Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የመስኖ ፕሮጀክት ተጠቃሚዎች ሁለት ቢሊዮን ብር እንዳሳጡት አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ከ2.3 ቢሊዮን ብር በላይ አለመሰብሰቡም ታውቋል

በአገሪቱ የሚገኙ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን እንዲያስተዳድር ኃላፊነት የተሰጠው የኢትዮጵያ ኮንስራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ የመስኖ ውኃ ከሚያቀርብላቸው ተቋማትና ማኅበራት ማግኘት የነበረበትን ሁለት ቢሊዮን ብር ያህል ገቢ ማግኘት አልቻልኩም አለ፡፡ ከመስኖ ፕሮጀክቶቹ የሚጠቀሙ የግልና የመንግሥት አልሚዎች ከወንዝ እየተጠለፈ ለሚመጣላቸው የመስኖ ውኃ ክፍያ ለመፈጸም ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ኮርፖሬሽ አስታውቋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በ2009 ዓ.ም. በአገሪቱ በሙሉ ያሉ የመስኖ ውኃ ፕሮጀክቶች የተሰጡት የመስኖ ፕሮጀክቶቹን እየገነባና እያለማ ለተጠቃሚዎች ውኃ በማቅረብ ገቢ እንዲሰበስብ ታስቦ መሆኑን፣ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ አያሌው (ኢንጂነር) ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ልምድ በውጭ አገሮች የሚሠራበት በመሆኑም በኢትዮጵያ ለመተግበር ታቅዶ የነበረ መሆኑንም አክለዋል፡፡

የመስኖ ፕሮጀክቶቹን ማስተዳደር ውኃ እንደየመጠኑ እንዲለቀቅ ማድረግ፣ የግድብ በሮችን መክፈት፣ እንዲሁም ግድቦችን መጠገንን ያካትታል፡፡ ከመስኖ ውኃው ተጠቃሚ የሚሆኑ ተቋማትና ማኅበራትም የተጠቀሙትን የመስኖ ውኃ አገልግሎት ክፍያ ሲፈጽሙ ገንዘቡ ለጥገናና ሌሎች አስተዳደራዊ ወጪዎች ክፍያ ይውላል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በዚህ ዕቅድ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ሲገነባና ሲያስተዳደር ለዓመታት ቢቆይም፣ ይሁንና ዕቅዱ እንደታሰበው መሬት ላይ መውረድ አልቻለም፡፡ ስኳር ኮርፖሬሽንን ጨምሮ ተጠቃሚ ተቋማትና የግል አልሚዎች ከወንዝ ተጠልፎ ለሚመጣው ውኃ ክፍያ ለመፈጸም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው፣ ኮርፖሬሽኑ ሊያገኝ ይገባ የነበረውን ሁለት ቢሊዮን ብር ያህል ገቢ አላገኘም፡፡

በዚህም ምክንያት ከ2009 ዓ.ም. ጀምሮ የመስኖ አውታሮችን እየገነባና እያስተዳደረ ያለው ኮርፖሬሽኑ ለፕሮጀክቶቹ የወሰደውን ብድር መክፈል እንዳልቻለ ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ተጨማሪ  በኮርፖሬሽኑ ተቀጥረው የፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ለተሳተፉ የደቡብ ውኃ ሥራዎች፣ የኦሮሚያ ውኃ ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ እንዲሁም የዲዛይን ሥራውን ለሠራው አካልና ለውጭ አማካሪዎች ክፍያ መፈጸም አለበት፡፡

እንደ ዮናስ (ኢንጂነር) ገለጻ የችግሩ አንዱ ምንጭ ለመስኖ ውኃ አቅርቦቱ ምን ያህል ገንዘብ እንዴት ይከፈላል የሚለው ዝርዝር አፈጻጸም የሌለው መሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም ከወንዝ ለተጠለፈ ውኃ ክፍያ የመፈጸም ልምድ ባለመኖሩ አልሚዎቹ ክፍያ ለመፈጸም ፈቃደኛ አይደሉም፡፡

ኮርፖሬሽኑ በዚህ ምክንያት ያጣውን ገቢ ለማግኘት ከገንዘብና መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር ጋር ንግግር  እየተደረገ መሆኑን ያስታወቁት ሥራ አስፈጻሚው፣ በብደር የተወሰደው ገንዘብ ሥራው ላይ ስለመዋሉ ጥናት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በዚህም የተሠራው ሥራ ከተከፈለው ገንዘብ በላይ መሆኑ ተረጋግጦ ኮርፖሬሽኑ ወጪውን እንዲያገኝ ታስቧል፡፡

ሦስት የመንግሥት ኮንስትራክሽን ድርጅቶች ተዋህደው በ2008 ዓ.ም. የተቋቋመው የኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን በተያዘው በጀት ዓመት የውል ዋጋቸው ከ37.1 ቢሊዮን ብር የሆኑ የ49 ፕሮጀክቶችን ግንባታ በማከናወን ላይ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ በስድስት ወር አፈጻጸሙ ለትርፍ ከሚገነቡ ፕሮጀክቶች 4.3 ቢሊዮን ብር ለማግኘት አቅዶ 2.2 ቢሊዮን ብር ገቢ የሚያስገኝ ሥራ በመሥራት የዕቅዱን 51.6 በመቶ አሳክቷል፡፡ ለዕቅዱ አለመሳካትም የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በምክንያትነት ተጠቅሷል፡፡

ከዚህ ባሻገር ኮርፖሬሽኑ እስከ አንደኛው የበጀት ዓመት አጋማሽ ማጠናቀቂያ ድረስ 2.35 ቢሊዮን ብር ሒሳብ አልሰበሰበም፡፡ ያልሰበሰበው ሒሳብ ከትራንስፖርትና ውኃ መሠረተ ልማት ኮንስትራክሽን ዘርፎች፣ ከሕንፃና ቤቶች ኮንስትራክሽን ዘርፍ፣ ከማኔጅመንት ክፍያ፣ እንዲሁም ከቫት ተመላሽ መሰብሰብ የነበረበት ነው፡፡ በአምስት ዘርፎች ከተከፋፈለው ያልተሰበሰበ ሒሳብ ውስጥ ከፍተኛውን ወይም 1.4 ቢሊዮን ብር ያህሉ ከቫት ተመላሽ መሆን የነበረበት ገንዘብ ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዮናስ (ኢንጂነር) እንደሚያስረዱት፣ ሒሳቡ ያልተሰበሰበበት የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ተቋማት በጀት ያልያስያዙ ሲሆን፣ አንዳንድ ፕሮጀክቶች ደግሞ ከአማካሪ ድርጅቶች ጋር ተያይዞ ያልተጠናቀቁ ሥራዎች በመኖራቸው ነው፡፡ በተጨማሪም ከኮርፖሬሽኑ ኃላፊነት ውጪ በሆኑ ምክንያቶች የፕሮጀክቶች ሥራ በመጓተታቸው ክፍያዎች አልተፈጸሙም፡፡ እነዚህን በተመለከተ ግን ችግሩ ከኮርፖሬሽ ካልሆነና ወጪ የሚያስወጡ ከሆኑ፣ ከፍያው ለኮርፖሬሽኑ መፈጸም ስላለበት ክፍያ እንዲፈጸም ጥያቄ መቅረቡን ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ፕሮጀክቶችን ይዞላቸው ክፍያ ያልፈጸሙ የመንግሥት ተቋማት መኖራቸውን የጠቀሱት ዮናስ (ኢንጂነር)፣ ከእነዚህ ውስጥ አንዱ የሆነው የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ጋር ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ያልተከፈለ ገንዘብ መኖሩን ተናግረዋል፡፡ ሒሳብ ባለመክፈላቸው ጉዳያቸው በሕግ እየተያ ያሉ ተቋማት መኖራቸውንም አስታውቀዋል

ካልተሰበሰበ ሒሳብ ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚይዘው ከቫት ተመላሽ ሒሳብ ግን፣ ከገቢዎች ጋር በተደረገ ንግግር ኮርፖሬሽኑ የሚኖሩበት የተለያዩ የግብር ክፍያዎች ላይ እየተካካሰ እንዲሄድ እየተደረገ መሆኑን ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች