሚ ለሚመለከታቸው የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ቢሮ፣ የገንዘብ ቢሮ፣ የትምህርት ቢሮ፣ የከተማ ልማትና የኮንስትራክሽን ቢሮ፣ እንዲሁም የፍትሕ ቢሮ እንዳቀረቡ ያስታወቁት አቶ ሙሉቀን፣ እስካሁን ምላሽ ለማግኘት አልተቻለም ብለዋል፡፡

በማኅበሩ ሥር የሚገኙት ከደረጃ አንድ እስከ አሥር የሚደርሱ ሥራ ተቋራጮች ማናቸውንም የመልሶ ማልማት ሥራዎችን የመሥራት አቅም እንዳላቸው የገለጹት አቶ ሙሉቀን፣ የተሳታፊነት ዕድሉ ከተገኘ ማኅበሩ የሚያቀርባቸው ተቋራጮች ተገቢውን መሥፈርት የሚያሟሉና አቅም ያላቸው እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡

‹‹አንዳንድ የፌዴራል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የመልሶ ማልማት ግንባታ ሥራውን ለኢትዮጵያ የግንባታ ተቋራጮች ማኅበር ለመስጠት በሒደት ላይ መሆናቸውን ተረድተናል፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ ሆኖም የአማራ ክልል ሥራ ተቋራጮች ማኅበር በሥሩ ከሚገኙት ተቋራጮች ብዙኃኑ ከተጠቀሱት ችግሮች ጋር ተያይዞ ችግር ላይ በመውደቃቸው፣ በመልሶ ማልማት ግንባታ በቀጥታ ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ማኅበሩ 345 ያህል አባላት እንዳሉት ያስታወቁት አቶ ሙሉቀን፣ ከግንባታ ዋጋ ማሻቀብና በጦርነቱ ምክንያት ለከፍተኛ ጉዳት የተጋለጡት ቁጥር 200 ይደርሳሉ ብለዋል፡፡

ጥያቄው የቀረበላቸው አካላት በጎ ምላሽ እንደሚሰጡ ተስፋ እንዳለው ያስታወቀው ማኅበሩ፣ ይህ የማይሆን ከሆነ ጥያቄውን በግንባር ከማቅረብ አንስቶ የተለያዩ የሚዲያ አውታሮችን በመጠቀም ምላሽ እንዲገኝ  ጥረት ይደረጋል ብሏል፡፡

ሪፖርተር በጉዳዩ ላይ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የከተሞችና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢያዝን እንኳንሆነ ለማነጋገር ባደረገው ጥረት ማኅበሩ አቤቱታውን ለቢሮው እንዳቀረበ ተናግረው፣ ነገር ግን ለሚመለከተው ዘርፍ ተመርቶ የዘርፉን አስተያየት እንዲቀርብላቸው እየጠበቁ መሆናቸው ተናግረዋል፡፡

ኮንትራት የመስጠትና የመንሳት ጉዳይ የቢሮው ኃላፊነት እንዳልሆነ ገልጸው፣   የሚመለከተው የክልል አካል በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች