በኢትዮጵያ በበይነ መረብ አማካይነት በሕፃናት ላይ በከፍተኛ መጠን ፆታዊ ጥቃት እንደሚፈጸምና በዓመት 300 ሺሕ የሚደርሱ ሕፃናት ተጠቂ መሆናቸው በጥናት ተመላከተ።
በኢትዮጵያ የኢንተርኔትና የሞባይል ስልኮች መበራከት ምክንያት፣ በሕፃናት ላይ የሚፈጸሙ የበይነ መረብ ፆታዊ ጥቃቶችን ለማወቅ ኢንተርፖል፣ ዩኒሴፍና ኢሲፒኤቲ የተባሉ ድርጅቶች ጥናት አድርገዋል።
ጥናቱ ከመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ሲካሄድ የነበረ መሆኑን፣ በዋናነትም በሕፃናት፣ በተለይ በታዳጊ አገሮች እየደረሰ ያለውን ፆታዊ ጥቃት የዳሰሰ መሆኑን በኢትዮጵያ የኢሲፒኤቲ (ECPAT) ተወካይ አቶ ያሬድ አሰፋ ተናግረዋል። ስለሕፃናት ጥቃት ሲነሳ በተለይ በኢትዮጵያ በአካል ስለሚደረግ ጥቃት እንጂ፣ በበይነ መረብ ስለሚደርስ ጥቃት ትኩረት አልተሰጠም ብለዋል።
በዚህም መነሻነት የጥቃቱን መጠንና ጥቃቶቹ የሚስተናገዱበትን የሕግ ጉዳዮች ለመፈተሽ፣ ሦስቱ ተቋማት ለአራት ዓመታት በከተሞች፣ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ጥናት ሲያካሂዱ መቆየታቸውን ገልጸዋል። በጥናቱ 1‚000 ሕፃናት፣ አሥር የመንግሥት አካላት፣ 30 በልጆች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ተቋማትና ግለሰቦች መካተታቸው ተገልጿል፡፡
በጥናቱ ግኝት መሠረት በተለይ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ብቻ በኢትዮጵያ ከ12 እስከ 17 ዓመት ዕድሜ ካላቸው የበይነ መረብ ተጠቃሚ ሕፃናት ውስጥ አሥር በመቶ ያህሉ ‹‹ለከፋ›› የበይነ መረብ ወሲባዊ ጥቃት ተዳርገዋል። ይህም ሕፃናቱ በወሲባዊ ተግባራት እንዲሳተፉ በማስገደድና መደለያ ገንዘብ በመስጠት የተፈጸሙ ናቸው ተብሏል። በዚህም መሠረት በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 300 ሺሕ ያህል ሕፃናት በበይነ መረብ አማካይነት ፆታዊ ጥቃት እንደሚደርስባቸው ጥናቱ አመልክቷል።
በበይነ መረብ ጥቃት የሚፈጸምባቸው ሕፃናት የሚደረግላቸውን የሕግ ከለላ የዳሰሰው ጥናቱ ወሲባዊ ጥቃት ከደረሰባቸው ሕፃናት ውስጥ ለሕግ አካላት አቤቱታ ያቀረቡ አለመኖራቸውን የገለጹት አቶ ያሬድ፣ ይህም መደበኛ የአቤቱታ ማቅረቢያ መንገድ ባለመኖሩ ምክንያት መሆኑን አስረድተዋል። በሕግ ሥርዓቱ ውስጥም ጉዳዩን ለማስተናገድ የሚያስችል አሠራርም ሆነ ግንዛቤ ያለው የሕግ አካል አለመኖሩን፣ በጥናቱ ለማወቅ ተችሏል ብለዋል።
ፌስቡክና ቴሌግራም በዋናነት የሕፃናት ፆታዊ ጥቃት የሚፈጸምባቸው ማኅበራዊ መገናኛዎች መሆናቸውን ያመለከተው ጥናቱ፣ እስከ 27 በመቶ የሚደርሱ ጥቃቶች በማይታወቁ ሰዎች ጭምር የተፈጸሙ መሆናቸውን አብራርቷል። የሕፃናቱን ምሥል በመጠቀም ማስፈራራትና በገንዘብ መደለል ለጥቃቱ ዋነኛ መንገዶች ሲሆኑ፣ አብዛኛው ጥቃት የሚፈጸመው ሕፃናቱ በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል።
በጥናቱ ግኝት መሠረት በተለይ የፖሊስ አደረጃጀት የበይነ መረብ ጥቃት የሚስተናገድበት አሠራር እንዲኖረው፣ ባለሙያዎችም በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ማድረግ እንደሚያስፈልግ አቶ ያሬድ ጠቁመዋል። በተጨማሪም በሕግ ሥርዓቱ ውስጥ ይህንን ድርጊት ለመከላከል የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እንዲካተት ማድረግ ይገባል ብለዋል።
ጥናቱ በአጠቃላይ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ኬንያና ኡጋንዳን ጨምሮ በ13 አገሮች የተካሄደ መሆኑን፣ ሰባት ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደተደረገበትም አቶ ያሬድ ገልጸዋል።