Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዘመን ባንክ አዲስ የክፍያ አገልግሎት ይፋ አደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ዘመን ባንክ እየሰጠ ያለውን አገልግሎት በማስፋት፣ የባንክ ተጠቃሚዎች በድረ ገጽ የሚደረጉ ክፍያዎችን ከማስተር ካርድ ክፍያዎች ጋር በማስተሳሰር በየትኛውም ቦታ ግብይት መፈጸም የሚያስችል አዲስ የክፍያ ዘዴ ይፋ አደረገ፡፡

ባንኩ አዲሱን አገልግሎት በተመለከተ በሰጠው መግለጫ፣ አገልግሎቱ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሲተገበር የመጀመርያ መሆኑን ገልጾ፣ የዘመን ባንክ የማስተር ቪዛ ካርድ የያዙ ደንበኞች በየትኛውም የዓለም ክፍል ሆነው ክፍያቸውን በዲጂታል መንገድ ለመፈጸም የሚያስችል ነው፡፡

ባንኩ ያመቻቸው መተግበሪያ፣ ደንበኞች የዘመንን ካርድ ይዘው በዓለም አቀፍ ገበያ መገበያየት የሚያስችላቸውን ዕድል የሚፈጥር ከመሆኑም ሌላ፣ ማንኛውንም ክፍያ በድረ ገጹ ለመፈጸም የሚያስችል ነው፡፡ ይህ አገልግሎት የተለያዩ ኩባንያዎችን ድረ ገጽ ከካርዶቹ ጋር በማስተሳሰር፣ በቀጥታ ክፍያዎችን መክፈል የሚያስችል እንደሆነም ተገልጿል፡፡ አገልግሎቱ ከባንኩ ደንበኞች ሌላ ሌሎች ተገልጋዮችንም መጠቀም የሚያስችል እንደሆነም ታውቋል፡፡  

ዘመን ባንክ ከማስተር ካርድ ጋር በመተባበር ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ የመጀመርያውን ከንንኪ ነፃ የተጓዦች ካርድ በማስተዋወቅ፣ ደንበኞች በጉዟቸው ወቅት ያለ ጥሬ ገንዘብ በዶላርና ዩሮ ያለ ሥጋት ክፍያቸውን እንዲፈጽሙ የሚያስችል አሠራር መተግበሩ የሚታወስ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ ሌላ ተያያዥ አገልግሎት ይዞ መቅረቡ ተነግሯል፡፡  

ይህ የማስተር ካርድ የክፍያ አገልግሎት በተለያዩ በይነ መረብ ድረ ገጾች በተንቀሳቃሽ ስልክ መተግበሪያዎችና በተንቀሳቃሽ ክፍያ መፈጸማቸው፣ ማሽኖች ላይ የአገልግሎት ቅልጥፍናና መናበብ በመፍጠር ደኅንነቱ የተጠበቀ ዘመናዊ የመገበያያ መንገድ ሊሆን መቻሉም ተጠቅሷል፡፡

በትናንትናው ዕለት ይፋ የተደረገው አዲስ አገልግሎት፣ የማስተር ካርድ የክፍያ አገልግሎት በድረ ገጽ የሚደረጉ ክፍያዎችን ከማስተር ካርድ የክፍያ ዘዴዎች ጋር በማጣመር በዘመን ባንክ፣ ማስተር ካርድና ቪዛ የካርድ ግብይት እንዲፈጸም የሚያስችል መሆኑን የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ዘበነ ገልጸዋል፡፡ ደንበኞቻችን (Merchants) ለደንበኞቻቸው ምቹና ባሉበት ሆነው ክፍያቸውን በዲጂታል መንገድ እንዲያከናውኑ የሚያስችላቸው መሆኑን አገልግሎቱን በተመለከተ ከተሰጠው ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ከዚህም ሌላ በዋናነት የክፍያ አገልግሎቱ ተግባራዊ መሆን ደንበኞቻችን ከክፍያ ጋር በተያያዘ ዓለም አቀፍ ተደራሽነታቸውን እንዲጨምርላቸው ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ መሆኑ ነው ተብሏል፡፡ ይህንን አዲስ አገልግሎት ይበልጥ እንዲጎላ ተጨማሪ ሥራዎች የሚሠሩ መሆኑን የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ በተለይ ባንኩ በቅርቡ ተግባራዊ በሚያደርገው አዲሱ ስትራቴጂ የደንበኞች አገልግሎትና ዘመናዊነት በአዳዲስ የቴክኖሎጂ ትግበራ እየታገዘ የበለጠ ለማገለገል የሚያስችል ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑንም ባንኩ ገልጿል፡፡

የባንኩ የኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አመሐ ታደሰ  በበኩላቸው፣ ይህ የማስተር ካርድ ክፍያ መስጫ ደንበኞች በሻጮች ዲጂታል ክፍያ መሰብሰቢያ ላይ ቀለል ብሏቸው መጠቀም እንዲችሉ ማስቻሉ ዋነኛ ጠቀሜታው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተለይ ሆቴሎች፣ የንግድ ሱቆች፣ የጉዞና አስጎብኚ ድርጅቶች፣ አየር መንገዶች የንግድ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች፣ መካከለኛና ትልልቅ ድርጅቶች ከዚህ የተቀናጀ የኢ ኮሜርስ አገልግሎት መስጫ መንገድ እጅጉን የሚጠቀሙ መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡ ይህ የክፍያ መፈጸሚያ የሆቴሎችን የቀን ተቀን ሥራ ለማቀላጠፍና እንከን የለሽ የክፍያ መፈጸሚያ መንገዶችን ለደንበኞች የሆቴል ቦታ ለማስያዝና ቆይታቸውን ጨርሰው ሲወጡ ለሚፈጽሟቸው ክፍያዎች የሚያገለግል፣ እንዲሁም በአየር መንገዱ ዘርፍ ብዙ ጥቅም የሚሰጠውን ይህንን ኢ ኮሜርስ መጠቀም ደንበኞቻቸውን ቦታ እንዲያስይዙና ለቲኬቶቻቸው በበይነ መረብ እንዲከፍሉ የሚያስችል ነው፡፡  

የማስተር ካርድ የክፍያ መንገዶችን በመጀመር ዘመን ባንክ በኢትዮጵያ ዲጂታል ፕላት ፎርም አሻራውን እያሳረፈ እንደሚገኝ የጠቀሱት አቶ ደረጀ፣ በመንግሥት የተቀመጠውን የ2025 ዲጂታል ዕቅድ በማሳካት በኩል የበኩሉን ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ አገልግሎቱ ክፍያዎችን በቪዛና ማስተር ካርደ በበይነ መረብ ደብዳቤ ትዕዛዝ፣ በስልክ ትዕዛዞች፣ በጥሪ ማዕከሎች፣ አይቪአር፣ ሞባይል ኮሜርስ፣ በኩል መፈጸም ያስችላል ብለዋል፡፡

ዘመን ባንክ በኢትዮጵያ የካርድ ባንኪንግ በማስተዋወቅ ቀዳሚ ከሚባሉ የግል ባንኮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ባንኩ እንዲህ ያለውን ቴክኖሎጂ በማስፋፋት አሁንም ቀጣይ ሥራዎችን እንደሚተገብር አስታውቋል፡፡ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ12 ዓመታት በላይ የዘለቀው ዘመን ባንክ፣ የ2014 የግማሽ የሒሳብ ግርድፍ ሪፖርቱ እንደሚያሳየውም፣ በስድስት ወራት ውስጥ ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት ከ1.14 ቢሊዮን ብር በላይ ማትረፍ የቻለ ሲሆን፣ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ ያለው መሆኑ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች