Monday, September 25, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትበአዳዲስ ክብረ ወሰኖች የታጀበው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና

በአዳዲስ ክብረ ወሰኖች የታጀበው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና

ቀን:

ሙሉ ትኩረቱን በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ላይ አድርጎ የሰነበተው የአትሌቲክስ ቤተሰብ፣ መዳረሻውን የሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ በሆነችው ሐዋሳ ከተማ ላይ አድርጓል። በዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና እንዲሁም በተለያዩ የአውሮፓ ከተሞች በተዘጋጁት ውድድሮች ላይ አትሌቶቻቸውን በመያዝ ቆይታ ያደረጉ ዕውቅ አሠልጣኞች፣ ማናጀሮች እንዲሁም አትሌቶች በሐዋሳ ከትመዋል።

በርካታ ብርቅዬ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች መነሻ የሆነው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ ለመካፈል ክለቦች፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ ተቋማትና አካዴሚዎች በሩጫና የሜዳ ተግባር ላይ ለመታደም ሐዋሳ ተገኝተዋል፡፡

51ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ላይ በሩጫ ውርወራና ዝላይ (ሩውዝ) ለመካፈል በሁለቱም ጾታዎች 1,033 አትሌቶች ከመጋቢት 19 እስከ 24 ቀን 2014 .ም. ተሳትፎ ያደርጋሉ።

በመጪው ሐምሌ ለመጀመርያ ጊዜ በአሜሪካ ኦሪገን በሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናም ሆነ በሞሪሸሱ የአፍሪካ ሻምፒዮና ላይ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶችን ለመምረጥ ግቡን ያደረገው የሐዋሳው ሻምፒዮና ገና ከጅምሩ ብሔራዊ ክብረ ወሰኖች እየተሠበሩበት መካሄዱን ቀጥሏል። በቅብብሎሽ ቀጥሎ ከአምስት አሠርታት በላይ ያስቆጠረው ሻምፒዮናው ዛሬም ተሰፋ የሚጣልባቸውን አትሌቶች እያበረከተ ይገኛል።

ሰኞ መጋቢት 19 ቀን 2014 .ም. በሐዋሳ ስታዲየም በጀመረው ሻምፒዮናው በ10 ሺሕ ሜትር ወንዶች ፍጻሜ ታደሰ ወርቁ 28:11.92 በመግባት ለ16 ዓመታት በስለሺ ስህን የቆየውን ክብረ ወሰን ማሻሻል ችሏል። ስለሺ የርቀቱን ክብረ ወሰን 1996 .ም. የያዘው 28:16.23 በመግባት ነበር። የደቡብ ፖሊስ ክለብ አትሌት የሆነው ታደሰ በረዥም ርቀቱ ተስፋ ከተጣለባቸው አትሌቶች አንደኛው ነው። አትሌቱ በኬንያ በተካሄደው የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ሻምፒዮና 3,000 ሜትር ወርቅ እንዲሁም በ5,000 ሜትር የብር ሜዳልያ ማግኘት ችሏል። ታደሰ ለዘንድሮው የኦሪገን የዓለም ሻምፒዮና ከወዲሁ ትኬቱን የቆረጠበትን ድል በሐዋሳ ሻምፒዮና ማሳየት ችሏል።

በወንዶች 10 ሺሕ ፍጻሜ ሚልኬሳ መንገሻ ከኦሮሚያ ክልል 28:27.26 ሁለተኛ፣ እንዲሁም ገመቹ ዲዳ ከኤሌክትሪክ ክለብ በ28:29.93 ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል። በማግስቱ ማክሰኞ መጋቢት 20 ቀን በተደረገው የ10 ሺሕ ሴቶች ፍጻሜ ሌላኛው በሻምፒዮናው ድምቀት የሆነ ውድድር ነበር። በፍጻሜው ግርማዊት ገብረ እግዚአብሔር ከኤሌክትሪክ ክለብ 31:21.48 በመግባት የሻምፒዮናውን ክብረ ወሰን መስበር ችላለች።

ግርማዊት በ2011 .ም. የትራንስ ኢትዮጵያ አትሌት በነበረችው ለተሰንበት ግደይ ተይዞ የነበረውን 32:10.13 ክብረ ወሰን ማሻሻል ችላለች። የመከላከያዋ ሐዋ ፈይሳ 31:48.84 ሁለተኛ፣ እንዲሁም አበራ ሽማና ስቦ ከኤሌክትሪክ በ32:10.74 ሦስተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።

በሻምፒዮናው ከአትሌቲክስ ባሻገር በሜዳ ተግባር ዲስከስ ውርወራ፣ ሥሉስ ዝላይና አሎሎ ውርወራ ክብረ ወሰኖች ተሻሽለውባቸዋል።

ለዓለም አቀፍ ውድድሮች እንደ ቅደመ ማጣሪያ ሆኖ የሚያገለግለውና በአገር ውስጥ ሻምፒዮናው ተካፍለው ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃን በመያዝ ያጠናቀቁ አትሌቶች በቀጥታ የሚመረጡበት ሒደት ቢኖርም፣ በተለያዩ የዓለም ሻምፒዮናዎች ስማቸው የገነነ አትሌቶች በአገር ውስጡ ውድድር ላይ ሲካፈሉ አይስተዋልም። በዚህም ምክንያት በምርጫ ወቅት የክርክር መንስዔ ሲሆኑ ይስተዋላል።

ምንም እንኳን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ማንኛውም አትሌት በአገር ውስጥ ሻምፒዮናዎች ላይ መሳተፍ ካልቻለ፣ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ መካፈል አይቻልም የሚል አስገዳጅ ሕግ ባይኖርም ማንኛውም አትሌት የአገር ውስጥ ሻምፒዮና ላይ መካፈል ይኖርበታል ብለው የሚያነሱ አሉ። ከዚህም በተቃራኒው ደግሞ በዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎች ጥሩ ስዓት ያላቸው አትሌቶች በአገር ውስጥ ውድድሮች መሳተፍ አይጠበቅባቸውም ብለው የሚከራከሩም አሉ።

ከፍተኛ ፉክክር በተስተዋለበት የወንዶች 10 ሺሕ ሜትር ፍጻሜ ላይ የተገኘው የቶኪዮ ኦሊምፒክና የቤልግሬዱ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቱ ሰለሞን ባረጋ አትሌቶቹን ከማበረታታት ባሻገር በአገር ውስጥ ሻምፒዮናው መካፈል ባለመቻሉ ይቅርታ ጠይቋል።

የእግር ኳሱ ጨዋታዎችን በማስተናገድ የምትታወቀው ሐዋሳ ከተማ በቀሪዎች ቀናት የተለያዩ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናዎችን የምስተናግድ ሲሆን፣ ወቅታዊ የአየር ንብረቷም ለአትሌቶቹ የተመቸ ይመስላል። በዓለም አቀፍ ውድድሮች አገራቸውን ወክለው፣ እንዲሁም በግላቸው የሚውዳደሩ አትሌቶች በማሠልጠን የሚታወቁ አሠልጣኞች እንዲሁም ማናጀሮች በሻምፒዮናው አዳዲስና ተተኪ አትሌቶችን መንጥረው ለማውጣት በትኩረት ሲከታተሉ ተስተውሏል። ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተለያዩ የዓለም አደባባዮች ባንዲራ ከማውለብለብ ባሻገር በግል ሕይወታቸው ስኬታማ መሆን የቻሉትን ብርቅዬ አትሌቶች ስኬት የተመለከቱ አሠልጣኞች በሻምፒዮናው ተተኪ አትሌት ለማግኘት በንቃት መጠባበቅ ተቀዳሚ ሥራቸው ሆኗል።

ባለፉት የአገር ውስጥ ሻምፒዮናዎች የበላይነት ሲያሳዩ የነበሩት ጥቂት ክለቦች  በሒደት በጠንካራና አዳዲስ ክለቦች እየተፈተኑ ይገኛሉ። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እየተጠናከሩ ከመጡት ክለቦች መካከል ሲዳማ ቡና፣ ደቡብ ፖሊስ እንዲሁም ኤሌትሪክ ይጠቀሳሉ።  ክለቦቹ በተለይ በመካከለኛና በረዥም ርቀቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ አዳዲስ አትሌቶችን ማብቃት ችለዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና መካሄድ ከተጀመረበት 1963 ዓ.ም. ወዲህ ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ የተካሄደው ሁለት ጊዜ፣ ማለትም በ2005 .ም. በአሰላ ከተማና እንዲሁም ዘንድሮ በሐዋሳ ብቻ ነው።

በአዳዲስ ክብረ ወሰኖች የታጀበው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና

 

ለበርካታ ዓመታት በአዲስ አበባ ብቻ የተወሰነው ሻምፒዮናው በሐዋሳ መከናወኑን ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነ በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተሳትፎና ውድድር ዳይሬክተር አቶ አስፋው ዳኜ ያብራራሉ። እንደ ዳይሬክተሩ አስተያየት ከሆነ፣ ሻምፒዮናው በአዲስ አበባ ሲከናውን የአየር ንብረቱ ከፍተኛ (2000ሜ ከባህር ጠለል በላይ) በመሆኑ አትሌቶች ሰዓቶች ማሻሻል ሲቸገሩ እንደነበር ጠቅሰው፣ በሐዋሳ 1600ሜ ከባህር ጠለል መሆኑ ክብረ ወሰኖች ለማሻሻል ማመቸቱን ለሪፖርተር አስረድተዋል።

ዚህም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከዚህ ቀደም በተለያዩ አገሮች ሲያከናውን የነበረውን ቅድመ ማጣሪያ ወይም የሰዓት ማሟያ ውድድሮች ለማድረግ ዕድል እንደሚኖረው ይናገራሉ። በዚህም እንደ ባህር ዳር ያሉ ከተሞችን የመሮጫ መሠረተ ልማት ምቹ ማድረግ እንደሚያስፈልግም አክለዋል።

በሐዋሳው ሻምፒዮና አዲስ የመነሻ ቴክኖሎጂን (False Starter) ለመጀመርያ ጊዜ መጠቀም የተቻለ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ዳኞችን ከአዲስ አበባ እያጓጓዘ ሲጠቀም የነበረውን አሠራር በመቀየር በክልሉ የሚገኙ ዳኞች መጠቀሙን የፌዴሬሽኑ ዳሬክተር  አስረድተዋል።

 ሻምፒዮናው በተከታታይ ዓመታት ሲከናወን የቆየ ቢሆንም በ2012 .ም. በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ሳይከናወን ቀርቷል። ሻምፒዮናው ከግማሽ ምዕት ዓመታት በላይ ጉዞው እንደነ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ገዛኸኝ አበራ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ ብርሃኔ አደሬና መሠረት ደፋር የመሳሰሉ አትሌቶችን ማፍራት ችሏል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...