የኢትዮጵያ መንግስት ከወራት ጥበቃ በኋላ ከሳዑዲ ዓረቢያ ወደ አገራቸው የመለሳቸው ስደተኞች ዛሬ መጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም ጠዋቱ 3:00 ገደማ አዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፊያ ደርሰዋል። ወደ አገራቸው የተመለሱት 490 ሲሆኑ በሙሉ ሴቶችና ህፃናት ናቸው።
መንግስት ከሳዑዲ ወደ ኢትዮጵያ ሊመልሳቸው ያሰበው ከ100 ሺህ በላይ ስደተኞች ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ከሰባት እስከ 11 ወራት እንደሚወስድ አስታውቋል። ለመመለስ ምዝገባ ያደረጉት 45 ሺህ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውም ታውቋል።
በተያዘው ጊዜ ውስጥ ይመለሳሉ የተባሉትን 102 ሺህ ስደተኞች ወደ አገር ለማምጣት በየአንድ ቀን ልዩነት በረራዎች እንደሚኖሩና በቀን ሶስት በረራ እንደሚደረግ ተገልጿል። ዛሬ ጠዋት ከገቡት ስደተኞች በተጨማሪም ከሰዓት በኋላ ሌላ በረራ እንዳለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል።